ኢብሳ ነመራ
. . . ግድቡን ለመስራት ብድርና እርዳታ እንዳናገኝ የተለያዩ ኃይሎች
ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ ምክንያት የፕሮጀክቱን ወጪ ለመሸፈን የሚተባበረን ሃገር ወይም ተቋም ማግኘት አልቻልንም። ስለሆነም ወጪውን
ብቻችንን ከመሸፈን አልፈን በራሳችን ቁጠባ ለመሸፈን የምንገደድበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
የፕሮጀክቱ የገንዘብ ወጪ ከ3 ነጥብ 3 ቢሊየን ዩሮ በላይ ወይም ከ78
ቢሊየን ብር በላይ በመሆኑና ከዚህ ፕሮጀክትም ባሻገር ሌሎች በራሳችን ወጭ ልንሸፍናቸው የሚገቡን በርካታ ፕሮጀክቶች በመኖራቸው፣
ወጪውን መሸፈን እጅጉን እንደሚከብደን ጥርጥር የለውም። ሸክሙን ለማቃለል፣ ያደረግነው ጥረት ስላልተሳካና ያለፉት ሃምሳ አመታት
ታሪካችን እንደማይሳካ ያረጋገጡልን በመሆኑ የሚኖረን አማራጭ አንድም ግድቡን አለመስራት ነው፣ አለበለዚያ እንደምንም በራሳችን መሸፈን
ነው።
ከእነዚህ ከባድ ሁለት አማራጮች መሃከል፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ምርጫ የትኛው
እንደሚሆን ግልፅ ነው። በተለመደው ወኔው ‘ምንም ያህል ደሃ ብንሆንም ድህነታችንን ለማስወገድ ማንኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል
ዝግጁ ነን። ስለዚህ ፕሮጀክቱ መሰራት አለበት’ እንደሚል ለአፍታም ያህል አልጠራጠርም።
ይህ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ በተጣለበት ዕለት መጋቢት 24፣ 2003 ዓ/ም ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ አድርገውት
ከነበረው ንግግር የተወሰደ ነው።
እንደምናስታውሰው
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ መጣሉን ተከትሎ ኤርትራ ወረራ ፈፅማብን በነበረበት ወቅት የታየው አይነት ታላቅ
ሃገራዊ መግባባት ተፈጥሯል። ሁሉም የኢትዮጵያየ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች፣ በአንድ አፍ “ግድቡን እንገነባዋለን!” ብለው ተነስተዋል፤ በፍጹም
ልባዊ ሰሜት። የኢትዮጵያ ህዝብ ይህን ስሜቱን አደባባይ በመውጣት ገልጿል። ግንቦት 2003 ዓ/ም በመላ ሃገሪቱ ከተሞች የተካሄዱት
ትዕይንት ህዝቦች ኢትዮጵያውያን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለመገንባት ያላቸውን ፍላጎትና ቁርጠኝነት የገለጹበት ነበር።
ይህን
ተከትሎ የህዳሴ ግድብ ከህጻን እሰከአረጋውያን ቀልብ የገዛ አጀንዳ ሆነ። የኢተዮጵያውያንን በአባይ ውሃ የመጠቀም መብት ቆልፎ የነበረውን
ድህነት በመጠርመስ በራሳችን አቅም ግድቡን በመስራት የአባይን ውሃ ወደመጠቀም የሚሻገሩበት ገዜ ላይ መድረሳቸው የዘመናት ቁጭታቸውን
የሚሽር በመሆኑ ነው የሁሉንም ዜጎች ቀልብ የገዛው። ይህ ስሜት አሁንም ግለቱ አልቀነሰም። በተለይ በየዓመቱ የግድቡ ግንባታ የመሰረት
ድንጋይ የተጣለበት ዕለት ሲዘከር እየታደሰ እዚህ ደርሷል።
በዚህ
ስሜት ውስጥ የነበሩት ኢትዮጵያውያን በመሉ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ማድረግ ጀመሩ። በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገራት በተለይ ለህዳሴው
