በሣህለማርያም ገ/መድህን
የኢትዮዽያ
ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ እ.ኤ.አ ጁላይ 2013 ላይ የኢትዮጵያን የሕዝብ ብዛት በተመለከተ ባወጣው የትንበያ ሪፖርት መሠረት፤
እ.ኤ.አ በ2016 አጠቃላይ በሀገሪቱ ውስጥ ይኖራል ተብሎ ከተተነበየው 92‚000‚205‚000 (ዘጠና ሁለት ሚሊዮን ሁለት መቶ
አምስት ሺህ) ሕዝብ ውስጥ፤ 45‚000‚902‚000 (አርባ አምስት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሁለት ሺህ) አካባቢ የሚሆነውን የሕዝብ
ቁጥር የሚሸፍኑት ሴቶች ናቸው፡፡
ሴቶች
በቤታቸው፣ በአካባቢያቸው፣ በሀገርም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡ በመሆኑም የማኅበረሰቡ የጀርባ አጥንቶች ከመሆናቸውም
ሌላ ለቤተሰባዊም ሆነ ለሀገራዊ ዕድገት አስተማማኝ መሠረቶች ናቸው፡፡ የትኛውም ዓይነት የልማት እንቅስቃሴ ዕውን ሊሆን የሚችለውም
ሴቶችን ባሣተፈ እና እኩል ተጠቃሚነታቸውን ባረጋገጠ መልኩ ሲከወን ነው፡፡
ቀደም
ባሉት ጊዜያት በሀገራችን ለሴቶች ብዙ ሁኔታዎች ምቹ አልነበሩም፡፡ ንብረት የማፍራት፤ ከትዳር አጋራቸው ጋር ያፈሩትን ሀብት በጋራ
የመጠቀም፤ የመሬት ባለቤት የመሆን፤ በተለያዩ ማኅበራዊ መስተጋብሮች ላይ እኩል የመሳተፍ፤ እኩል የትምህርት እና የሥራ ዕድል የማግኘት፤
በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ የመሳተፍ፤ በተለያዩ የውሳኔ ሰጪነት ቦታዎች ላይ የመቀመጥ ወዘተ. መብታቸው ተገድቦ ቆይቷል፡፡ ሌላው
ቀርቶ ከአጠቃለይ የኅብረተሰቡ ቁጥር ልቀው የሚገኙት ሴቶች ለዘመናት ለትምህርት ዓለም እንግዳ ሆነው ኖረዋል፡፡ በዚህ ፋንታ ባሎቻቸውን
እና ቤተሰቦቻቸውን በመንከባከብ እና በቤት ውስጥ በተገደቡ ሥራዎች ላይ ብቻ ተወስነው መኖራቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
በኢፌዴሪ
ሕገ መንግሥት አንቀጽ 35 ንዑስ አንቀጽ 3 ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው፤ ሴቶች በበታችነት እና በልዩነት በመታየታቸው የደረሰባቸውን
የታሪክ ቅርስ ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ቅርስ እንዲታረምላቸው በተጨማሪ የድጋፍ እርምጃዎች ተጠቃሚ የመሆን መብት አላቸው፡፡
በዚህ በኩል የሚወሰዱት እርምጃዎች ዓላማ በፖለቲካዊ፤ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስኮች እንዲሁም በመንግሥት እና በግል ተቋሞች
