ኢብሳ
ነመራ
በ1985
ዓ/ም ኦሮሚያ ራሷን በራሷ ማስተዳደር ስትጀምር የክልሉ ቢሮዎች ቀጠረው በየዞኑ ከመደቧቸው ሰራተኞቸ አንዱ ነበርኩ። እኔ ወደ ባሌ
ነበር የሄደኩት፤ ወደባሌ ጎባ/ሮቤ። ያኔ ከአዲስ አበባ ወደ ባሌ ሮቤ ወይም ከሮቤ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዝ መንገደኛ በአብዛኛው
መንገድ ላይ ለማደር ይገደድ ነበር። ወደ ሮቤ ሲኬድ ዶዶላ ወይ አዳባ ላይ ማደር የተለመደ ነው። ጠጋ ተብሎ ዲንሾ ላይ አይታደርም።
ዲንሾ የኤሌትሪከ ሃይል - መብራት ተጠቃሚ ስላልሆነች፣ የገብስ ቆሎዋና ጣፋጭ የበግ ጥብሷን እንጂ የምሽት ጨለማዋን ማንም አይፈልግም።
ከሮቤ ወደ ወደ አዲስ አበባ ለሚመለሱ ደግሞ አዳማ ላይ ማደር የተለመደ ነው። ትንሽ ዘግየት በሎ የተነሱ ሻሸመኔ ላይ ያድራሉ።
ልብ
በሉ ሮቤ ከአዲስ አበባ 430 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የምትገኘው። የባሌ ዞን በሰብል አምራችነቱ የሚታወቅ አካባቢ በመሆኑ ከፍተኛ
የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ይካሄደበታል። የሁን እንጂ ከአስራ አምስት ዓመት በፊት ሮቤ ውስጥ ለተሽከረካሪ የሚሆን ነዳጅ ማግኘት ብርቅ
ነው። በመላ ሃገሪቱ ነዳጅ እንደ ልብ ሲቀዳ ባሌ ላይ ግን ልክ በደርግ ግዜ እንደነበረው በዞኑ የንግድ መምሪያ አማካኘነት በኮታ
ነበር የሚታደለው። የዚህ ሁሉ ችግር ምንጭ መንገድ ነበር። ከአሰላ እና ከሻሸመኔ ጀምሮ ያለው መንገድ ኮሮኮንች በመሆኑ በተለይ
ተራራማ መልከዓምድራዊ አቀማመጡ ለተሽከርካሪ አመቺ ባለመሆኑ የተፈጠረ ችግር ነው። ነዳጅ ጫኝ መኪኖች አዳባን አልፈው የዲንሾን
አቀበት ሲጀምሩ ወገባቸውን ይይዛቸዋል።
የሮቤ
ከተማ ከመቶ አመት በፊት ወደ ሃገር ውስጥ የገባው የማናቤላ ስልክ ተጠቃሚ ነበረች። ከፍተኛ የእህል ምርት ገበያ ማዕከል የሆነችው
የሮቤ ከተማ ከስልክ ግንኙነት ውጭ ነበረች። ስልክ ለመደወል የሚፈልገ የነበረው አማራጭ ወደ ቴሌ መደወያ ማዕከል መሄድ አለበለዚያ
ማናቤላ የተጠመደበትን ስልክ አሽከርክሮ በቴሌ ኦፕሬተር አገናኝነት ወደሚፈልገው ቦታ መደወል ነበር፤ የሮቤ የስልክ አገልግሎት ይሄው
ነበር።
አሁን
ይህ ሁሉ ተቀይሯል። ከአዲስ አበባ የተነሳ ሰው ዘጠኝ ሰአት ሳይሆን ሮቤ ይደረሳል። ከአዲስ አበባ እሰከ ሮቤ አልፎም እስከ ጎባ
ያለው መንገድ አስፓልት በመሆኑ። ነዳጅ የጫኑ መኪናዎች የዲንሾን አቀበት አቅቷቸው የሚቆሙበት ሁኔታ አሁን የለም። የኮሮኮንቹን አቀበት ሽሽት የጫኑትን
ነዳጅ ሻሻመኔ ላይ አራግፈው የሚመለሱ የነዳጅ ቦቴዎች አሁን የሉም። አሁን ሮቤ የሞባይልና የዲጅታል ስልክ ተጠቃሚ ነች።
ይህ የመሰረተ ልማት መሻሻል ባሌ ሮቤን ብቻ የሚመለከት እውነታ አይደለም። አካባቢውን
በቅርበት አውቀው ስለነበረ ለማሳያነት ጠቀስኩት እንጂ በሁሉም የሃሪቱ አቅጣጫዎች ያለው እውነታ ይህን የሚመስል ነበር። ባለፉ ሁለት
አስርት ዓመታት በሁሉም የሃገሪቱ አቅጣጫዎች ያሉት መንገዶች ደረጃቸው ተሻሽሏል። በርካታ አዳዲስ መንገዶችም ተሰረተዋል። ከሁለት
አስርት ዓመታት በፊት 19 ሺህ ኪሎ ሜትር የነበረው የሃገሪቱ አጠቃላይ መንገድ በስድስት እጥፍ አድጎ አሁን 110 ሺህ 414 ኪሎ
ሜትር ደርሷል።
በአሁኑ
