(ሰለሞን
ሽፈራው)
እየነገርናቸው፤እያረጉት ዋዛ
ከተመለመለው፤የተሰጠው በዛ…
መንደርደሪያ
እንዲል
ወሎዬው መንዙመኛ፤እነሆ እስካለፈው 2007 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ለመላው የምስራቅ አፍሪካ ቀጠና እንደምሳሌ የሚወሰድ ሆኖ የቆየው
የሀገራችን ሰላምና መረጋጋት አሁን ላይ ላለመረጋጋቱ ዋስትና እንደሌለን
ይሰማን ጀምሯል፡፡ እናም ስለጉዳዩ አሳሳቢነት ያለመታከት እየፃፉ ተገቢ ትኩረት ይሰጠው ዘንድ አበክረው ሲያስገነዝቡ ከቆዩት ሰላም ወዳድ የዚች ሀገር ተርታ ዜጎች መካከል እኔም አንዱ መሆኔን
ሳስበው ከላይ በመግቢያዬ ያሰፈርኩት ግጥም ማስታወስ የሚያስፈልግ ሆኖ የተሰማኝ፡፡
ስለዚህ
የኢትዮጵያን የህዳሴ ጉዞ የሚፈታተኑት ችግሮቻችን እየተባባሱ መጥተው ዛሬ ላይ እንደ ሀገር ወደ ምንገንበት አጠቃላይ እውነታ እንዲያደርሱን
ስለቻሉበት ምክንያት መነሳት አለባቸው ብዬ የምወስዳቸውን መሰረታዊ ነጥቦች ነቅሴ እያወጣው የግል አቋሜን ማስቀመጥ ተገቢ መስሎ
ይሰማናልና ነው ብዕር ከወረቀት ማገናነቴ፡፡ እንግዲያውስ ከ2008 ዓ.ም መጀመሪያ ወዲህ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለውንና በተለይም ደግሞ አሁን ላይ
ይቺን ሀገር ወደ ለየለት የስርዓት አልበኞች መፈንጫነት ለመቀየር ያለመ አደገኛ አዝማሚያ እየያዘ የመጣ የሚመስለውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ
በተመለከተ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት እስካሁን ድረስ የሚሰጠው መግለጫና የሚያሳየው አቋም እንዴት ይገለፃል? እውን የችግሩን ስፋትና ጥልቀት በሚመጥን ጥናት ላይ የተመሰረተ
የመፍትሄ እርምጃ ለመውሰድ ሲሞክር የታዘብንበት አጋጣሚ አለን? ደግሞስ ይሄን ያህል በተደራጀ መልኩ ሀገር የማተራመስ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚችል አመፅ
ናፋቂ ሀይል እስኪፈጠር ድረስ ያውም እንደ ኢትዮጵያ ያለች ሀገር የመምራትን እጅግ ከባድ ሃላፊነት የተሸከመ የመንግስት አካል በዚህን
ያህል መጠን መዘናጋት ነበረበትን? ወዘተ ለሚሉ ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ የሚሆን የጋራ መግባባትን በሚጋብዝ ሀተታ ነው የሚጀምረው፡፡
ሌላው ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያለውና እንደሁለተኛ መሰረታዊ ነጥብ
ሊቆጠር የሚችል ሆኖ የሚሰማኝ ጉዳይ ደግሞ፤ ይህንን ሀገር ለማተረማመስ እየተሞከረበት ያለውን የአመፅ ተግባር እንቅስቃሴ የሚያቀነባብሩበትና
የሚመሩበት ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች በእርግጥ ይታወቃሉ ወይ?ከታወቁስ የትኞቹ ከየትኛው ክልል ህዝብ መሀል እየኖሩ ነው ለህዳሴው
ዘመን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን የማይመጥን የጥፋት ተልዕኮዋቸውን ማሳካት የያዙት? ለመሆኑ እነዚህ ስርዓቱን እንደ ስርዓት ለመናድ
ያለመ የቀለም አብዮት እንዲቀሰቀስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የሌላቸው የተቃውሞው ጎራ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በየሰበቡ የሚጭሩት
የነውጠኝነት እሳት እያስከተለ ስላለው ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ ጉዳይስ
ኢትዮጵያውያን እንደህብረተሰብ ምን ያህል የጋራ ግንዛቤ መጨበጥ ይጠበቅብናል?
