Sunday, 1 January 2017

ተጠርጣሪዎቹ ዜጎች የህብረተሰቡ ሰላም ፋና ወጊ ሊሆኑ ይገባል!




                                                         ዘአማን በላይ
በኦሮሚያና በአማራ አንዳንድ አካባቢዎች በተቀነባበረ የጥፋት መረጃ ተመርተውና በስሜት ተገፋፍተው ወደ ሁከት ተግባር ለተሰማሩ ተጠርጣሪ ወጣቶች መንግስት የሰጠው የተሃድሶ ትምህርት ወደ ሰላማዊ ህይወት የመለሳቸው ነው። እነዚህ ዜጎች ቁጥራቸው 9 ሺህ 800 ሲሆኑ፤ በተሰጣቸው የተሃድሶ ትምህርት በህገ መንግስቱና በተለያዩ ጉዳዩች ዙሪያ ጠቀሜታ ያለውንና የህዝብን ንብረት ማውደም አግባብ አለመሆኑን መገንዘባቸውን ገልፀዋል—ተግባራቸውንም “አይደገምም” በማለት። ዜጎቹ ወደ መጡበት ማህበረሰብ ሲመለሱም የተማሩትን ትምህርት ለህብረተሰቡ እንደሚያስተምሩም አሳውቀዋል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አማካኝነት ኮማንድ ፖስቱ በቁጥጥር ስር አውሏቸው የነበሩት እነዚህ ዜጎች በተሃድሶ ስልጠናቸው ላይ አንድ ወር ከ10 ቀን የቆዩ ሲሆን፤ በቆይታቸውም ስለ ህገ መንግስት፣ ሃሳብን በሰላማዊ መንገድ በነፃነት ስለመግለፅ እንዲሁም ሀገራችን ውስጥ ስላለው የስራ ፈጠራ ጉዳይ ግንዛቤ እንዲጨብጡ ተደርጓል። በተሃድሶ ትምህርታቸውም ህገ መንግስቱ በሚፈቅደው መሰረት ተገቢው እንክብካቤና ድጋፍ ተደርጎላቸዋል። ይህም አዋጁ ዜጎችን ወደ ህግ የሚያቀርብ ብቻ ሳይሆን፣ አስተምሮም የሚለቅ መሆኑን በግልፅ የሚያሳይ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ አዋጁ ህግና ስርዓትን መሰረት አድርጎ የሚሰራ እንጂ በህግ ከተደነገገው ውጪ ምንም ዓይነት ተግባር ገቢራዊ እንደማያደርግ ያስገነዝበናል።
አዎ! አንዳንድ የሀገራችንን ገጽታ ትክክለኛ ባልሆነ መንገድ ለመተርጎም የሚሹ ፅንፈኛ ሚዲያዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከህግ አግባብ ውጭ ተግባሮችን እንደሚያከናውን በማስመሰል የሚያካሂዱትን አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ ሰሞነኛው ኮማንድ ፖስቱ አስምሮ ወደ መጡበት አካባቢ እንዲሄዱ ያደረጋቸው ዜጎች ሁነኛ ማረጋገጫ ይመስለኛል። እርግጥም አዋጁ ካገዳቸው ጉዳዩች ይልቅ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የእነዚህ ዜጎች ትምህርት ወስደው ወደ መጡበት መመለስና እነርሱ ያወቁትን ጉዳይ ላላለወቁ ወገኖች ለማሳወቅ ቃል መግባታቸው አመላካች ይመስለኛል። በእኔ እምነት በኮማንድ ፖስቱ አማካኝነት ተጠርጣሪ ዜጎቹ ወደ መጡበት መመለሳቸው ሁለት ጠቀሜታዎች ይኖሩታዋል። አንደኛው እነዚህ ዜጎች እንዳለፉት ጊዜያት በፀረ-ሰላም ሃይሎች የውሸት ፕሮፖጋንዳ ተታልለው የህዝብን ንብረት የሚታደጉ ከፍ ሲልም ሌሎች ወደ ተመሳሳይ ጥፋት ውስጥ እንዳይገቡ በማድረግ ረገድ የበኩላቸውን ሚና የሚጫወቱ ይሆናሉ። ሁለተኛው ደግሞ ዜጎቹ ህግና ስርዓትን በማወቃቸው ለወደፊቱ የሚያከናውኑት ማናቸውም ተግባራት የህግ የበላይነትን እንዲያሰከብሩና እንዲያስከብሩ ያደርጋል።
እነዚህ ጠቀሜታዎች ደግሞ ቀደም ሲል ወጣቶችን በማደናገርና በስሜት ማዕበል ውስጥ እንዲገቡ ያደርጉ የነበሩ አፍራሽ ቅስቀሳዎች ተፅዕኗቸው እንዲመናመን አሊያም ምንም ውጤት እንዳያገኙ የሚያደርጋቸው ይመስለኛል። ሰላምና መረጋጋትን በመፍጠርና ህብረተሰቡም በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ ይዞ የሰላሙ ጠባቂ ራሱ እንዲሆን ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።