ውስጥ ሴቶች ከወንዶች ጋር በእኩልነት ተወዳዳሪ እና ተሣታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ እንዲቻል ልዩ ትኩረት ለመስጠት ነው ሲል ተደንግጓል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 10፣ 16፣ 17፣ 18፣ 25 እና 32 ላይ በሴቶች ላይ የሚደርሱ የኃይል ተግባራትን ቀጥተኛ ባልሆነ መልኩ የሚከለክሉ አንቀፆች ተካተዋል፡፡ ይህም የሴቶች ሁለንተናዊ
መብቶች ሙሉ ለሙሉ መከበር እንደሚኖርበት አጽንዖት የሚሰጥ ነው፡፡
የኢትዮጵያ
የሽግግር መንግሥት በተመሠረተበት ማግሥትም በ1985 ዓ.ም የሥርዓተ ፆታ እኩልነት እንዲኖር የሚያስችል ፖሊሲ ተዘጋጅቶ በሥራ ላይ
ውሏል። ፖሊሲው በወንዶች እና በሴቶች መካከል የፆታ እኩልነት እንዲኖር የሚያስችሉ አመቺ ሁኔታዎችን የመፍጠር፤ ሴቶች በፖለቲካ፣
በኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ኑሮ እኩል ተሣትፎ እና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ፤ ሴቶች ከወንዶች እኩል ሀብት የማፍራት እና የመያዝ፣
የመጠቀም እንዲሁም የማንኛውንም ሰብዓዊ መብት ተጠቃሚ እና ውሳኔ ሰጪነት ተግባር ላይ ተሣታፊ እንዲሆኑ የማድረግ ዓላማን ያካተተ
ነው፡፡
ከዚህም
በላይ ሥራ ላይ የዋሉት የሥነ ሕዝብ፣ የትምህርት፣ የጤና፣ የባህል እና ሌሎችም የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ፖሊሲዎች ሴቶችን፣ ሕፃናትን
እና ወጣቶችን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ እንዲዘጋጁ እና ተግባራዊ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ እነዚህን ፖሊሲዎች ተግባራዊ ለማድረግ
የሚያስችሉ አደረጃጀቶችም በፌዴራል እና በክልሎች እንዲሁም በከተማ አስተዳደሮች ተፈጥረዋል፡፡ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ሥራ ላይ
እንዲውል ተደርጓል። ከዚህ በተጨማሪ የሀገሪቱ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ በማሻሻል በሴቶች ላይ የሚደርሱ በደሎችን እና ጾታዊ ጥቃቶችን
ለመግታት በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ የሴቶች ስምምነት (CEDAW) በአንቀጽ 10 ላይም ስምምነቱን የፈረሙ/ የተቀበሉ ሀገሮች ሴቶች በትምህርት መስክ ከወንዶች እኩል መብቶች እንዲኖራቸው
ለማድረግ እና ማንኛውንም ዓይነት አድሎአዊ ልዩነት እንዳይደረግባቸው ለማረጋገጥ ተገቢ የሆኑ እርምጃዎችን ሁሉ እንዲወስዱ ይደነግጋል፡፡
የትምህርት
እና የጤና አገልግሎት በመላው ሀገሪቱ በመስፋፋት የሴቶችን ተሣትፎ ለማበረታታት እና ተጠቃሚ ለማድረግ ተችሏል፡፡ በሕግ አውጪ፣
አስፈጻሚ እና ተርጓሚው የሥራ መስክም የሴቶች ተሳትፎ እንዲበረታታ ተደርጓል፡፡ በዚህም ረገድ በየደረጃው በተቋቋሙ ምክር ቤቶች