ዜጎቿ፤የዕለት ጉርስ የዓመት ልብስ ፍለጋ ወደ የትኛውም የዓለም
ጥግ ሲሰደዱና በዚህ ምክንያትም ለፈርጀ ብዙ አደጋ እየተጋለጡ ህይወታቸውን
እስከማጣት ሲደርሱ በሚስተዋሉባት ድሀ ሀገር አቅም የተገነቡ የመሰረተ ልማት ተቋማትን እንደተራ ነገር በእሳት እያጋዩ ማውደምስ
ምን የሚሉት ፈሊጥ ነው? መላው የሀገራችን ህዝቦች ከጋራ ጠላታቸው ከድህነትና ከኁላ ቀርነት ለመላቀቅ ሲሉ በርካታ ዓመታትን በጠየቀ
ብርቱ ጥረት የገነቧቸውን እጅግ ጠቃሚ የመሰረተ ልማት ተቋማት በጥቂት ቀናት፤ ወይም ደግሞ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ የማውደም ዕኩይ
ተግባር ሲፈፅሙ እያየናቸው፤ከኢህአዴግ የተሻለ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የሚበጅ ነገር ለማምጣት እየታገሉ ነው ብለን እንድናምን
መጠበቁስ የንቀት ንቀት እንጂ ሌላ ምን ሊባል ይችላል…..? እያለን እርስበርሳችን የምንወያይበትን የጋራ መድረክ ስለመፍጠር አስፈላጊነት
ጉዳይ የሚያወሱ ነጥቦችን መጠቆም ተገቢ ይመስለናል፡፡
ይህን ስንልም ደግሞ እውን ሀገራችን ኢትዮጵያ ከህዳር
2008 ዓ.ም ጀምሮ እየተባባሰ ለመጣው የሰላምና መረጋጋት እጦት እንድትጋለጥ ያደረገው ዋነኛ ምክንያት የመልካም አስተዳደር ችግር
ነውን? ወይስ ይህን የመንግስት አቋም ፉርሽ የሚያደርጉ የተቃውሞው ጎራ ፖለቲከኞች ሰው ሰራሽ እክሎች ናቸው ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋታችንን
እንዲህ በአጭር ጊዜ ውስጥ አሳሳቢ አደጋ ላይ ሊጥሉት የቻሉት? የሚሉ ጥያቄዎችን እንደዋነኛ ማጠንጠኛ ነጥብ ወስዶ በግልፅ
መወያየት የተጋረጠብንን ወቅታዊ ፈተና ለማለፍና ችግሮቹን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚበጅ የመፍትሄ ሃሳብ ለማመንጨት የሚረዳ ጠቀሜታ
ሊኖረው እንደሚችል መጠቆሜ ነው፡፡
እናም ከዚህ አኳያ እንደ አንድ የድህረ ደርግ ኢትዮጵያን ፖለቲካዊ
ሂደት ከትላንት እስከ ዛሬ በቅርበት ከመከታተል ቦዝኖ የሚያውቅ ታዛቢ፤ ዛሬ ላይ ሀገራችንን ስለገጠማት ችግር የበኩሌን አስተያየት
መሰንዘር ካለብኝ የግል ምልከታዬን እነሆ እንደሚከተለው አሳጥሬ ለማስቀመጥ እሞክራለሁና አብረን እንመልከት፡፡ ማለትም፤ ከዚህ ቀደም
በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ የሚያጠነጥን መሰረተ ሃሳብ ባነሳሁባቸው መሰል መጣጥፎች ላይ ስር ነቀል የስርዓት ለውጥ ሂደቱን ለማስቀጠልና
ላለማስቀመጠል በሚፈልጉ ሁለት ዓይነት የፖለቲካ ሃይሎች መካከል እጅጉን የተለየ ጥንቃቄ የሚጠይቅ የአመለካከት ገመድ ጉተታ የሚስተዋልበት