ግዜ ሁሉም የሃገሪቱ ከተሞች የስልክና የኤሌትሪክ ሃይል ተጠቃሚዎች ናቸው። ሁሉም የሃገሪቱ ከተሞች የውስጥ ለውስጥ የኮብል ድንጋይ
መንገድ ግንባታ ተካሂዶባቸዋል። በየአካባቢው አይነገብ የሆኑት ከተሞች እያንዳንዳቸው ቢያንስ አስር ሺህ ተማሪዎችን የሚያስተናግዱ ዩኒቨርሲቲዎች አሏቸው። አሁን በሁሉም የሃገሪቱ
ክልሎች በሚገኙ 33 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ግማሽ ሚሊየን ያህል ተማሪዎች ትምህርታቸውን ይከታተላሉ። ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት
የዩኒቨርሲቲዎቹ ቁጥር 2፣ ተማሪዎቹ ደግሞ ከአስር ሺህ የሚበልጡ አልነበሩም። አብዛኞቹ የሃገሪቱ የወረዳ ከተሞች የቴክኒክና ሞያ
ማሰልጠኛ ኮሌጆች አሏቸው። ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት 16 ብቻ የነበሩት የቴክኒክና ሞያ ተቋማት አሁን በመቶ እጥፍ ገደማ አድገው
1 ሺህ አራት መቶ ገደማ ደርሰዋል።
አሁን
የትምህርት እድል ለከተሜዎች የተሰጠ ልዩ ጸጋ አይደለም። የአርሶ አደሩ ህጻናት ልጆች በ2 ተኩል ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ የአንደኛ
ደረጃ ትምህርት ቤት ተገንብቶላቸዋል። በመጪው ትውልድ ሁሉም ዜጋ
ቢያንስ ማንበብና መጻፍ የሚችል ስለመሆኑ ከወዲሁ መናገር ይቻላል። በዚህም ከሁለት አስርት ዓመት በፊት 2 ሚሊየን ገደማ የነበረውን
የተማሪዎች ቁጥር አሁን 27 ሚሊየን ማድረስ ተችሏል።
አሁን
ሁሉም ኢትዮጵያዊ በቅርብት ርቀት መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ማግኘት ይችላል። ከሁለት አስርተ ዓመታት በፊት 150 የነበሩት የሃገሪቱ
የጤና ጣቢያዎች አሁን 3 ሺህ 5 መቶ ደርሰዋል። ከሁለት አስርተ ዓመታት በፊት 72 ብቻ የነበሩት የሃገሪቱ ሆስፒታሎች አሁን በአራት
እጥፍ አድጎ 310 ደርሰዋል። ከዚህ በተጨማሪ 40 ሺህ ያህል የጤና
ኤክስቴንሽን ባለሞያዎች የአርሶ አደሩ መንደር ድረስ በመዝለቅ የጤና አገልግሎት ይሰጣሉ፤ በንጽህና ጉደለት የሚመጡና ቀደም ሲል
በተለይ ለህጻናት ሞት ምክንያት ይሆኑ የነበሩ በሽታዎችን በቀላሉ መከላከል እንዲቻል ትምህርት ይሰጣሉ።
በመላው
ሃገሪቱ የማምረቻ ፋብሪካዎችና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ተሰፋፍተዋል። በቅርቡ በኦሮሚያ ውሰጥ በተቀሰቀሰው ሁከት በእሳት ከወደሙት
ከ60 በላይ ፋብሪካዎች ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የተገነቡ ናቸው። ልብ በሉ ሁከት የተቀሰቀሰው
ከ350 የኦሮሚያ ወረዳዎች በበ50ዎቹ ብቻ ነው። ይህ የማምረቻ ኢንደስትሪው ምን ያህል እንዳደገ ያመለከታል።
ከላይ
ለማሳያነት ያህል ጨልፌ ያነሳኋቸው የሃገሪቱ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶች የሃገሪቱን የድህነት ደረጃ መቀነስ አስችለዋል። በሚሊየን
ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ እድል ፈጥረዋል።
እንግዲህ
ይህ እድገት እንደመና ከሰማይ የወረደ አይደለም። በቅድሚያ በሃገሪቱ የተረጋገጠው ሰላም ውጤት ነው። በሃገሪቱ ሰላም መረጋገጥ የቻለው