እና አስፈጻሚ አካላት የሴቶች ስብጥር እያደገ እንዲሄድ አስፈላጊው የፖሊሲ እና አስተዳደራዊ እርምጃዎች በመወሰዳቸው አመርቂ ውጤቶች
ሊመጡ ችለዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የሕግ አውጪ በሆነው በሕዝብ ተወካዮች ምክር በት የሴቶች ተሣትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣት
በአምስተኛው የምርጫ ዘመን የሴቶች ተሣትፎ ወደ 30 በመቶው ሊደርስ ችሏል።ይህም የኢፌዴሪ መንግሥት ሴቶችን ለማብቃት እና እኩል
ተጠቃሚ፣ ውሳኔ ሰጪ ለማድረግ እያደረገ ያለውን ጥረት ያሳያል።
ለበርካታ
ዘመናት ታፍነው ከኖሩበት አስከፊ ሥርዓት ነፃ በመውጣታቸው፤ የሀገራችን ሴቶች አሁን አሁን ከአርሶ/አርብቶ አደርነት ሕይወት በመውጣት በሴቶች አይሞከሩም፤
አይታሰቡም በሚባሉት ዘርፎች (የሕዝብ
መሪ፣ አውሮፕላን አብራሪ ፣ የኮንስትራክሽን ባለሙያ፣ አርቲስት፣ ሐኪም፣ ዲፕሎማት፣ ቴክኒሻን፣ ጋዜጠኛ፣ ስኬታማ የቢዝነስ ሰው፣ መሃንዲስ፤ ወታደር…) ውስጥ ሴቶችን ማየት
እየተለመደ መጥቷል፡፡ በከተማም ሆነ በገጠር
አካባቢ የሚከናወኑ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፎች የሴቶችን ተሣታፊነት እና ተጠቃሚነትን ያጠናከሩ፤ ያረጋገጡ እና መሆን የሚፈልጉትን
ነገር ማድረግ እንደሚችሉ ያሳየ ሐቅ ነው፡፡ በርካታ ሴቶች በንግድ ዘርፍ ተሠማርተው ሀብት አፍርተዋል፤ በኃላፊነት ወንበር ላይ ተቀምጠው ድንቅ ብቃታቸውን አስመስክረዋል፤በፖለቲካው ጉዳይ ተሣታፊ ሆነው
መሥራት እንደሚችሉ አሳይተዋል፤ በውድድር ስፖርቶች የሀገር ሠንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ በማድረግ ዓለም በአንድ ላይ ቆሞ
እንዲያጨበጭብ አድርገዋል፡፡
በዚሁ
በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 01 አስተዳደር በተለምዶ አለርት ሆስፒታል በሚባለው አካባቢ አካል
ጉዳተኛ ሴቶችን አሣታፊ ያደረገ ትልቅ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ የዶሮ እርባታ ሥራ፡፡ በዚህ ሥራ ላይ ሀምሳ የሚሆኑ ጉዳተኛ
ሴቶች ተሠማርተው ይገኛሉ፡፡ ሴቶቹ በአካባቢው ለረጅም ጊዜያት የቆዩ ሲሆኑ፤ ጎዳናን ቤቴ፤ ልመናንም መተዳደሪያዬ ብለው ይኖሩ የነበሩ
ናቸው፡፡
እነዚህ
ጉዳተኛ ሴቶች ባለፈው ሥርዓት ከተለያዩ ክልሎች ሕክምናቸውን ለመከታተል የመጡ ሲሆኑ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ መጡበት አካባቢ
ለመመለስ ባለመቻላቸው በዚሁ ስፍራ የሰው እጅ እየተመለከቱ ለዘመናት ኖረዋል፡፡ ሆኖም በአሁኑ ጊዜ ሴቶቹ መንግሥት ለዜጎች በዘረጋው
ምቹ ሁኔታ በመጠቀም እጅግ አስከፊ ከሆነው የልመና ሕይወት ለመላቀቅ ችለዋል፡፡