ግድብ ግንባታ የተዘጋጀውን የመንግስት ቦንድ በመግዛት፣ በአርሶ አደሩ በኩል ደግሞ ግድቡን ለዘለቄታው በደለል ከመሞላት የሚከላከል
እርከን በአባይ ተፋሰስ ተዳፋት መሬት ላይ በመስራት የአካባቢ እንክብካቤ በማድረግ ወዘተ።
የግድቡ
ህዝባዊ
ተሳትፎ
ማስተባበሪያ
ብሄራዊ
ምክር
ቤት ሰሞኑን ባካሄደው
8ኛ
መደበኛ
ጉባኤ
ባለፉት
አምስት
አመታት
ከ28
ቢሊየን
ብር
በላይ
ገንዘብ
ከመላ
በመላ ሃገሪቱ
ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መሰብሰቡን
አሳውቋል።
ይህም
ቃል
ከተገባው
49 ነጥብ
5 ቢሊየን
ብር
ከግማሽ
በላይ
ነው።
በ2008
በጀት
አመት
12 ነጥብ
4 ቢሊየን
ብር
ቃል
ተገብቶ፣
8 ነጥብ
6 ቢሊየን ብር
ተሰብስቧል።
ይህም ካለፉ አምስት ዓመታት ሁሉ የላቀ ነው። በውጭ ሃገራት
ከሚኖሩ የኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውወያን ማህበረሰብም
እስካሁን
2 ነጥብ
6 ቢሊየን
ብር
ተሰብስቧል።
አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ይህ እስከ ግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያመለክታል። ይህ ለአንድ ዓላማ ገንዘብ
የማሰባሰብ ተግባር በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው።
የታላቁ
የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ግዜ ጀምሮ ህዝቡ የግንባታውን ሂደት እንደህጻን ልጅ እድገት በጉጉት
እየተከታተለ 2006 ዓ/ም ላይ የግንባታው ሂደት አንድ እርከን ላይ ደረሰ፤ ይህም የአባይ ወንዝ ውሃ ለዘመናት ሲፈስበት የነበረበትን
ቦይ ለአጭር ግዜ ለግድቡ መገንቢያነት ለቆ በአዲስ ቦይ መፍሰስ መጀመሩ ነው። ይህ ግዚያዊ የውሃ ፍሰት አቅጣጫ መቀየር የአባይን
ውሃ አንድም ጠብታ የማያስቀርና በማንኛውም የግድብ ግንባታ ሂደት የሚከናወን ቢሆንም፣ በግብጾች ዘንድ ግን አብሯቸው የኖረውን ኢትዮጵያ
በአባይ ውሃ እንዳትጠቀም የማድረግ የዘመናት ፍላጎት ቀስቅሶ ፉከራዎች ቢጤ ሰምተናል።
በወቅቱ
ግብጽን ሲመሩ የነበሩት ፕሬዝዳንት መሃመድ ሙርሲ ካቢኔያቸውን ሰብስበው ኢትዮጵያ ላይ ቀጥታ የሃይል ጥቃት መሰንዘር ባይቻል እንኳን
ማስፈራራት እንዳለበቸው ምክክረ አደረጉ። ይህ በሚስጥር የተካሄደ ምክር በስህተት በቀጥታ በቴሌቪዥን ተላልፎ እኛ ኢትዮጵያውያን
ጆሮ ደረሰ። ታዲያ በዚህ ኢትዮጵያን በአየር መደብደብ ባንችል እንኳን
እናስቦካ የሚል ሃሳብ ያስተናገደ ስብሰባ ላይ በተለይ በዳዉድ ኢብሳ የሚመራውን ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ብሎ የሚጠራ
ቡድን በመጠቀም በእጅ አዙር ኢትዮጵያን የማተራመስና የማዳከም እርምጃ የመውሰድ ውጥንም ጉዳይ ተነስቷል።
በኢትዮጵያ
በኩል ግን ለግብጽ ካቢኔና ለሚዲያዎቻቸው ድንፋታ ብዙም ዋጋ ባለመስጠት፣ በአንድ ወገን የግድቡን ግንባታ በታቀደለት ፍጥነት በማስቀጠል
በሌላ በኩል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአባይ ውሃ ኤሌትሪክ ለማመንጨት ከመዋል አልፎ የውሃውን ፍሰት የማያግድ መሆኑን ለግብጽ
መንግስትና ህዝብ የማረጋገጡን የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወኗን ቀጠለች። በዚህ የዲፕሎማሲ ጥረት በመጨረሻም በሶስቱ የታችኞቹ ተፋሰስ