ደግሞ በኢፌዴሪ ህገመንግስት ብዝሃነትን ማስተናገድ በመቻሉ፣ እንዲሁም ገና የሚቀረው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የዴሞክራሲያዊ ስርአት
መሰረት በመጣሉ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የሃገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ልማት ፖሊሲ ተነድፎ ተግባራዊ በመደረጉ
ነው። በሃገሪቱ ከሰፈነው ሰላምና ዴሞክራሲ፣ ትክክለኛ የልማት ፖሊሲ መቀረጽና ተግባራዊ መደረግ በተጨማሪ በህዝብ አገልጋይነት መነፈስ
የሚሰራ አመራር በመኖሩ ነው።
ይህን
እንጂ በተለይ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ባሀገሪቱ ከተመዘገበውና ህዝብን ተጠቃሚ ካደረገ ልማት ጀርባ የነበረው የህዝብ አገልጋይነት
መንፈስ እየተሸረሸረ መጥቷል። ባለፉት ዓመታት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አመራሮች ውስጥ የመንግስት ስልጣንን ለራስ መገልገያነት
የማዋል ዝንባሌ አየገነነ መጥቷል። ይህ ጥገኝነትና ኪራይ ሰብሳቢነት የፈጠረው በመንግስት ስልጣን ራስን የማገልገል ዝንባሌ የህግ
የበላይነትን በመሸርሸር መልካም አስተዳደር በጉልህ እንዲጓደል አድርጓል። ይህ ሁኔታ ዜጎች መብትና ነጻነታቸው እንዲጣስ፣ ፍትሃዊ
የሃብት ተጠቃሚነት እንዲዛባ አድርጓል። ብዙዎች በንብረታቸው ላይ የባለቤትነት መብታቸውን ተቀምተዋል። ለልማት በሚል ሽፋን አርሶ
አደሮች ዘላቂ ህየወታቸውን ያገናዘበ ካሳ ሳያገኙ መሬታቸውን ተነጥቀዋል። የመንግስት ባጀት ለልማት ከመዋወል ይልቅ ተመዝብሯል።
ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ከታሰበላቸው ባጀት ከእጥፍ በላይ ፈጅተዋል። የመጠናቀቂያ ግዜያቸውም፣ የአንዳንዶቹ መድረሻቸው ተጠናቀው
አገልግሎት መስጠት ሳይሆን መገንባት እስኪመስል ተጓቷል። ይህ ሁኔታ ከፕሮጀክቶቹ ሊገኝ ይችል የነበረውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲሁም
ሊፈጠር ይችል የነበረን ሰፊ የስራ እድል አስቀርቷል። በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ጭምር ያለ የአመራር ብልሹነት በስራ ፈጠራ ተጠቃሚ
መሆን ይችሉ የነበሩ የበርካታ ዜጎችን እድል ዘግቷል።
በሌላ
በኩል ጥቂት ሰዎች ከየት እንዳመጡት ሳይታወቅ በአጭር ግዜ ውስጥ ሚሊየነር የሆኑበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ምን እንደሚሰሩ እንኳን የማይታወቁ
ሰዎች በሚሊየን የሚቆጠር ሃብት ሲያንቀሳቅሱ፣ ትላልቅ ህንጻዎቸ ሲገነቡ፣ በርካታ የኮንዶሚኒየም የንግድና የመኖሪያ ቤቶች እየገዙ
ሲያከራዪ ታይተዋል።
ይህ
የአመራር ብልሹነት ውጤት ነው፤ በህዝብ ውክልና ስልጣን የተረከበው ኢህአዴግ በየደረጃው የሾማቸው አመራሮችና አብረዋቸው የሚሰሩ ባለሞያዎች ዘንድ የተፈጠረ የአመራር ብልሹነት። ከአመራር
ብልሹነት በተጨማሪ የአመራር ብቃት ችግርም በሰፋት ታይቷል። ሰዎች ህግና ፖሊሲን በማስፈጸም የሞያ ብቃትና ክህሎታቸው ሳይሆን በፖለቲካ
ታማኝነታቸውና በፓርቲ ውስጥ ባላቸው ሃላፊነት ልክ የመንግስት አስፈጻሚነት ስልጣን የሚይዙበት ሁኔታ መኖሩ ለአስፈጻሚው ብቃት ማነስ
