Friday, 28 October 2016

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ግቡን እንዲመታ…..




ስሜነህ
ኢትዮጵያውያን ፍትሐዊ ጥያቄዎችን ቢያነሱም፤ ማንሳታቸውም የዴሞክራሲያዊ ስርአቱ መገለጫ ቢሆንም ይህን ሂደት የግብፅ መንግሥት ተቋማትና የኤርትራ መንግሥት   ለራሳቸው ዓላማ በመጥለፍ ኢትዮጵያን ለመበታተን ሲያጠነጥኑ ተደርሶባቸዋል። እነዚህ ሃገሮች በውስጥ የሚገኙ አፍራሽ ሃይሎችን በገንዘብ ሲደግፉና ሲያስታጥቁ የተደረሰባቸው ለመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት አሳማኝ ማስረጃዎችን እያቀረበ ነው፡፡
ጉዳዬ ከአስቸኳይ አዋጁ ጋር የተያያዘ ቢሆንም ይህን ለማብራራት በቅርቡ በአንዳንድ የአገራችን ክልሎች ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለመናድ ሲካሄዱ የቆዩ አፍራሽ እንቅስቃሴዎችን መሠረታዊ ባህርይና አንድምታ በትክክል ማስገንዘብ ተገቢ ይሆናል።
የአገሪቱ ሕዝቦች በሰላማዊ መንገድ ያቀረቡት ቅሬታን በመጥለፍ ወደ ሁከትና አውዳሚ እንቅስቃሴ ለመቀየር የተረባረቡ የውጭ ኃይሎች መኖራቸው የመጀመሪያው ነው፡፡ ኢትዮጵያ በህዳሴ ጉዞ ላይ መሆኗን የማይቀበሉ ሃገሮች ሊያተራምሱን በስፋት መንቀሳቀሳቸውና አሁንም እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ሁለተኛው እና የአዋጁን ፋይዳ ለመገንዘብ መጤን የሚገባው ጉዳይ ነው።
ከነዚህ ሃይሎች ባሻገርም ከጽንፈኛ ዳያስፖራዎች ጀምሮ በአባይ ወንዛችን ላይ የተጠቃሚነት መብታችንን ለማረጋገጥ የጀመርነውን እንቅስቃሴ ለማኮላሸት የሚንቀሳቀሱት ሁሉ ታላቁን የኢሬቻ በዓል ከማወክ ጀምሮ በልዩ ልዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ያካሄዱት ውድመትና ቃጠሎንም ስለአዋጁ ፋይዳና የግድነት ማስታወስ ያስፈልጋል ።
በተለይ ታላቁን የኢትዮጵያህዳሴ ግድብ ግንባታ የማንንም እጅ ሳንጠብቅ በመላ የሃገሪቱ ሕዝቦች ተሳትፎና በሃገራዊ አቅም በመተማመን መገንባት መጀመራችን ያስቆጣቸው አገሮች፣ ረዘም ላሉ ዓመታት ውስጥ ውስጡን ሲዘጋጁ ከርመው በአሁኑ ጊዜ ጽንፈኛ የዳያስፖራ ኃይሎች ከቀሰቀሱት ነውጥ ጋር በመመጋገብ አገሪቱን ለማተራመስ በቀጥታ መረባረባቸው እና አሁንም ያልተኙ መሆናቸው በምንም መልኩ ሊዘነጋ አይገባም፡፡
ወጣቶችን የጥፋት ሐሳብ፣ ክብሪትና ነዳጅ እያስታጠቁ ለአገሪቱ ቁልፍ የኢኮኖሚ አስተዋጽኦ ያላቸውን ፋብሪካዎች፣ የአበባ እርሻዎችና ሌሎች ተቋማት በማጋየት ከፍተኛ ውድመት ማስከተላቸውንም በተመሳሳይ፡፡ የኦነግና የግንቦት ሰባት መሪዎች ከግብፅ መንግሥት ተቋማት ጋር እጅና ጓንት በመሆን ባቀነባበሩት የጥፋት እንቅስቃሴ በርካታ አገራዊና የውጭ ባለሀብቶችና ሠራተኞቻቸውን ለአደጋ ያጋለጠ የታሰበበት ከፍተኛ ውድመት መፈጸሙም አይካድም፡፡ እኒህና መሰል የጥፋት ዘመቻዎች በተጠናከረ እና በተጠና አግባብ የተፈጸመና በመፈጸም ሂደት ላይ ባለበት ሁኔታ በነባሩ የህግ አግባብ ጉዳዩን መቆጣጠር ይቻላል ማለት ዘበት ስለሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሰብአዊ መብት ጥሰትን ሰበብ እያደረጉ ማንኳሰስና ጥርጣሬ ላይ እንዲወድቅ መፍቀድ ከጥፋት ሃይሎቹ ሴራ የማይተናነስ ትልቅ ጥፋት ይሆናል።
በአንድ ሃገር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ከሚያሳደሩ ጉዳዮች መካከል አለመረጋጋት አንዱ ነው፡፡ በምጣኔ ሃብታዊ ተመራማሪዎች ጥናት መሰረት አንድ ዓመትና አንድ ዓመት ከመንፈቅ የቆዩ ግጭቶች 10 እስከ 15 በመቶ የአገሪቱን በኢኮኖሚ የመመንደግ አቅም ያቀጭጫሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ግጭቱ ካቆመ በኋላ አገሪቱን ወደነበረችበት ለመመለስ 10 እስከ 15 ዓመታት እንደሚፈጅባትም እነዚሁ ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ በመሆኑም ነገሮች ችላ በሚባሉበት ጊዜ፣ የሰዎች ትኩረት ከኢንቨስትመንትና ከምርት ይልቅ ወደ ሌላ አቅጣጫ ያዘነብላል፡፡