ለዚህ
መልካም ውጤት ማሳያ ከሚሆኑት አንዷ ወ/ሮ አልማዝ ደርሰህ ይባላሉ፡፡ የአካል ጉዳተኛ እና የሦስት ቤተሰብ አስተዳዳሪ ናቸው፡፡
እኒህ ሴት ለረጅም ጊዜያት በልመና ሕይወት መቆየታቸውን ይናገራሉ፡፡ በልመና በሚያገኙት ገቢም ሁለት የዘመድ ልጆችን ያሳድጋሉ፡፡
ወ/ሮ አልማዝ ዓይናቸው እንባ እያቆረዘዘ የኖሩበትን ሕይወት ሲያስታውሱ ያንገሸግሻቸዋል፡፡ በልመና ሥራ ላይ ከሦስት አስርት ዓመታት
በላይ ቆይተዋል፡፡ እጅና እግራቸው ጤነኛ በመሆኑ ወዲያ ወዲህ ብለው እና የሰው ቤትም ተቀጥረው ለመሥራት ፍላጎቱ እንደነበራቸው
ይናገራሉ፡፡ ሆኖም በከንፈራቸው ላይ ባለው የአካል ጉዳት ምክንያት ሰዎች ይጸየፏቸዋል፣ ያገሏቸዋል፣ ቀጥረው ለማሠራትም ፊታቸውን
ያዞሩባቸዋል፡፡ በመሆኑም እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው ለመሥራት እና ቤተሰባቸውን ለመደገፍ አልቻሉም ነበር፡፡
በዚህም
የተነሳ ወ/ሮ አልማዝ በጣም ብዙ እንቅልፍ አልባ ሌሊቶችን አሳልፈዋል፡፡ ይህ ተግባር እሳቸው ብቻ አልነበረም፤ በሥራቸው ያስተዳድሯቸው
የነበሩት ቤተሰቦቻቸውም ጭምር እንጂ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በልመና ሥራ ሕይወታቸውን እስከመቼ እንደሚገፉት፣ የቤተሰባቸውን መሠረታዊ
ፍላጎት መቼ እንደሚሞሉት፣ የሚያሳድጓቸው ልጆች መቼ ከሰው እኩል እንደሚሆኑ፣ ለማኝ የሚለውን ስም ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ መቼ
ከሕይወት መዝገባቸው ላይ እንደሚፍቁት በመጓጓታቸው ነው፡፡ ግን እንዴት? መቼ?
ይህ
ጥያቄ በወ/ሮ አልማዝ ቤተሰብ ጭንቅላት ውስጥ ለብዙ ዘመናት ቢመላለስም መልሱ ሊገኝለት ያልቻለ ጥያቄ ነበር፡፡ ሆኖም አንድ ቀን በዚያው በልመና ላይ እንዳሉእነ
ወ/ሮ አልማዝን ሰዎች ጎበኟቸው፡፡ ከዚያም ለምን አትደራጁም የሚል ጥያቄም አያይዘው አቀረቡላቸው።
የአካል
ጉዳተኛ ሴቶቹ የነበረው ምላሽም በማን ዕድል የሚል ሆነ፡፡ ከዚህ በኋላ ፕሮጀክቱ ተነድፎ ለመንግሥት የድጋፍ ጥያቄ የቀረበ ሲሆን፤
በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የወረዳ 01 አስተዳደርም በማይክሮ ፋይናንሱ በኩል ለ50ዎቹ በልመና የሚተዳደሩ አካል ጉዳተኛ ሴቶች
ሥራ ሕጋዊ ዕውቅና እና ፈቃድ እንዲያገኝ አድርጓል፡፡ መንግሥትም ዛሬ ነገ ሳይል አራት ትልልቅ ሼዶችን በክፍለ ከተማው ወረዳ
7 አካባቢ አዘጋጀላቸው፡፡ ሥራችሁን በፍጥነት ጀምሩ ብሎም መርቆ ሠጣቸው፡፡
ቀን
ተቆርጦም በአግሮ ኢንዱስትሪ በተለይም በዶሮ ሀብት ልማት ላይ ሥራውን ባተኮረ ተቋም የክህሎት ሥልጠና ተዘጋጀ፡፡ ከሥልጠናው በተጨማሪ
ቃሊቲ አካባቢ በሚገኝ አንድ ትልቅ የዶሮ እርሻ ልማት ውስጥ ተግባር ተኮር ልምምድ ተካሄደ፡፡ ይህም ለ 50ዎቹ የጎዳና ተዳዳሪ