ምክንያት የሆበት ሁኔታ ታይቷል። ይህም የመረረ የህዝብ ቅሬታ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።
ይህ
የመረረ ቅሬታ እስከ አፍ ገደፉ ስለሞላ ትንሽ ሰበብ ሲያገኝ ገንፍሎ እየወጣ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች፣ በተለይ ኦሮሚያና አማራ
ክልሎች ሁከት የተለመደ ክስተት እንዲሆን አድርጓል። የህዝብ ቅሬታ የፈጠረው በየአጋጣሚው እየገነፈለ ወደሃይል ተቃውሞነት መቀየር
የጀመረ ሁኔታ፣ በውጭ ሃገራት ለሚኖሩ ህገመንግስታዊ ስርአቱን በሃይል መናድ ለሚፈልጉ ቡድኖች እጃቸውን ማስረጊያ ቀዳዳ ከፍቶላቸዋል።
ህገመንግስታዊ ስርአቱን የመናድ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች እጃቸውን ማስረግ መቻላቸው ደግሞ ግብጽን ለመሳሰሉ የሃገሪቱ ስትራቴጂካዊ
ጠላቶች እኩይ ዓላማቸውን ማስረግ የሚያስችል መንገድ ከፍቷል። ይህ ሁኔታ ህገመንግስታዊ ስርአቱን አደጋ ላይ የጣለ አውዳሚ ሁከት
እንዲፈጠር አድርጓል።
ገዢው
ፓርቲ ኢህአዴግና አባል ድርጅቶቹ በስራ አስፈጻሚ፣ በማእከላዊ ኮሚቴና በፓርቲ ምክር ቤት ደረጃ የሃገሪቱ ወቅታዊ ችግር ላይ መክረው ፓርቲው ውስጥ በተፈጠረ የአመራር ብልሽት የሃገሪቱ ህልውና አደጋ ላይ መውደቁን
ተስማምተውበታል። የመፍትሄ ሃሳብም አስቀምጧል። እንደመፍትሄ የተቀመጠው የፓርቲውና የመንግስት መዋቅር ውስጥ ተሃድሶ ማካሄድ ነው፤
አመራሩን በጥልቀት የማደስና መዋቅር የማስተካከል እርምጃ።
ይህ
በጥልቀት መታደስ የሚል ሃሳብ በዋናነት በጥገኝነት የተለከፉና የመንግስት ስልጣንን ህዝብን ለማገልገል ሳይሆን ለራሳቸው ጥቅምና
ክብር መገልገያ ያደረጉ አመራሮችን ገምግሞ ማስወገድን ይመለከታል። በፓርቲው፣ በመንግስትና በአጠቃላይ በዜጎች ውስጥ የህዝብ አገልጋይነት
መንፈስ ገዢ አመለካከት እንዲሆን ማድረግም የዚሁ በጥልቀት የመታደስ አካል ነው። ከዚሁ ጎን ለጎን የመንግስት አስፈፃሚዎች አሰያየም
በፓርቲ ውስጥ ባላቸው ሃላፊነት ልክ ሳይሆን በብቃትና በህዝብ አገልጋይነት ፍላጎት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ይደረጋል። የመንግስት
አስፈጻሚ ሃላፊዎች ከገዢው ፓርቲ አባል ውጭ ብቃትና የህዝብ አገልጋይነት ፍላጎትን መሰረት በማድረግ እነደሚሾሙ ከፓርቲውና ከመንግስት
የተገኙ መረጃዎች አመልክተዋል።
እንግዲህ
በጥልቀት የመታደስ ጉዳይ በገዢው ፓርቲ አቋም ከተያዘበት ሰነባብቷል። ይህ በጥልቀት የመታደስ እርምጃ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልላዊ
መንግስት ውስጥና በክለሉ ገዢ ፓርቲ ኦህዴድ ውስጥ በግልጽ ታይቷል። ይህ ይበል የሚያሰኝ ነው። ሌሎቹ የኢህአዴግ ፓርቲዎችና የሚወክሏቸው
ክልላዊ መንግስታት፣ እንዲሁም የፌደራል መንግስትም ይህንኑ በጥልቀት የመታደስ ሂደት ጅምር ያሳዩናል ብለን እንጠብቃለን። በጥልቀት
የመታደሱ መድረሻ የህዝብን ቅሬታ በመግፈፍ፣ ተጠቃሚ ይሚሆኑበትን ሁኔታ መፍጠር ነው። የተሸረሸረ የህዝብ አገልጋይነት መነፈስ ህገመንግስታዊ
ስርአቱን ለአደጋ እንደሚያጋልጥም መታወቅ አለበት።
No comments:
Post a Comment