አባ
መላኩ
አዋጅ ወይም
የጸጥታ ሃይል የአገር ሰላም ዋስትና ሊሆኑ አይችሉም። በየትኛውም ዓለም የሰላም ዋስትና ህብረተሰቡ ነው።
የእኛ አገርም ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም። እስካሁን በአገራችን የተመለከትነው የህግ የበላይነት የተረጋገጠው በህብረተሰቡ ቀጥታ ተሳትፎ ብቻ ነው። በአገራችን
የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ውጤታማ የሚሆነው የህብረተሰቡ ተሳትፎ ሲኖርበት ብቻ ነው። አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የአገርን ደህንነትና ሰላም ለማረጋገጥ እንጂ የዜጎችን
ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለመደፍጠጥ አይደለም።
የአስቸኳይ ጊዜ
አዋጅ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታችንን ሊቀለብሰው ከቶ የሚችል አይሆንም። አንዳንዶች አገራችን የደነገገችውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን
ተከትሎ የሚሰሙ ትችቶች አግባብነት የጎደላቸው ሆነው አገኝቻቸዋሉ። ለአብነት
አበቃልን ወደ ደርግ ስርዓት ልንመለስ ነው፤ የዜጎችን መብት ሙሉ ለሙሉ የሚደፈጥጥ ነው፤ መንግስት የፈለገውን ማድረግ
እንዲችል በማሰብ ያደረገው ጉዳይ ነው ወዘተ በማለት የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰነዝሩ ይደመጣሉ። የሁንና እውነታው ይህ አይደለም።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን የዴሞከራሲ ስርዓት ቁንጮ ነን በሚሉት በምዕራባዊያን አገሮችም በአሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ቱርክ ታውጇል። የተፈጥሮን ወይም ሰው ሰራሽ አደጋን ለመከላከል ወይም ለመቆጣጠር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይደነገጋል። ይህ የሚደነገገው
ለህዝብና አገርና ጥቅም ሲባል በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ የሚቆይ
ህግ እንጂ የዜጎችን መብት ለመጋፋት አይደለም።
የአገራችን
ህገመንግስት የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብትን ማረጋገጥ የቻለ የብሄሮች፣ የብሄረሰቦችና ህዝቦች የቃልኪዳን ሰነድ ነው።
አገራችን ህግመንግስታዊ መብቶች የተረጋገጡባት፣ ማንም የፈለገውን ሃሳብ
በሰላማዊ መንገድ ማራመድ የሚችልባት ህገመንግስታዊ
ስርዓት የነገሰባት አገር ነች። ህገመንግስታዊ ስርዓቱ
ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ማንነታቸውን እንዲያውቁ ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር እንዲችሉ የህግ የበላይነት
እንዲረጋገጥ አድርጓል። የሁንና በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈሩ የህዝቦች መብቶች ሁሉም በሚገባው መንገድ
ተተግብረዋል ማለት ግን አይደለም። በርካታ እጥረቶች አሉ። እነዚህን ታግለን የማስተካከል የሁላችንም ሃላፊነት ነው። በቅርቡ
በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች በተለይ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተነሱ ሁከቶች ከዚህ የመነጩ እንደሆኑ ማየት ይቻላል።
የዴሞክራሲ ባህሉ እጅግም ባልጠነከረባት አገራችን፣ ሁሉም ህገመንግስታዊ መበቶች በአግባቡ ባይተገበሩ አይገርምም።
በአገራችን ያለው
የፓለቲካ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ የመጣ መሆኑን ሁሉም የሚስማማበት ጉዳይ ነው። የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መጎልበት በርካታ
ጉዳዮችን መሰረት ያደረገ ነው። የቀድሞው የአገራችን ሁኔታ፣ ህብረተሰቡ
ለመብቱ ወይም ስለሌላው ያለው አስተሳሰብ (ባህል፣ ትምህርት፣ ወግ)
ወዘተ ተጠቃሾች ናቸው። የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በአጭር ጊዜ የምናጎለብተው ሳይሆን፤ ውስብስብና ትግልን
የሚሻ የማያቋርጥ ሂደት ውስጥ ማለፍን የሚጠይቅ ነው፡፡ አገራችን ወደ ዴሞክራሲ መስመር አቀናች እንጂ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታዋ ብዙ የሚቀረው ነው። አገራችን አሁን ለምትገኝበት የዴሞክራሲ ስርዓት መቃናት የሁላችንም አስተዋጽዖ እንዳለበት ሁሉ ክፍተቱንም መሙላት የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይገባል። አገራችን ተጨባጭ ለውጦችን