በየትኛውም ሀገር ውስጥ እውን እንዲሆን የሚፈለግ ሰላም ያለ ህዝቡ ተሳትፎ ምንም ዓይነት ውጤት ሊያመጣ አይችልም። የሰላም ዋጋን ዋነኛ መዛኙ ኃይል ህዝብ ነው። ህዝብ ጥቅሙን የማያውቀው ሰላም ዕውን ሊሆን አይችልም። እርግጥም ለአንድ ሀገር ልማትና ዕድገት ሰላም ከምንም በላይ የገዘፈ ዋጋ ያለው መሆኑ አያጠያይቅም። ሰላም እንደ እውነቱ ከሆነ የሰላም ዋጋ በምንም አይነት ምድራዊ ዋጋ ሊለካ የሚችል አይመስለኝም።
ሰላም የሚተመንበት አሊያም የሚሰፈርበት ልኬት አለው ሊባል የሚችልም አይመስለኝም። ከግለሰብ የነገ ማንነት ህልም ጀምሮ እስከ የሀገር ህዳሴ ዕውን መሆን ድረስ ሰላም ዋጋው እጅግ የገዘፈ ነው። አዎ! የአንድ ሀገር ሰላም የህዝቧቿ ሰላም ነው። እናም ዜጎች መብትና ግዴታዎቻቸውን ሲያውቁና ሌላውን ለማስተማር ሲነሳሱ የሀገር ሰላም ይረጋገጣል። ልማትና ዕድገትም ይደረጃሉ፤ ዴሞክራሲያዊ እሴቶችም በዚያው መጠን እያበቡ ይሄዳሉ።
ተጠርጣሪ ዜጎቹ በአብዛኛው ወጣቶች ናቸው። እነዚህ ወጣቶች የነገዋ ኢትዮጵያ ተረካቢና ተስፋዎች ናቸው። የሀገራችን ትንሳኤ ፋና ወጊዎችም ናቸው። ፋና ወጊዎቹ የሀገራቸውን ሁለንተናዊ ገፅታ ማወቅ ይገባቸዋል። በምን ዓይነት መንገድ ተቃውሞም ሆነ ድጋፍ ማድረግ እንደሚችሉ፤ የትኛውንም ወገን መደገፍና አለመደገፍ ህገ መንግስታዊ መብታቸው መሆኑን ማወቅና የህገ መንግስቱን ሁለንተናዊ ገፅታ በመገንዘብ በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ድጋፍም ሆነ ተቃውሞ እንደምን ማካሄድ እንደሚኖርባቸው ይገነዘባሉ። ይህም ወጣቶቹን ከስሜታዊ ተግባር በማራቅ ህግና ስርዓትን ተገንዝበው ማናቸውንም ተግባሮቻቸውን  በዚያው ልክ እንዲከውኑ ያስችላቸዋል። የትኛውም አካል ከህግ በላይ ሆኖ ያሻውን ተግባር መከወን እንደማይችልም ተገንዝበዋል ብዬ አስባለሁ። ተጠርጣሪዎቹ የህዝቡ አካል እንደመሆናቸው መጠን ሰላማቸውን እንደ ማንኛውም ዜጋ በዕውቀት ላይ ተመርኩዘው እንዲጠብቁ ያደርጋቸዋል።
እርግጥ የሀገርን ሰላምና ደህንነት መጠበቅ የመንግስት ብቻ አይደለም—ዋነኛው ተዋናይ የሆነው የሀገራችን ህዝብ ጭምር እንጂ። አዎ! ህዝቡ በያለበት ሆኖ ሰላሙን ከጠበቀ ሰላምን ለማደፍረስ የሚሮጥ የትኛውም ሃይል አቅም ሊኖረው አይችልም። የሰላምን ምንነት የሚገነዘብ ህዝብ ውስጥ ፀረ ሰላምነትን ማንገስ አይቻልምና። እናም ህዝብ የሚጠቀምባቸውን ማንኛውንም ዓይነት ንብረቶችንና የግለሰቦችን ሃብት ለማውደም አይበቃም— ይጠብቃቸዋል እንጂ። ለፀረ ሰላም ሃይሎች ፕሮፖጋንዳ የማይፈታ የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል የዜጎች ንብረት በምንም ዓይነት መንገድ እንዲወድም አይሻም።
ወጣቶች እንደ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ መሆን ይሻሉ። ተጠቃሚነታቸውን ግን ማሳካት ያለባቸው በህጋዊና ህጋዊ መንገድ ብቻ መሆኑን ተጠርጣሪዎቹ ወደ ህብረተሰቡ ሲቀላቀሉ ማስተማር ይኖርባቸዋል። ሀገራችን ውስጥ ከተገኙት የልማት ውጤቶች አቅም በፈቀደ መጠን ተጠቃሚ መሆን አለባቸው። ሆኖም ተጠቃሚነታቸው ሊረጋገጥ የሚችለው በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ እንጂ ከሁከትና ከብጥብጥ አለመሆኑን ማወቅ ይኖርባቸዋል። በመሆኑም በተሃድሶ ትምህርት ቆይታቸው በቀሰሙት ትምህርት የህዝብን ሰላም በማወክ ተግባር ላይ የተሰማሩትንም ሆነ ሊሰማሩ የተዘጋጁትን ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ በማድረግ ረገድም ፋና ወጊ በመሆን የዜግነት ግዴታቸውን ሊወጡ ይገባል።