አግባብ ስለመኖሩ ከጠቆም ተቆጥቤ እንደማላውቅ ሁሉ፤ ዛሬም ደጋግሜ ላስምርበት የምፈልገው ቁልፍ ነጥብ የቆየ እምነቴን የሚያጠናክር
ይሆናል፡፡
ስለዚህም በኔ እምነት፤መላው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና
ህዝቦች እንደ የአንድ ሀገር ህብረተሰብ ሀ ብለው ከጀመሩት ከ25 ዓመታት በላይ ያስቆጠረውን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ወደፊት ለማስቀጠል
የሚያደርገውን ጥረት በሚመራው ኢህአዴግና እንዲሁም ደግሞ ፌደራላዊ ስርዓቱን ዕውቅና ሊሰጠው አይገባም ከሚል ፅኑ አቋማቸው በሚመነጭ
ፅንፈኛ የፖለቲካ እሳቤ ዙሪያ እየተሰባሰቡ አዲሱን የታሪክ ምዕራፍ ለመቀልበስ ያለመ የአመፅ ሴራ ከመዶለት ለአንዲት ቀን ጀምበር እንኳን ቦዝነው የማያውቁት የተቃውሞው
ጎራ ሃይሎች የተያያዙት የአመለካከት ገመድ ጉተታ እየከረረ በመምጣቱ ምክንያት እንጂ ሌላ የተለየ ተዓምር ስለተፈጠረ አይደለም የአሁኑን
ሁከትና ግርግር ለማስተናገድ እተገደድን ያለነው፡፡ ስለዚህ ቀጥሎ መነሳት የሚኖሩበት ወሳኝ ጥያቄ ሆኖ የሚሰማኝ፤ስር ነቀል የስርዓት
ለውጥ ሂደቱን የመቀልበስ ዓለማ ይዘው በመንቀሳቀስ የሚታወቁት ተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎች ዛሬ ላይ ደርሰው ሀገሪቷን ለማተራመስ የሚያስችል የህዝብ ድጋፍ ያገኙ የመሰሉበት ሁኔታ ምንን ያመለክታል
? የሚለው ነው፡፡
ምንም እንኳን ለዚህ መሰረታዊ ጥያቄ የሚያጠግብ ምላሽ ለመስጠት
የሚያስችሉ ወቅታዊና በጥናት ላይ የተመሰረቱ ተጨማሪ መረጃዎችን ማግኘት እንደሚገባን ባያከራክርም፤ግን ደግሞ ከትላንት እስከ ዛሬ
አሳምረን ከታዘብነው የድህረ ደርግ ኢትዮጵያ ፖለቲካ አጠቃላይ ቅኝት በመነሳት ወደተጨባጩ እውነታ የቀረበ ምላሽ መስጠት የሚያዳግት
አይደለም ባይ ነኝ፡፡ምክንያቱም ከዚህ አኳያ ባፉት 25 ዓመታት የተጓዝንበትን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ለመቀልበስ ያለመ የተቃውሞው
ጎራ ፖሊቲከኞች እንቅስቃሴ ስርዓቱን በተደጋጋሚ የቅልበሳ ሙከራ ሲያንገራግጨው እንደቆየና ስርዓቱን ከመሰል የቅልበሳ አደጋ የመታደግ
አለመታደግ ጉዳይ በኢህአዴግ መራሹ መንግስት ጫንቃ ላይ የወደቀ ሸክም የመሆኑን ጥሬ ሀቅ አምነን እንድንቀበል ግድ የሚል ስለነበርም
ጭምር ነው ፡፡
እናም ስር ነቀል የስርአት ለውጥ ሂደቱን ካልታሰበ የቅልበሳ
አደጋ እየጠበቀ አጠናክሮ የማስቀጠል ታሪከላዊ ሃላፊነት የተሸከመው ኢህአዴግ መራሹ ሕገ መንግስታዊ ጫንቃ በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት
የመዛል አዝማሚያ ሲያሳይ የአመለካከት ገመድ ጉተታውን ከወዲያኛው ፅንፍ ወጥረው የያዙት የትምክህትና የጠባብነት ብሄርተኝነት ሃይሎች
በዚያው ልክ የመጎልበት ዕድል ይገጥማቸዋል፡፡ ስለዚህ አሁን መላውን ሰላም ወዳድ የህብረተሰብ ክፍል ዛሬም ነግቶልናል ስንል እየመሸብን
ይሆን እንዴ? የሚል ጥያቄ እንዲያነሳ እያስገደደው ያለውን ብርቱ ሀገር አቀፋዊ ስጋት የፈጠረው ወቅታዊ የፀጥታና የመረጋጋት መጓደል
ችግርም ከዚሁ የድህረ ደርግ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ የሃይል አሰላለፍ መገለጫ ሆኖ ከቆየው ነባራዊ ሀቅ የመነጨ እንጂ እንደዱብ ዕዳ
የሚቆጠር አዲስ ክስተት አይደለም የሚለው ነጥብ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
ይህ ከዛሬ 25 ዓመታት በፊት ጀምቶ ይስተዋል፤ የነበረና ከጊዜ
ወደ ጊዜ መልኩን እየቀያየረ የመጣ ፖለቲካዊ የአመለካከት ገመድ ጉተታ የሚገለፅበት ነባራዊ እውነታ እንደ ተጠበቀ ሆኖ፤ አሁን የቅልበሳ
አደጋውን ይበልጥ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እያደረሱት ያሉ ተጨማሪ ምክንያቶች ስለመበራከታቸው ግን መነጋገር የሚኖርብን ይመስለኛል፡፡
ከዚህ አኳያ አዲሱን የታሪክ ምእራፍ ወደ ፊት ለማስቀጠልና ላለማስቀጠል የሚፈልጉት ሃይሎች ሲያካሂዱት የቆዩትን ፖለቲካዊ የአስተሳሰብ
ገመድ ጉተታ ወደ መረረና ወደ ከረረ ጡዘት አሸጋግረውታል ሊባሉ የሚችሉት ዋና ዋና ነጥቦች ከሞላ ጎደል እንደሚከተለው ሊተነተኑ
ይችላሉ የሚል እምነት ነው ያለኝ ፡፡
ቀዳሚ ስፍራ ሊይዝ የሚገባው የኢትዮጵያን
የህዳሴ ጉዞ ለቅልበሳ አደጋ የሚያጋልጥ አሉታዊ ተፅእኖ ፈጣሪ ምክንያት፤ በተለይም የምዕራቡ ዓለም ባለፀጋ ሀገራትን ተተግነው የየራሳቸውን
የቅንጦት ህይወት እየኖሩ ያሉ አክራሪ ዲያስፖራ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች የሚያስተባብሩት እና በዋናነት “ፌስቡክ ” የተሰኘውን ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቅመው የሚያዛምቱት ውዝምብር ነው ቢባል ነባራዊ እውነታውን
በተሻለ መልኩ ሳይገልፀው አይቀርም፡፡ ይህን ስል ደግሞ ሻዕቢያ መራሹን የኤርትራ መንግስት ጨምሮ፤ ሌሎች ከእርሱ በስተጀርባ ሆነው ኢትዮጵያን ለማተራመስ
ከመዶለት ቦዝነው የማያውቁ እና አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም ሀገራት ቀለብ ይሰፍሩላቸዋል ተብሎ የሚነገርላቸውን ተቃዋሚ የፖለቲካ ሀይሎች
ጭምር ማለቴ እንደሆነ ግንዛቤ ይወሰደልኝ፡፡
ከዚህ አኳያ የለየለትን የሀገር ክህደት ተግባር ወደ መፈፀም እንደገቡ የሚያረጋግጥ ተጨባጭ መረጃ