ሃገራት (ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ) መሃከል የመርህ ስምምነት ላይ ማድረስ ተቻለ። ስምምነቱ በሶስቱ ሃገራት መሪዎች ነበር የተፈረመው።
የመርህ ስምምነቱ ሰነድ በመግቢያው ላይ፤ የግብፅ አረብ ሪፐብሊክ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራሊያዊ ዴሞክራሲያ ሪፐብሊክ እና የሱዳን ሪፐብሊክ እየጨመረ የሚገኘውን ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብቶቻቸውን የመጠቀም ፍላጎትን መሰረት በማድረግ የናይል ወንዝ የግብፅ፣ የኢትዮጵያ እና የሱዳን ህዝቦች ህይወት እና ልማት ምንጭ የሆነ ሀብት መሆኑን በመገንዘብ ሶስቱ ሀገራት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ለተዘጋጁት ቀጣይ መርህዎች ይሰራሉ። ይላል።
ይህ የስምምነቱ መግቢያ ላይ የሰፈረ ግብፅ የናይል ወንዝ ውሃ ለግብፃውያን የህይወት ጉዳይ ለሌሎቹ የላይኛው ተፋፈስ ሃገራት በተለይ ለኢትዮጵያውያን የማያስፈልጋቸውና የመጠቀም መብትም
ሊኖራቸው የማይገባቸው አድርጋ የያዘችውን አቋም በመቀየር ናይል ለኢትዮጵያውያንም እንደግብጽና ሱዳን ህዝብ
ሁሉ የልማታቸው መሰረት ለመሆኑ በእኩል በይፋ እውቅና የሰጠ ነው።
የመርህ
ስምምነቱ አስር አንቀፆች ያሉት ሲሆን ለዚህ ጽሁፍ ዓላማ የተወሰኑትን እንመልከት፤
አንቀጽ 1. የትብብር መርህ፤
በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ ትብብር፣ የጋራ ፍላጎት፣ መልካም አሳቢነት፣ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ እና የአለም አቀፋዊ ህጎች መርህዎችን የተከተለ፤
የታችኛውም ሆነ የላይኛው የተፋሰሱ ሀገራት ውሃ እንደሚያስፈልጋቸው ተረድቶ በትብብር መስራት፣
አንቀጽ 2. የአካባቢያዊ ትስስርና ዘላቂ ልማት መርህ
የህዳሴው ግድብ ዓላማ ሀይል ማመንጨት፣ ለምጣኔ ሀብት እደገት አስተዋፅኦ ማድረግ፣ አከባቢያዊ ትብብርን መፍጠር፣ አስተማማኝ የሆነ የታዳሽ ሀይል በማመንጨት አከባቢያዊ ጥምረትን ማምጣት ነው።
3. ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርህ
ሶስቱም ሀገራት በአባይ ወንዝ አጠቃቀማቸው ጉልህ ጉዳት ላለማድረስ ተገቢውን አካሄድ ይከተላሉ።
ሆኖም ከሶስቱ አገራት መካከል በአንዱ ላይ ጉዳት ቢደርስ ያለምንም ስምምነት ጉዳቱን ያደረሰው አገር የዚያን ጉዳት መጠን ለመቀነስ ተገቢውን ስራ ያከናውናል፤ ሲመች ለመካስም ይወያያል።
4. ፍትሃዊና ተገቢ የውሃ አጠቃቀም መርህ
ሶስቱም ሀገራት በሀገራቸው ውስጥ የሚገኙ የጋራ ውሃቸውን በፍትሃዊነትና በአግባቡ ይጠቀማሉ።
በፍትሃዊነት እና በአግባቡ በጥቅም ላይ ስለመዋሉም ለማረጋገጥ አገራቱ የሚከተሉትን መመሪያዎች ያጤናሉ።
ሀ. መልክዓ ምድር፣ የውሃ መልክዓ ምድር በውሃው ላይ ተመስርተው የሚኖሩትን፣ የዓየር ንብረት፣ ስነ ምህዳሩን እና ሁሉንም ተያያዥ የተፈጥሮ ነገሮች
ለ. የአባይ ተፋሰስ አገራትን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎትን
ሐ. በአባይ ተፋሰስ አገራት በወንዙ ላይ ህይወታቸው የተመሰረተ ነዋሪዎች
መ. በአንዱ የወንዙ ተፋሰስ አገር የወንዙን ውሃ መጠቀም በሌላው የተፋሰሱ አገር ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ
ሰ. በወቅቱ እና በቀጣይ ሊኖር የሚችል የውሃ ተጠቃሚነት
ረ. የውሃ ምንጮችን መጠበቅ፣ ከጉዳት መከላከልና ማልማት እና ይህም የሚጠይቀው ወጪ
