Wednesday, 19 October 2016

የማንነት ጥያቄ መድረሻ እኩልነት ይሁን፣ የክልል መንግስታትም ለጥያቄው ህገመንግስታዊ ምላሽ ይስጡ




ኢብሳ ነመራ
የአምስተኛው ዙር የመንግስት የስልጣን ዘመን ሁለተኛ ዓመት ስራ ሲጀመር የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር በተያዘው ዓመት መንግስት የሚያከናውናቸውን ተግባራትን መዘርዘራቸው ይታወሳል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕሬዝዳንቱ ንግግር ለማጽደቅ መብራራት አለባቸው የተባሉ ጉዳዮችን አንስቶ የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል። የውሳኔ ሃሳቡ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርም ደሳለኝ ማብራራያ ከተሰጠበት በኋላ በቅርቡ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህ ጽሁፍ ፕሬዝዳንቱ በያዝነው ዓመት ይከናወናል ብለው ካነሷቸው ጉዳዮች መሃከል በሃገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የማንነት ጥያቄዎችን አስመልክተው ያቀረቡትን ሃሳብ ልመለከት ወድጃለሁ።
የማነነትን ጥያቄ አስመልክተው ፕሬዝዳንቱ ባደረጉት ንግግር፤ 2ኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተግባራዊ ማድረግ በጀመርንበት ዓመት የተከሰቱት ችግሮች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንድምታ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታችንን በማዳበር ልንፈታቸው የሚገባ ልዩ ልዩ ፖለቲካዊ ችግሮች እንዳሉም አመላክተውናል። በዚህ ረገድ ቀዳሚው ጉዳይ በሃገራችን የብሔር ብሔረሰቦችን መብት መሰረት አድርገው የሚነሱ የማንነት ጥያቄዎችን በህገ-መንግስታችን በጥብቅ በመመራት የመፍታት አስፈላጊነት ነው። ለማንም ግልፅ እንደሚሆነው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን የተዋቀረው ሃገራችን የብዙ ህዝቦች አገር የመሆኗን እውነታ ያለማቅማማት በመቀበል ነው። ብለዋል።
ሁላችንም እንደታዘብነው ኢህአዴግና አጋር ድርጅቶቹ የሃገሪቱ ከፍተኛ የስልጣን አካል የሆነው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን ሙሉ በሙሉ አሸንፈው መንግስት አዋቅረው ሶስት ወራት እንኳን ሳይጓዙ በኦሮሚያ ክልል አንድ ጥግ ፈንድቶ መላውን የክልሉን ከተሞች እስከማዳረስ የዘለቀ ሁከት አዘል ተቃውሞ ተቀስቅሷል። በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎችም ተመሳሳይ ሁከት ተቀስቅሷል። አንዳንድ በተቃውሞ ጎራ የተሰለፉ ወገኖች ኢህአዴግ ምርጫውን ሙሉ በሙሉ አሸንፌያለሁ ባለ ማግስት የተቀሰቀሰውን ይህን ተቃውሞ ምርጫው በትክክል አለመካሄዱንና ኢህአዴግ የማይገባውን ድምጽ ለማግኘቱ ማሳያ አድርገው እንደወሰዱትና የተቃውሞ አጀንዳቸው አድርገውት እንደነበረም ታዝበናል። እርግጥ ነው፣ ሙሉ የምክር ቤት መቀመጫን ያሸነፈ ፓርቲ ገና ሶስት ወር እንኳን ስልጣን ላይ ሳይቆይ የሃገሪቱን አንድ ሶስተኛ በሚወክለው የኦሮሚያና አማራ ክልሎች መረር እና ሰፋ ያለ ተቃውሞ ሲገጥመው የምርጫውን ተአማኒነት ጥያቄ ላይ መጣሉ አይቀሬ ነው።