መንግሥታት ሙሉ ጊዜያቸውን የፖለቲካ ትኩሳቶችን ለማርገብ በሚያውሉበት ጊዜ በልማት ጉዳዮች ላይ የሚደርሰውን ጫናመመልከት በሃገራችን ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አስቀድሞ የነበርንበትን ማስታወስ በቂ ነው።
ጦርነት በበዛባቸው የአፍሪካ አገሮች ከጦርነቱ በኋላ ወደነበሩበት ለመመለስ 15 ዓመታት ፈጅቶባቸዋል፡፡ ሶሪያን ያየን እንደሆነ አሁን ከሚታየው አኳያ፣ አገሪቱ 30 ወይም 40 ዓመታት በኋላም ልታገግም እንደማትችል ጠበብቶቹ እየተነበዩ ነው፡፡ መፍትሔ የሚሆነው መንግሥት የትኛውም አካል ላለበት ችግርና ፖለቲካዊ አለመግባባቶችን በመወያየትና በመነጋገር መፍታት ካልተቻለ፣ የትኛውም ያለመግባባትና ቅሬታ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ካልመጣና ከላይ በተመለከቱት አግባቦች ሊፈታ የሚሞከር ከሆነ ሃገር አደጋ ላይ መውደቋ አይቀሬ ይሆናል፡፡ ... 2000 በፊት በነበሩ አሥር የአፍሪካ አገሮች ላይ ጥናት  ያደረጉ እና ... 1980ዎቹ ውስጥ በየዓመቱ ይከሰቱ የነበሩትን ግጭቶችን የሚያስታውሱት ጠበብቶች  በግርድፉ 20 ወይም ከዚያም በላይ ግጭቶች ሲከሰቱ መቆየታቸውን እና፤ በእነዚህ አገሮች የነበረው የኢኮኖሚ ዕድገትም ከዜሮ በታች ወይም ከአንድ እስከ ሁለት በመቶ ባለው ዝቅተኛ መጠን ሲያድግ መቆየቱን ይገልጻሉ፡፡  
ስለሆነም ከመሬት ተነስቶ ወደነበርንበት መመለስ የምንችልበትን ጥርጊያ ባመላከተን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ሌላ ታርጋ ከመለጠፍ የኮማንድ ፖስቱ ተባባሪ ሆነን ስለሰላማችን ልንተጋና ባለቤቱም እኛው ልንሆን ይገባል።
በእርግጥ የአዋጁን መንፈስ ለማሳት የሚሹት ሃይሎች ጥቂት ስለመሆናቸው በራሱ ከሰሞኑ በነበረው የህዝቡ ትብብርና የጥፋት ሃይሎችን የማጋላጥ ተሳትፎ የተረጋገጠ ሆኗል።   የፌዴራል ፖሊስ ከኦነግ ጋር ግንኙነት በመፍጠርና አመራር በመቀበል የጥፋት ተግባር ላይ ተሰማርተዋል በሚል የጠረጠራቸውን 17 ወጣቶች በቁጥጥር ሥር አውሎ ክስ ለመመስረት የቻለው በከፍታኛ የህዝብ ትብብር ነው፡፡
እነዚህ ወጣቶች ከኦነግ አመራሮችና የሽብር ቡድን አባላት ጋር የስልክ ግንኙነት በማድረግ በአገር ውስጥ አባላትን ሲመለምሉ እንደነበር፣ ዓላማቸውም የኢትዮጵያን መንግሥት በኃይል የመለወጥ የፖለቲካ ዓላማ እንደነበራቸው በክሱ ገልጿል፡፡ እነዚህ ወጣቶች መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ፣ በቢሾፍቱ፣ በጅግጅጋና በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች በማድረግ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር የክስ መዝገቡ ያስረዳልና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ፋይዳ በዚህም ልብ ይሏል፡፡
በምዕራብ ሸዋ ዞን የዕርዳታ እህል የጫኑ ተሽከርካሪዎችን ያቃጠሉ፣ በመንገድ ሥራ ላይ የነበሩ ማሽነሪዎች፣ ሆቴሎችና የአስተዳደር ጽሕፈት ቤቶች ላይ ጉዳት ያደረሱ ተጠርጣሪዎች የተያዙት በነዋሪዎች ጥቆማ መሆኑንም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ስለሚያንኳስሱት ጥቂት ግለሰቦች ልብ ማለት እና ተሳትፎን ማጠናከር ያሻል፡፡