ሸ. ታቅዶ በሚውል ወይም ለተመረጠ የውሃ ፍጆታ ያለው ተነፃፃሪ አማራጭ እስከየትነት
ቀ. ለናይል ወንዝ ስርዓት የተፋሰሱ አገራት ድርሻ መጠን
በ. በእያንዳንዱ የናይል ተፋሰስ አገር የናይል ተፋሰስ ሽፋን የሚኖረው ደርሻ
አንቀፅ 9. የሉዓላዊነት፣ የአንድነት እና የአገር ግዛት ሉዓላዊነት መርህ
የናይል ወንዝን በተቻለ መጠን ለመጠቀም እና ለመጠበቅ ሶስቱ አገራት እኩል ሉዓላዊነት፣ አንድነት እና የአገር ግዛት ሉዓላዊነትን መሰረት በማድረግ ተባብረው ይሰራሉ።
አንቀጽ 10. ልዩነቶችን በሰላም የመፍታት መርህ
እነዚህን መርህዎች በመተርጎሙ እና በመተግበሩ ሂደት የሚፈጠሩ ልዩነቶችን በመልካም ፈቃድ መርህ በንግግር እና በድርድር ይፈቷቸዋል።
በንግግሩ እና በድርድሩ የተሳተፉ አካላት ልዩነቶችን መፍታት ካልቻሉ ለሽምግልና ወይም ለንግግር ወደ አገራቱ ፕሬዚዳንቶች እና ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሊልኩ ወይም ሊጠይቁ ይችላሉ።
እነዚህ
የመረጥኳቸው ኢትዮጵያ ሱዳንና ግብጽ ተስማምተው የፈረሙት የመርህ ስምምነት አንቀጾች ግብጽ የኢትዮጵያን በአባይ ወሃ የመጠቀም መብት
ማክበሯን፣ ልዩነቶች ቢኖሩም በሰላማዊ መንገድ ብቻ ለመፍታት መሰማማቷን ያመለክታሉ።
ከቅርብ
ግዜ ወዲህ ይፋ የሆኑ መረጃዎች ግን ግብጽ ለዘመናት ስታደርገው እንደኖረችው ሁሉ ኢትዮጵያ በአጠቃላይ በአባይ ውሃ የመጠቀም አቅም
እንዳይኖራት በተለይ የህዳሴውን ግድብ የመገንባት አቅም የሌላት ደካማ፣ ከተቻለም ህልውና የሌላት አገር እንድትሆን በተለያዩ ተቋሟቷ
በኩል የምትችለውን ሁሉ እያደረገች መሆኑን አረጋግጠዋል። በኦሮሚያ ክልል ሁከት ተቀስቅሶ በነበረበት ወቅት ሁከቱን መነሻ በማድረግ
የግብጽ የኮንጎ ወንዝ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ናንሲ ኡመር ከአል ኢስማን ቴሌቪቭን ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የኦነግ አመራር
ነን የሚሉ ግለሰቦች ለተያዩ የግብጽ ሚዲያዎች የሰጡት አስተያየት፣ የግብጽ ባለሃብቶች በዚያ ሃገር የሚኖሩትን የኦነግ አባላትና
ደጋፊዎች ሰብስበው ያደረጉትን ንግግርና የገቡትን ቃል ወዘተ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የፈረጇቸውን ኦነግና
ግንቦት 7 የመሳሰሉ ቡድኖችን በመርዳት በእጅ አዙር ጥቃት ኢትዮጵያን ለማተራመስና ለማፈረስ እያከናወነች ያለውን ሴራ አጋልጧል።
እነዚህ ማስረጃዎች በሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በተደጋጋሚ ስለቀረቡ ዝርዝር ውስጥ መግባት አልፈልግም።
እርግጥ
ግብጽ ኢትዮጵያን ለማተራመስና ለማፈረስ እያከናወነች ያለውን የእጅ አዙር ጥቃት ኢትዮጵያ በማስረጃ አስደግፋ ይፋ ማወጣቷን ተከትሎ
የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲ ሲ ሃገራቸው ኢትዮጵያን የማተራመስ ዓላማ እንደሌላት ገልጸዋል። ከኢትዮጵያ ጋር ሰላማዊ
ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያደርጉት አል ሲ ሲ በይፋ ከዚህ የተለየ ነገር ሊናገሩ እንደማይችሉ የታወቀ ነው። ይገርም የነበረው በይፋ
ኢትዮጵያን እያተራመስኩ ነው ብለው ቢናገሩ ነበር። ማስረጃዎች
ግን ውስጥ ውስጡን ኢትዮጵያን እየገዘገዙ መሆናቸውን አደባባይ አውጥተውታል።
አፍሪካን