ሁኔታውን ጠለቅ ብለን ስናየው ግን ለየት ያለ ዕውነት መኖሩን እንረዳለን። በቅድሚያ ኢህአዴግ አብላጫ ቁጥር ያለው መራጭ ህዝብ ለኢህአዴግ ድምጽ የሰጠው ኢህአዴግ ፍጹም ጥሩ ነው በሚል እምነት አለመሆኑ መታወቅ አለበት። ኢህአዴግ ለመመረጥ ያበቃው ለተፎካካሪነት ከቀረቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ሲነጻጻር፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት እንዲመዘገብ ካደረገው እድገት በተጨማሪ የመንግስት ስልጣን በክልሎች እጅ ባለበትና ባልተማከለው ፌደራላዊ ስርአት ሃገሪቱን መምራት የሚያስችል የተሻለ አወቃቀርና ጥንካሬ ያለው በመሆኑ ነው። ህዝብ ለኢህአዴግ ድምጽ ሲሰጥ ኢህአዴግ የነበሩበትን አማራሪ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በሚገባ ያውቅ ነበር። ጥቂቶች እጅግ እየበለጸጉ ብዙሃኑ ግን በነበሩበት እንኳን መዝለቅ ተስኗቸው የሚንገዳገዱበትን ፍትሃዊ ያልሆነ የሃብት ክፍፍል ማስተካካል እንዳልቻለ ህዝቡ ያውቅ ነበር። በርካታ ወጣቶች ወደከፍተኛ የትምህርት ተቋማት - ዩኒቨርሲቲዎችና የቴክኒክና ሞያ ኮሌጆች የመግባት እድል ማግኘታቸው ብዙ ቤተሰቦችን ቢያስደስትም ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ ቤት መዋላቸው ግን በተለይ በወጣቱ ዘንድ ተስፋ መቁረጥና ቅሬታ እንዳሳደረ ነበር።
በዚህ ሁኔታ ኢህአዴግን የመረጡት፣ ቀደም ሲል እንዳነሳሁት ከተፎካካሪዎቹ ጋር ሲነጻጻር የተሻለ በመሆኑ፣ እንዲሁም እህአዴግም እንደሚለው ችግሮቹን ያስተካክላል በሚል እምነት ነው። ሆድ ለባሰው  እንዲሉ ድሮም የተሻለ አማራጭ አጥቶ እንጂ ወዶትና ተመክቶበት ያልመረጠው ህዝብ፣ በተለይ ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ትንሽ ሰበብ ሲያገኝ ቅሬታው ፈንድቶ ለተቃውሞ የተነሳበት ሁኔታ መኖሩ አይካድም። ተቃውሞው ከተቀሰቀሰ በኋላ ሁኔታውን ሃገር ለማተራመስ አጀንዳ የተጠቀሙበት ቡድኖች መኖራቸውም ይታወቃል።  ይህ ሁኔታ ፕሬዝዳንቱ በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ 2ኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተግባራዊ ማድረግ በጀመርንበት ዓመት የተከሰቱት ችግሮች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንድምታ ነበረው በሚል የገለጹትን ትክክለኛነት ያመለክታል።
ሃገሪቱን ከገጠማት ችግር ጀርባ ካለው ከኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ በተጨማሪ ፖለቲካዊ አንደምታዎችም እንደነበሩ ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው አንስተዋል። ይህም . . . ባለፈው ዓመት ያጋጠሙን ችግሮች የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታችንን በማዳበር ልንፈታቸው የሚገባ ልዩ ልዩ ፖለቲካዊ ችግሮች እንዳሉም አመላክተውናል። በዚህ ረገድ ቀዳሚው ጉዳይ በአገራችን የብሔር ብሔረሰቦችን መብት መሰረት አድርገው የሚነሱ የማንነት ጥያቄዎችን በህገ-መንግስታችን በጥብቅ በመመራት የመፍታት አስፈላጊነት ነው። በሚል ያቀረቡት ነው።
ይህ ፕሬዝዳንት ሙላቱ በንግገራቸው ያነሱት ሃሳብ በተለያዩ አካባቢዎች ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ የተቀሰቀሱትን ለሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆኑ ተቃውሞዎችንና ሁከቶችን ይመለከታል። ባለፈው ዓመት በአማራ ክልል ከቅማንት ህዝብ የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ችግር ተፈጥሮ እንደነበር እናስታውሳለን። በዚሁ ክልል በትግራይ ክልላዊ መንግስት ውስጥ በወልቃይት አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ጉዳይ ጋር በተያያዘም እስካሁንም እልባት ያልተበጀለት ችግር መፈጠሩም እንዲሁ ይታወቃል። በደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስትም እንዲሁ በኮንሶ ወረዳ አካባቢ የማንነት ጥያቄ አለን ከሚሉ ቡድኖች ጋር በተያያዘ የሰው ህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት ያስከተለ ሁከት ተቀስቅሷል።