በአርሲ ነገሌ የውኃ ፕሮጀክቶች ላይ ጉዳት ያደረሱና የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችን ያቃጠሉ በርከት ያሉ ወጣቶች በቁጥጥር ሥር የዋሉትም በተመሳሳይ መንገድ ነው፡፡
የግብፅ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተለያዩ ጊዜያት ከቀጣናቸው በመውጣት አለመረጋጋት የሚታይባቸውን የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በድብቅ በመጎብኘት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ታይተዋል፡፡ ከእነዚህም አገሮች መካከል ኤርትራ አንዷ ስትሆን በዚህች አገር የግብፅ ፍላጐት እንደተሟላ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የኤርትራ መንግሥት የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችን በማስጠለል ሲተባበር፣ ግብፅ አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ እያደረገች መሆኑ በሚታወቅበት አግባብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ብቻ ሳይሆን የተጠናከረ የህዝብ ተሳትፎ እና የጸጥታ ስራ ማከናወን ተገቢ ይሆናል፡፡
ይህንኑ ተመሳሳይ እንቅስቃሴ በሶማሌላንድና በደቡብ ሱዳን ለመድገም እንቅስቃሴ የተደረገ ቢሆንም፣ የሶማሌላንድ መንግሥት አለመቀበሉን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በሶማሌላንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መድረክ ዋና ዳይሬክተር ሞሐመድ አህመድ ባርዋኒ፣ የግብፅ መንግሥት ኃላፊዎች ከጥቂት ወራት በፊት በሶማሌላንድ ያደረጉት ጉብኝት ዓላማው፣ በአገሪቱ ጦራቸውን ለማስፈር የሚያስችላቸውን ስምምነት ለመፍጠር ቢሆንም አልተሳካላቸውም የሚል ምላሻቸውን ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን መስጠታቸውንም ማስታወስ ያስፈልጋል፡፡
ዓላማቸውን እውን ለማድረግ ከየመን ጋር የተያያዙ ምክንያቶችን ያቅርቡ እንጂ፣ ጉዳያቸው ኢትዮጵያ ነች የሚል እምነት እንዳላቸው ባርዋኒ ለነዚሁ መገናኛ ብዙሃን ነግረዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የደቡብ ሱዳንን ችግር እንዲፈታ ኃላፊነት የሰጠው ለምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት (IGAD) ቢሆንም፣ ግብፅ በዚህ አካባቢ ጦሯን ለማሰማራት ከፍተኛ ፍላጐት እንዳላት መግለጿንም ስለሰላማችን ተሳትፎ ማጤን ያስፈልጋል፡፡
የግብፅ መንግሥት ሁለት እጆች እንዳሉት በአፍሪካ በተለይም በቀጠናችን ላይ ምርምር ያደረጉ የፖለቲካ ልሂቃን የሚገልፁ ሲሆን፤ አንደኛው ውስጥ ለውስጥ የሚንቀሳቀስበት ከመንግሥት ጋር ንክኪ የሌላቸው ተደርገው የሚቆጠሩ ተቋማት፣ ነገር ግን ሙሉ የበጀት ድጋፍ በግብፅ መንግሥት የሚደረግላቸው ሲሆኑ፤ ሁለተኛው ራሱ የግብፅ መንግሥት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚፈጽመው ሴራ ነው (የዚህ ዝርዝሩ ብዙ በመሆኑ ሌላ ግዜ ተመልሰን ለማየት እንስማማና እንለፈው)፡፡
ባጠቃላይ፣ ባለፉት ዓመታት ሃገሪቱ ያስመዘገበችውን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማደናቀፍ፣ የወጣቶችን ሕጋዊ የተጠቃሚነት ጥያቄ ጠልፈው መሠረተ ልማቶችን ወደ ማውደም የተሸጋገሩ ኃይሎች ተልዕኮ፣ ወደ ድህነት የተመለሰችና የፈራረሰች አገር መፍጠር መሆኑን በመገንዘብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ግቡን እንዲመታ ሁሉም ሊረባረብና የድርሻውን ሊወጣ ይገባል።


No comments:

Post a Comment