ማስመዝገብ ችላለች። ነገር ግን ይህን ለውጥ ማስቀጠል የሚቻለው የያዝነውን በማስጠበቅ አዳዲስ ውጤቶችን ማስመዝገብ ስንችል ነው። በአገራችን ችግሮችን በመነጋገርና በመወያየት የመፍታት ባህል የተፈለገውን ያህል ባይዳብርም መወያየት የሚያስችል
ሁኔታዎች ግን አሉ።
በአገራችን ከቅርብ
ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ አካባቢዎች ሁከትና ብጥብጥ በተደጋጋሚ እየታየ
ነው። የሰው ህይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፣ ዜጎች ተሰደዋል፣ ንብረታቸው ተዘርፏል፤ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተጥሰዋል፤
ስነልቦናዊ ጫና ደርሶባቸዋል። ይህ ድርጊት የውጭ ሃይሎች የህዝብ
ጥያቄዎችን ተንተርሰው አገራችንን ለማተራመስ አቅደው እየፈጸሙ ያሉት እኩይ ተግባር መሆኑን መገንዘብ የሚያዳግት አይመስለኝም። ይህን የተቀናጀና
የተናበበ የጠፋት ድርጊት በመደበኛው የህግ አገባብ በአጭር ጊዜ ለመፍታት የሚቻል ባለመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈልጓል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መንግስት የፈጠረው ነገር አይደለም። መክረን ዘክረን
ባጸደቅነው የኢፌዴሪ ህገመንግስት ወስጥ በዝርዝር የተቀመጠ አገሪቱን ከተፈጥሮና ሰውሰራሽ አደጋዎች እንዲታደግ
የተዘጋጀ ነው። ህገመንግስታችን ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መቼ እንዴትና ለምን እንደሚደነገግ በዝርዝር አስፍኗል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገራችን ላይ ከፍተኛ አደጋ ሊያመጣ
የሚችሉ አካሄዶች እየተስተዋሉ ነው። ዜጎች በብሄራቸው ወይም በዘራቸው የሚገለሉበት ወይም የሚገደሉበት፣ የሚፈናቀሉበት ወይም ንብረታቸው
የሚወድምበት አካሄድን እያስተዋልን ነው። የባለሃብቶች ንብረት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ጨምሮ በርካት ንብረት በጠራራ ጸሃይ
ጋይቷል አሊያም ተዘርፏል።
የነውጥ
ሃይሎች የህብረተሰብን ጥያቄ ከለላ በማድረግ ለነውጥ ያነሳሳል ያሉትን ስሜት ኮርኳሪ ነገሮችን በመጨማመር ወጣቱን ወዳልተፈለገ መንገድ
እንዲያመራ አድርገውታል። በዚህም ንጹሃንን ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። ከላይ ለማንሳት እንደሞከርት ህይወት ጠፍቷል፣ አካል ጎድሏል፣
ንብረት ወድሟል ስነልቦናዊ ውድቀት ደርሷል። የአገራችን መልካም ስም አጉደፏል። በቀጣይም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ላይ ትልቅ አሉታዊ ጫና የሚፈጥሩ
ድርጊቶች ተስተውለዋል። የአገር ወስጥና የወጪ ምርቶቻችን ላይም
ተጽዕኖ ፈጥሯል።
በዚህ
ከቀጠለ የአገራችን ህልውናም አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ምንም ጥርጥር የለውም። በአጠቃላይ ስርዓት
አልበኝነት በአገራችን እንዲነግስ እየተደረገ ነው። ይህ ሁሉ የጥፋት የተፈጸመው በተደራጁ ሃይሎች እንጂ እውነትም በተቃውሞ አደባባይ
በወጡ ህዝቦች አይደለም። ይህን አይነት የጥፋት ተልዕኮ በመደበኛው የህግ አግባብ በአጭር ጊዜ ወደነበረበት ለመመለስ አልተቻለም።
ለዚህም ነው አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያስፈለገው። ይህ አዋጅም ከሰማይ የወረደ፣ የዜጎችን መብት የሚገፍ፣ የህዝብን ጥያቄ የሚያፍን
አይደለም። በህገመንግስታችን አንቀጽ 93 በዝርዝር ስለ አስቸኳይ
ጊዜ አዋጅ እንደተቀመጠው፣
1. ሀ/ የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር
ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን፣ ማናቸውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት፣
የፌዴራሉ መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ሥልጣን አለው፡፡
ለ/ የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት የክልል መስተዳድሮች በክልላቸው
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያውጁ ይችላሉ፡፡ዝርዝሩ ክልሎች ይህን ሕገ መንግሥት መሰረት በማድረግ በሚያወጧቸው ሕገመንግሥቶች ይወሰናል፡፡
2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 /ሀ/ መሰረት የሚታወጅ የአስቸኳይ ጊዜ
አዋጅ፣