ፕሬዝዳንት ሙላቱ በንግግራቸው በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ባነሱት ሃሳብ ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የተገነባው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የአብዛኞቹን ብሔር ብሔረሰቦች ጥያቄ በተግባር የመለሰ ቢሆንም፣ በተወሰነ ደረጃ መሰረተ ሃሳቡ ተግባራዊ ያልተደረገባቸው ማህበረሰቦች ደግሞ እንደነበሩ ታይቷል። በዚህ የተነሳ ዘግይተው ጥያቄ የሚያቀርቡ ራሳቸውን የቻሉ ማህበረሰቦች የተከሰቱ ሲሆን፣ የነዚህ ህዝቦች ጥያቄ በዴሞክራሲያዊው ህገ መንግስታችን ማዕቀፍ ሊስተናገድ የሚችልና የሚገባው ሆኖ ይገኛል። ይሁንና ይህን የመሰለው ፍትሃዊ ጥያቄ  በወቅቱ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኝ ባለመደረጉ በተለያዩ አካባቢዎች ለግጭት መንስኤ ሲሆን ታይቷል።  ብለዋል።
የኢትዮጰያ ብሄሮች ብሄረሰቦችቸና ህዝቦች የማንነት ወይም ራስን በራስ የማስተዳደር ህገመንግስታዊ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ኢህአዴግ የሚያሳማው አቋም አለው የሚል እምነት የለኝም። ኢህአዴግ የብሄራዊ ማንነት ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት አለባቸው የሚል አቋም የያዘው የኢፌዴሪ ህገመንግስት ከጸደቀና በህዝብ ውክልና ስልጣን ከያዘ በኋላ ሳይሆን በትጥቅ ትግል ወቅት ነው።
በመሰረቱ፣ የኢፌዴሪ መንግስት በህገመንግስቱ መሰረት ሲዋቀር የማንነት ጥያቄ ያነሱ ሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጥያቄያቸው ተመልሷል ብሎ በድፍረት መናገር የቻላል። ይሁን እንጂ በተለያየ ምክንያት ተዳፍነው የቆዩ የማንነት ጥያቄዎች ሊነሱ እነደሚችሉም ይታወቅ ነበር። የኢፌዴሪ ህገመንግስት የማንነት ጥያቄ ምላሽ ያገኝ የሚችልበትን ስርአት የደነገገው ለዚህ ነው። የማንነት ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ተመልሷል የሚል እምነት ቢኖርማ ኖሮ፣ ምላሽ የሚያገኝበትን ስርአትን በህገመንግስት መደንገግ ባላስፈለገ ነበር። በመሆኑም በማንኛውም ግዜ የማንነት ጥያቄዎች ሲነሱ ጥያቄውን በአግባቡ መርምሮ ምላሽ መስጠት የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ህገመንግስታዊ ግዴታ ነው።
ፌደራላዊ ስርአቱ ከተዋቀረ በኋላ የማንነት ጥያቄዎች ተነስተዋል። በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ በደቡብ ክልል ከጉራጌ ብሄረሰብ ጋር ተጨፍልቆ የነበረው የስልጤ ብሄረሰብ አንስቶት በህገመንግስቱ መሰረት ምላሽ ያገኘው የማንነት ጥያቄ ቀደምት ነው። የስልጤ የማንነት ጥያቄ፣ ስልጤ የራሱ የማንነት መገለጫዎች ያሉት ብሄረሰብ ነው፣ የለም የቤተጉራጌ አካል ነው በሚሉ ወገኖች መሃከል ከተነሳ የሃሳብ ፍልሚያ የዘለለ ህይወት ወዳጠፋና ንብረት ወዳወደመ ግጭትነት ሳይሸጋገር በህገመንግስቱ መሰረት ነበር የተፈታው። ከዚያ በኋላ በአማራ ክልል የተነሳው የቅማንት ህዝብ የማንነት ጥያቄ ግን እንደስልጤው የማንነት ጥያቄ በቀላሉ መፍትሄ አልተበጀለትም። ለጥያቄው ምላሽ መስጠት ያለበት የአማራ ክልላዊ መንግስት ጉዳዩን ሲያጓትት ቆይቶ ተገቢ ያልሆነ መቃቃር እንዲፈጠር ምክንያት የሆነበት ሁኔታ መኖሩን የሚያመለክቱ ሁኔታዎች አሉ። ጥያቄው በህገመንግስቱ መሰረት ምላሽ ካገኘ በኋላም ቢሆን በተለይ ከወሰን አከላለል ጋር በተያየያዘ የባለፈውን ዓመት የሃገራችንን ገጽታ ያደበዘዘ ገዳይና አውዳሚ ሁከት ተቀስቅሷል። ይህ መደገም የሌለበት መማሪያ የሚሆን አጋጣሚ ነው።
ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ሌላው የባለፈውን ዓመት ድባብ ያደበዘዘ ግጭት የፈጠረው ከወልቃይት ጋር የተያያዘው ጥያቄ ነው። በትግራይ ክልላዊ መንግስት ስር ከሚገኘው የወልቃይት አካባቢ ህዝብ ጋር በተያያዘ የማንነት ጥያቄ መነሳቱን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሰምቷል። የጥያቄው አነሳስና አቀራረብ ግን ከግልጽነት መጥፋት ይሁን በሌላ  እስካሁን አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የተሟላ ግንዛቤ የለውም።
ይህን ያደረገው በቅድሚያ የማንነት ጥያቄው መነሳት የነበረበት ትግራይ ውስጥ በሚኖረው የወልቃይት አካባቢ ነዋሪ ህዝብ ሆኖ ሳለ ጥያቄው የቀረበው በአማራ ክልል በተለይ በሰሜን ጎንደር ዞን በሚኖሩና በተደራጁ ቡድኖች መሆኑ ነው። ይህ ሁኔታ በብዙዎች ዘንድ ጥያቄው የማንነት ሳይሆን የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ሆኖ የታየበት ሁኔታን አስከትሏል። እርግጥ ይህ የሆነው የትግራይ ክልላዊ መንግስት በክልሉ ውስጥ የዚህ አይነት ጥያቄ ማንሳት አይቻልም ብሎ አባሯቸው ከሆነ ጉዳዩ ህገወጥ ነው። የሁን እንጂ ይህ ሰለመደረጉ እስካሁን የተነገረ ነገር የለም።
በወልቃይት ጉዳይ ላይ የህዝብን ግንዛቤ ያዛባው ሌላው ጉዳይ፣ በህገመንግስቱ መሰረት ጥያቄው መቅረብ የነበረበት ለትግራይ ክልላዊ መንግስት ሆኖ ሳለ ይህ አለመደረጉ ነው። የትግራይ ክልላዊ መንግስት ጥያቄው እንዳልቀረበለት በይፋ አሳውቋል። የክለሉ መንግስት ጥያቄው ቀርቦለት አልቀበልም ብሏል የሚሉም ወገኖችን ግን አድምጠናል። በዚህ ዙሪያ ያለው መረጃ አሁንም በብዙዎች ዘንድ አሻሚ እንደሆነ ነው። ይህ በሃገር ጉዳይ ላይ ግልጽ መረጃ ማጣት በራሱ ችግር መሆኑ እንደተጠበቀ፣ በ2009 ዓ/ም ጥያቄ አለኝ የሚለወም ወገን ጥያቄውን ህገመንግስቱ በሚያዘው መሰረት ለክልሉ መንግስት እንዲያቀርብ፣ የክለሉ መንግስትም በህገመንግስቱ መሰረት ለጥያቄው በተገቢው ግዜ ውስጥ ምላሽ መስጠት መስጠት የሚገባው መሆኑ ግን ሁሉንም ዜጋ ያስማማል። ይህ የህግ የበላይነት እንዲከበርና የሃገሪቱ ሰላም ዋስትና እንዲኖረው የሚፈልጉ ዜጎች ሁሉ አቋም ነው። ፕሬዝዳንት ሙላቱም በንግግራቸው ይህንኑ ገልጸዋል።
ከማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ሌላ ድንግርግር ውስጥ ከቶን የነበረው የኮንሶ ህዝብ ጥያቄ ነው። በተለይ ውጭ ሃገር የሚገኙ ሚዲያዎች ጉዳዩን የኮንሶ ህዝብ የማንነት ጥያቄ እንዳነሳ አድርገው ሲናገሩ መቆየታቸው ይታወቃል። ይህን ጉዳይ ለማስተባባር የተቋቋመ ቡድን አመራር ነን የሚሉ ግለሰቦችን እያነጋገሩ የማንነት ጥያቄ መነሳቱን ሊያረጋግጡልን ሞክረዋል። ይህ ጉዳይ አደናጋሪ የሆነው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚያውቀው፣ የኮንሶ ህዝብ ለማንነቱ እውቅና ተሰጥቶት ራሱን በራሱ እያስሰተዳደረ የሚገኝ በመሆኑ ነው።