ሰላም ከሌለ ምንም ነገር ስለማይኖር በሰላም ጉዳይ መደራደር እንደማያስፈልግ ማሳወቅም ከተጠርጣሪ ወጣቶቹ የሚጠበቅ ተግባር ይመስለኛል። ሰላም ከሌለ ወጣቶቹም ይሁኑ ሌላው የህብረተሰብ ክፍል የሚመኘውን ተጠቃሚነት ዕውን ማድረግ አይቻልም። ሰላም ከሌለ ልማትንም ይሁን ዴሞክራሲን ማስፋትና ማረጋገጥ አይቻልም። ሰላም በሌለበት ሁኔታ ከእነዚህ መሰረታዊ መብቶች ባሻገር ዋነኛውና በህይወት የመኖር ዋስትና ሊኖር አይችልም። የሰው ልጅ በህይወት መኖር ካልቻለ ደግሞ ስለ ሌላው መሰረታዊ መብቶች ማሰብ ከጉንጭ አልፋነት የዘለለ ሚና ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም። እናም ተጠርጣሪ ወጣቶቹ ስለ ሀገራቸው ሰላም ይበልጥ ማሰብና መጨነቅ ያለባቸው ይመስለኛል።
እርግጥ ለዴሞክራሲ ግንባታም ሆነ ለልማት መጠናከር ወሳኝ የሆነውን ሰላምን በጋራ ለማቆም መንግስትን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሰላማዊ የውይይት ባህልን እየገነቡ መሄድም ይኖርባቸዋል። ለነገሩ በአሁኑ ወቅት መንግሥት፣ የፖለቲካ ሃይሎችና ህዝቡ በሰከነ መንገድ በመነጋገር እምብዛም ትኩረት ሳይሰጠው ከቆየው ሁኔታ ውስጥ እየወጡ ነው። ተጠርጣሪ ወጣቶቹ በጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተነጋግሮ የመስራት ባህላቸውን በቅድሚያ ራሳቸው በማስፋት ለጥቆም የሚኖሩበትን አካባቢ ማህበረሰብ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሊያስገነዝቡ ይገባል።
ምንም እንኳን ወጣትነት ትኩስነት ቢሆንም ይህ ትኩስነት ለሰላማዊ ተግባር መዋል ያለበት ይመስለኛል። እርግጥ ባለፉት ጊዜያት በአንዳንድ አካባቢዎች ወጣቱ ለመብቱ መከበር ያደረገውን ትግልና ያሰማውን ተቃውሞ ተገቢነት መንግስት መቀበሉና አክብሮቱንም መግለፁ ተገቢ ይመስለኛል። በመንግስት በኩል የነበሩ ችግሮች ግልፅ ናቸው። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ተጠርጣሪ ወጣቶቹ በኮማንድ ፖስቱ የተሰጣቸውን የተሃድሲ ትምህርት አጠናቀው ወደ መጡበት አካባቢ ሲሄዱ በስፍራው ተገኝተው እንደገለፁት፤ በመንግስት በኩል በነበረው የመልካም አስተዳደር ችግር ሳቢያ ለወጣቶች የሚፈለገውን ያህል ስራ መፍጠር አለመቻሉ ዋነኛ ጉዳይ መሆኑን ያሰመሩበትም ለዚሁ ይመስለኛል።
እርግጥ መንግስት ባለፉት ጊዜያት ወጣቶቹ ያነሱትን ጥያቄዎች ከፀረ ሰላም ሃይሎች ድርጊት ጋር ብቻ ጨፍልቆ ሳያልፈው በተሃድሶ መንፈስ ተግባራዊ ምላሽ መስጠት መጀመሩ ተገቢ ነው። የወጣቶቹ የተሃድሶ ትምህርትም የዚህ የመታደስና ራስን ተጠያቂ በማድረግ የሌላውን ችግርም የማሳየት አንዱ አካል ይመስለኛል። መንግስት በአሁኑ ወቅት እያከናወነ ያለው ተግባር የሀገሪቱን ሰላም ለማረጋጋጥም ሆነ የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ለማፋጠን ወሳኝ ርምጃ ተደርጎም ይወሰዳል። እናም ተጠርጣሪ ወጣቶቹ የዚህ ተሃድሶ ውጤት በመሆናቸው፤ በሚሄዱበት ቦታ ሁሉ ተግባራቸውን በፋና ወጊነት ተግባራቸውን ሊወጡ ይገባል እላለሁ።

No comments:

Post a Comment