ሴቶች የወደፊት ራዕይ ማሳኪያ መክፈቻ ቁልፍ ነበር፡፡ ዕውን እኛ ሥራ ልንሠራ?! ዕውን እኛ ከልመና ሕይወት ልንወጣ?! ሕውን እኛ
ለልጆቻችን ለቤተሰቦቻችን ትኩስ እንጀራ ልናበላ?! ሌላም ሌላም የደስታ ሲቃ ያረገዘ የሕሊና ጥያቄ በሁሉም ዘንድ ተመላለሰ፡፡ ግን
የሕሊና ጥያቄው የህልም ሳይሆን የዕውን ነበር፡፡
መንግሥት
ለእነዚህ ሴት ጉዳተኛ ዜጎች ፈጣን ምላሽ ሰጥቶ የአራት ትልልቅ ሼዶች ቦታ ከተገኘ በኋላ ከአግሮ ኢንዱስትሪው ጋር በመነጋገር ዶሮዎች፣
ለዶሮ እርባታው የሚያገለግሉ ግብዓቶች እና የመኖው አቅርቦት ሊሟላ ቻለ፡፡ ሙያዊ የሆነ ሥልጠናም ተመቻቸ፡፡ በአስተባባሪው ገለጻ
መሠረት በሁለቱ ሼድ ውስጥ የተደራጁት እያንዳንዳቸው 12 በድምሩ 24 ሴቶች ሲሆኑ፤ በሌላኛው ሁለት ሼዶች ውስጥ ደግሞ እያንዳንዳቸው
13 በድምሩ 26 ሴቶች እንዲደራጁ ተደርጓል።
ይህም
ብቻ አይደለም ሴቶቹ ሥልጠናው ከተሰጣቸው እና ሥራው ከተጀመረ በኋላ ከአግሮ ኢንዱስትሪው በተመደበ ባለሙያ የሥራ ላይ እንቅስቃሴያቸው
ይገመገም ነበር፡፡ ሼዱ በሚገኝበት ወረዳ 7 የሚገኙት የወረዳው የከተማ ግብርና ባለሙያዎችም ተገቢውን የቴክኒክ ድጋፍ አድርገውላቸዋል፡፡
የወረዳ
7 እንስሳት እርባታ ባለሙያ የሆኑት አቶ ኃ/ማርያም በዚህ የጉዳተኛ ሴቶች ተደራጅተው ባቋቋሙት የዶሮ እርባታ ላይ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡
በአንዱ ሼድ ውስጥ በሣምንት ለሦስት ቀናት ተገኝተው አስፈላጊውን ሙያዊ አስተዋጽዖ እያደረጉ ሲሆን፤ በሌሎቹም ሼዶች ውስጥ ሌሎች
ባለሙያዎች እየሠሩ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ በዚህም ሙያዊ እገዛዎችን እና የልምድ ማስተላለፍ ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል፡፡ ሌሎች
ባለድርሻ አካላት ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ ሴቶቹ በተደራጁበት ወረዳ በተያዘ በጀት ሙያዊ ሥልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡
እንደባለሙያው
ገለጻ ሴቶቹ ሥራውን ከጀመሩ ጥቂት ጊዜ ቢሆንም፤ ከዶሮ ርባታው የሚያገኙትን አጠቃላይ የዕንቁላል ምርት ሊያሳድጉ ችለዋል፡፡ በሂደትም
ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ለማድረግ
ከፍተኛ ዕገዛ እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በየቀኑ የሚመረቱትን እንቁላሎች እየመዘገቡ ለተገቢው አላማ እንዲያውሉና
ራዕያቸውን እንዲያሳኩ ተገቢው የምክር አገልግሎት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ሌላዋ