ሀ/ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ባለ ጊዜ የታወጀ ከሆነ በታወጀ በአርባ ስምንት ሰዓታት ውስጥ ለሕዝብ
ተወካዮች ምክር ቤት መቅረብ አለበት አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት ሦስተኛው ድምጽ ተቀባይነት ካላገኘ ወዲያውኑ ይሻራል፡፡
ለ/ ከላይ በንዑስ አንቀጽ /ሀ/ ሥር የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ባልሆነበት
ወቅት የሚታወጅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረብ ያለበት አዋጁ በታወጀ በአሥራ አምሥት ቀናት ውስጥ ነው፡፡
3. በሚኒስትሮች ምክር ቤት የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በምክር ቤቱ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ ሊቆይ የሚችለው
እስከ ስድስት ወራት ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምጽ አንድን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በየአራት ወሩ በተደጋጋሚ
እንዲታደስ ሊያደርግ ይችላል፡፡
4. ሀ/ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ጊዜ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣቸው ደንቦች መሰረት የሀገርን ሰላምና
ሕልውና፣ የሕዝብን ደህንነት፣ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ሥልጣን ይኖረዋል፡፡
ለ/ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን መሰረታዊ የፖለቲካና የዴሞክራሲ መብቶችን፣ የአስቸኳይ
ጊዜ አዋጁን ለማወጅ ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ለማስወገድ ተፈላጊ ሆኖ በተገኘውደረጃ፣ እስከ ማገድ ሊደርስ የሚችል ነው፡፡
ሐ/ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአስቸኳይ
ጊዜ አዋጅ ሥራ የሚያወጣቸው ድንጋጌዎችና
የሚወስዳቸው እርምጃዎች በማናቸውም ረገድ በዚህ ሕገመንግሥት
አንቀጽ 1፣፣ 88፣ 25፣ እና 39 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 የተቀመጡትን መብቶች የሚገድቡ ሊሆኑ አይችሉም፡፡
5. በሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ወቅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአባላቱና ከሕግ ባለሙያዎች
መርጦ የሚመድባቸው ሰባት አባላት ያሉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ያቋቁማል፡፡ ቦርዱ አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች
ምክር ቤት በሚጸድቅበት ጊዜ ይቋቋማል፣
6. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ የሚከተሉት ሥልጣንና ኃላፊነቶች
አሉት፡፡
ሀ/ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት የታሰሩትን ግለሰቦች ስም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ይፋ ማድረግና የታሰሩበትን
ምክንያት መግለጽ፣
ለ/ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የሚወሰዱት እርምጃዎች በማናቸውም ረገድ ኢሰብዓዊ አለመሆናቸውን መቆጣጠርና መከታተል፣
ሐ/ ማናቸውም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃ ኢሰብዓዊ መሆኑን ሲያምንበት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም የሚኒስሮች ምክር
ቤት እርምጃውን እንዲያስተካክል ሐሳብ መስጠት፣
መ/ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃዎች ኢሰብዓዊ ድርጊት የሚፈጽሙትን ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ማድረግ፣
ሠ/ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲቀጥል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ ሲቀርብ ያለውን አስተያየት ለምክር ቤቱ
ማቅረብ፡፡
እንግዲህ ይህ አዋጅ መንግስት የፈጠረው ሳይሆን በህገመንግስታችን ላይ የነበረ
ለህዝብና ለአገር ደህንነት ቀድሞ ታስቦና ታልሞ የተዘጋጀ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ አገር ወዳድ ህብረተሰብ ሁሉ ሊረባረብ ይገባል።
No comments:
Post a Comment