ኢንተለጀንስ የተባለ ተቋም በቅርቡ ይፋ ያደረገው መረጃም የግብጽ መንግስትና ተቋማት ከእጅ አዙር ጥቃት ባሻገር የአፍሪካ ሃገራትን
በማስተባባር ኢትዮጵያ እንዲጨቁኑ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አጋልጧል። የአፍሪካ ኢንተለጀንስ መረጃ አል ሲ ሲ በቅርቡ ማለትም እ ኤ
አ ከሴፕተምበር 13 እስከ 20፣ 2016 ዓ/ም በኒው ዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ጉባኤ ላይ አል ሲ ሲ የአፍሪካ ሃገራት
ኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያሳድሩ ሲወተውቱ እነደነበረ የሚያጋልጥ ነው። አል ሲ ሲ የአፍሪካ ሃገራት መሪዎች የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ
እድገት በመጫን እንዲተባበሯቸው የአፍሪካ መሪዎችን ለማግባባት ሞክረዋል። የደቡብ አፍሪካውን ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ፣ የናይጄሪያውን
ፕሬዝዳንት መሃመድ ቡሃሪ፣ የሶማሊያውን ፕሬዝዳንት ሃሰን ሼክ መሃመድ፣ ኢትዮጵያ በመገንባት ላይ የለችውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ
ግድብ በመቃወም እንዲተባበሯቸው ተማጽነዋል። አንድ የኦነግ ከፍተኛ አመራርም በግብጽ መጠለያ ተሰጥቶት በደህንነት ሃይሎች ጥበቃ
እየተደረገለት መሆኑን የተቋሙ መረጃ አጋልጧል።
ግብጽ
እረፍት አጥታ ውስጥ ለውስጥ ኢትዮጵያን ለማዳከም የምትሰራው ኢትዮጵያ አሁን ባላት የኢኮኖሚ እድገትና ዓለም አቀፍ ተሰሚነት ከቀጠለች
ከአፍሪካ ሃያላን ሃገራት አንዷ መሆኗን ስለተገነዘበች ይህን የኢትዮጵያ የገናናነት ጉዞ ለማክሸፍ ነው።
ግብጽ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ወደሃገሯ የሚፈሰውን የአባይ ውሃ እንደማይቀንስ ጠንቅቃ ታውቃለች። ይህ ብቻ ሳይሆን የውሃውን አመታዊ
ፍሰት በየወራቱ የተመጣጠነ እንዲሆን በማድረግና ወደግድቧ የሚገባውን ደለል በማስቀረት፣ እንዲሁም ርካሽ የኤሌትሪክ ሃይል ከኢትዮጵያ
በመግዛት (ይህ በመርህ ስምምነት ሰነዱ ላይም ሰፍሯል) ተጠቃሚ እነደሚያደርጋት ታውቃለች።
የግድቡን
ግንባታ የምትቃወመው ውሃ ያስቀርብኛል፣ ጉዳት ያስከትልብኛል
በሚል ስጋት ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ህዝብ የይቻላል መንፈስ በመገንባት ለበለጠ ስኬት ስለሚያነሳሳ፣ ወደብልጽግና የሚያሸጋግራትን
መንገድ በመቅደድ የአፍሪካ ሃያልነቷን ስለሚያረጋግጥ ይህን ለማጨናገፍ ነው። ሃያልነቷ የናይል ተፋሰስ ሃገራትን ባካተተው የናይል
ኢኒሼቲቭ በኩል እየተከናወነ ያለው ፍትሃዊና ሚዛናዊ የውሃ ሃብት ድርሻ ባለቤትነትን የማረጋገጥ ስራ ላይ ተጽእኖ የማሳደር ጉልበት
ይሰጣታል በሚል የኢትዮጵያንና ሌሎች የናይል ተፋሰስ ሃገራትን ፍትሃዊ የውሃ ባለድርሻነት መብት ጥያቄ ከወዲሁ ለማዳፈንም ነው።
በመሆኑም
የኢትዮጵያ ህዝብ በታላቅ ሃገራዊ መገባባት ‘ምንም ያህል ደሃ ብንሆንም
ድህነታችንን ለማስወገድ ማንኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን። ስለዚህ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሰራት አለበት’ በሚል ከአምስት ዓመት በፊት የገባውን ቃል በማደስ የህዳሴውን ግድብ
በመገንባት የኢትዮጵያን ሃያልነት ለማረጋገጥ መነሳት አለበት።
No comments:
Post a Comment