እየቀረበባቸው ያሉት ኦ.ነ.ግ እና ግንቦት ሰባትን የመሳሰሉት የፀረ ኢትዮጵያ ሀይሎች ጉዳይ አስፈፃሚ ቡድኖች ለወቅታዊው የዚች
አገር ፖለቲካዊ ችግር መፈጠር የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስዱም ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡ ለአብነት ያህልም ባለፈው መስከረም 22
ቀን 2009 ዓ.ም የተከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ የተከሰተውን የፀጥታ መደፍረስ ችግር ተከትሎ አንዳንድ የግብፅ መገናኛ ብዙሃን
ሲዘግቡ የሰነበቱትን ዜና ማስታወስ ተገቢ ይሆናል፡፡ በተለይም ደግሞ ራሱን “የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ” እያለ የሚጠራው
ኦ.ነ.ግ መቸም ቢሆን ስለ ኢትዮጵያና ስለኢትዮጵያን የህዝቦች ዘላቂ ጥቅም ለመሳብ የሚያስችል ፖለቲካዊ ተፈጥሮ እንደሌለው በድጋሜ
ያረጋገጠበትን መግለጫ መስጠቱን ነው ሰሞነኛው የካይሮ መገናኛ ብዙሃን ዘገባ የሚያመላክተው፡፡
ለዚህ ደግሞ በግብፅ መዲና ኦ.ነ.ግ የጠራው ስብሰባ ላይ አንድ የግንባሩ አመራር “ብቻ እናንተ
የኢትዮጵያን መንግስት እንድናስወግድ እርዱን እንጂ ከዚያ በሁላ የህዳሴው ግድብ ግንባታ እንዲቋረጥና የአባይ ወንዝ ውሃ ጉዳይ ዳግም
እንዳይነሳ ማድረግ እንደማያቅተን እናሳያችሁ አለን”
ሲል በውይይት ተሳታፊ ለነበሩ ግብፃውያን ፖለቲከኞች ቃል መግባቱን አስመልክተው በርካታ የካይሮ ሚዲያዎች
መዘገባቸውን ማንሳት ይቻላል፡፡ እንዲሁም የአማራን ህዝብ እንወክላለን ከሚሉት የትምክህተኝነት ፅንፍ አቀንቃኝ ተቃዋሚ የፖለቲካ
ቡድኖች በኩል ተመሳሳይ ተስፋ እንደተሰጣቸው ጭምር ነው የካይሮ ሚዲያዎች
በቅብብሎሽ ሲዘግቡት ከሰነበቱት ዜና መረዳት የሚቻለው፡፡ እናም እዚህ አገር ቤት የሚስተዋለውን የሁከት ፈጠራ እንቅስቃሴ ከሰሞነኛው
የግብፅ ሚዲያዎች ዘገባ ጋር አያይዘን ስናይ ነው ሰላም እንደገና እያልን ለህብረተሰብ እንዘምር ዘንድ ግድ የሚል የማንቂያ ደወል
ከመቼውም ጊዜ በላይ ጎልቶ የሚሰማን፡፡ ስለዚህም እኔ የወቅቱ ብሔራዊ መዝሙራችን መሆን አለበት የምለውን ሰላም እንደገና የሚል
ዝማሬ እነሆ እንደሚከተለው ዘምሬ ላብቃ…
አሁን ያጠላብን፤ የስጋት ዳመና
ሁከት ግርግሩ፤ አይበጀንምና…
እንዘምር ዘምሩ፤ ሰላም እንደገና!
ለህገ መንግስቱ፤ ክብር ልዕልና
አብረን እንዘምር፤ ሰላም እንደገና!
ቁመናው ይደልድል፤ መሰረቱ ይፅና፡፡
የኢትዮጵያን ህዝቦች ሰላም እንደገና
ፍቅር ይስፈንብን፤ ልክ እንደ ካችአምና!!
No comments:
Post a Comment