የኮንሶ ህዝብ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በመጀመሪያ በልዩ ወረዳነት በኋላ በሰገን ህዝቦች ዞን ውስጥ በወረዳነት በመረጣቸው ተወካዮቹ አማካኝነት፤ በራሱ ቋንቋ የመንግስት አገልግሎት እያገኘ፣ ልጆቹን በአፍ መፍቻ ቋነቋቸው እያስተማረ፣ ታሪኩን እየተንከባከበና እያስተዋወቀ፣ ባህሉን እያጎለበተ ሲኖር መቆየቱ ይታወቃል። የማንነት ጥያቄ መድረሻ ደግሞ የእነዚህ መብቶች መረጋገጥ ነው። በመሆኑም የማንነት ጥያቄው ምንነት ግር የሚያሰኝ ነበር። እርግጥ የኮንሶ ህዝብ አሁንም ከማንነት መብትና ነጻነቶቹ ጋር በተገናኘ ያልተመለሱለትና ሊመለሱለት የሚገባቸው ጥያቄዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ሳይዘነጋ፣ በይፋ የቀረበው ጥያቄ የሚያመለክተው ግን የማንነት ሳይሆን የአወቃቀር ጥያቄ መሆኑን ነው። ወረዳ ሳይሆን ዞን ሆኜ ልዋቀር የሚል ጥያቄ። ይሄም ቢሆን ግን በተለይ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የኮንሶ ህዝብ በአጠቃላይም የኢትዮጵያ ህዝብ በግልጽ ሊያውቀው በሚገባ አኳኋን አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል። ለጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ አለመስጠት ሃገሪቱን ማተራመስና ማውደም ለሚፈልጉ ወገኖች ቀዳዳ እንደሚከፍት መታሰብ አለበት።
በአጠቃላይ በህገመንግስቱ መፍትሄ የተበጀለት የማንነት ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ አጥቶ ወይም በወቅቱ ምላሽ ባለማግኘት የግጭት ምክንያት መሆን የለበትም። ለሚነሱ የማንነት ጥያቄዎች አፋጣኝ ህገመንግስታዊና ምላሽ አለመስጠት የህግ የበላይነትን ይጻረራል። ጥያቄ አቅራቢው ህዝብ በመንግስት ላይ ያለውን እምነት በመሸርሸር፣ መብቱን በሌላ አመቺ ነው ብሎ ባመነበት መንገድ ወደማስከበር እንዲሸጋጋር ያደርጋል። ይህ ያሀገሪቱን ሰላም ያደፈርሳል። የታሪክ ጠባሳ ሊጥል የሚችል ግጭትና ደም መፋሰስ ይፈጥራል። ለውጭ ጠላቶቻችንም ሃገሪቱን አተራምሶ ለማጥፋት የሚያመች ሁኔታ ይፈጥራል። በመሆኑም ያመንነት ጥያቄ መቼም ሊነሳ እንደሚችል ተረድቶ ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀት ህገመንግስታዊ ግዴታ መሆኑን በማሰብ፣ ይህን ሃላፊነት ለመወጣት መዘጋጀት በህዝብ ውክልና ስልጣን ከተረከቡ አካላት በሙሉ ይጠበቃል። በተለይ ክልላዊ መንግስታት በዚህ ረገድ ህገመንግስታዊ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆን አለባቸው። ፕሬዝዳንት ሙላቱም በንግግራቸው ይህንኑ አሳስበዋል።  
እንግዲህ ፕሬዝዳንት ሙላቱ በምክር ቤቶቹ የስራ ዓመት መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር የማንነት ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ሊያገኙ እንደሚገባ አሳስበዋል። ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው የዴሞክራሲያዊ ስርዓታችን በሚደነግገው መሰረት በሁሉም ክልሎች ከማንነት ጋር  ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎች በተቻለው ፍጥነት የተሟላ እልባት እንዲሰጣቸው ይደረጋል። በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የአስተዳደር አካላት በየክልላቸው የሚገኙ እውቅና ያልተሰጣቸው ማህበረሰቦች ጉዳይ እስካሁንም መቆየት ያልነበረበት ስህተት እንደሆነ በመገንዘብ፣ ይህንኑ በአፋጣኝና በማያዳግም ሁኔታ እንዲያስተካክሉ ይደረጋል።  ማህበረሰቦቹም ይህን አጋጣሚ ለእኩልነት እንጅ ለበላይነት በማይበጅ አቅጣጫ የማይጠቀሙበት እንደሆነ ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ነበር ያሉት። የማንነት ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖች መድረሻቸው የእኩልነት መብታቸውን ማረጋገጥ ይሁን፣ የክልል መንግስታትም ለጥያቄው አፋጣኝ ህገመንግስታዊ ምላሽ ይስጡ።
      

No comments:

Post a Comment