የማኅበሩ አባል ወ/ሮ ደመቁ ምስኬ ሲሆኑ፤ እንደሌሎቹ አጋሮቻቸው ሁሉ የሥጋ ደዌ ተጠቂ ናቸው፡፡ ወደዚህ ሥራ ከመግባታቸው በፊት
በልመና ሥራ ይተዳደሩ ነበር፡፡ አንዲት ሴት ልጅም አላቸው፡፡ በዶሮ ልማቱ ሥራ ተጠቃሚ እየሆኑ በመምጣታቸው መንግሥትን በከፍተኛ
ሁኔታ እንደሚያመሰግኑ ይናገራሉ፡፡ እሳቸው ባሉበት ሼድ ውስጥ የሚገኙትን ዶሮዎች ከሌሎች አባላት እና የእንስሳት ባለሙያው ጋር
በመሆን በከፍተኛ ሁኔታ እንክብካቤ በማድረግ ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ በየስድስት ቀናቱ ሁለት ሁለት ሆነው ለ24 ስዓታት ይሠራሉ፡፡
ሥራቸውም በቡድን መንፈስ እና በከፍተኛ ሞራል እንደሆነ ወ/ሮ ደመቁ ይናገራሉ፡፡
ወ/ሮ
የሺመቤት ጌታሁንም በዚሁ ማኅበር ተጠቃሚ ከሆኑት መሃል ናቸው፡፡ ራሳቸውን ጨምሮ የአራት ቤተሰብ አስተዳዳሪ ናቸው፡፡ እሳቸው በሚገኙበት
ሼድ ውስጥ የሚገኙት ዶሮዎች እንቁላል በመጣል ጀምረዋል። ወ/ሮ የሺመቤት እንደሚሉት "የዘመናት አስቀያሚ ሕይወታችን ትንሳዔ
አግኝቷል፤ የልፋታችንን ውጤት እያገኘን ነው። ሰው የዘራውን አይደል የሚያጭደው!! ለዘመናት የሰው እጅ በመጠበቃችን ድህነትን እና
የበታችነትን አጭደናል፤ ዛሬ ደግሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዶሮዎችን ተንከባክበን በመቶዎች የሚቆጠሩ እንቁላሎችን አምርተናል፤ ነገ ደግሞ
ይህንን የመቶ ዘር በሺህ ለመተካት እንቅልፍ አይዘንም!! የነብርን ጭራ አይዙም ከያዙም … አይደል የሚባለው"፡፡
በጥቅሉ
ለመናገር እነዚህ ሴቶች በሥራቸው ውጤታማ፣ አምራች፣ ሥራ ወዳዶች ሆነዋል፤ የቤተሰቦቻቸውንም ሕይወት ለመለወጥ ችለዋል፡፡ በመሆኑም
"ሴቶች እኮ አይችሉም" የሚለውን የተሳሳተ አባባል ሰብረዋል፡፡ የለውጥ ሐዋርያ የሆኑት እነዚህ ሴቶች በመሥራታቸው
ውጤት ማምጣታቸውን አስመስክረዋል፡፡
ሁሉም
ሴቶች በአንድ አቋም ይስማማሉ፡፡ የልመና ሥራ አስከፊ ነው፤ የልመና ሥራ አዋራጅ ነው፤ የልመና ሥራ የበታች አድራጊ ነው፤ የልመና
ሥራ የሰውን ፊት እንደ እሳት ይገርፋል፡፡ ልመና ማለት……፡፡ ይህን አስፈሪ እና ክፉ ሕይወት ዳግም ላናየው ተሰናብተነዋል፡፡ አሁን
ሀሳባችን ምን እንበላ ይሆን? ምን እንለብስ ይሆን? ለልጆቻችን ትምህርት ቤት ምናችንን እንከፍል ይሆን? አይደለም፡፡ ያለንን ሀብት
እንዴት እንምራ? እንዴት እናሳድግ? ነው፡፡ ታዲያ ለእንደዚህ አርአያነት ላለው ተግባር ከመንግሥት ጥረት በተጨማሪ የሚመለከተው
ሁሉ የበኩሉን ቢያደርግ በርካታ ዜጎችን ከልመና ሥራ በማውጣት አምራች ዜጋ ማድረግ ይቻላል። ስለዚህ የወገን መለወጥ የእኔ እና
የሀገር መለወጥ ነው ብሎ የሚያምን ዜጋ ሁሉ ለእንደዚህ ዓይነቱ አበረታች ተግባር የበኩሉን ይወጣ እያልሁ ሀሳቤን እቋጫለሁ።
No comments:
Post a Comment