Sunday, 1 January 2017

ርዕዩተ-ዓለም መራሹ ጫጫታ




                                                    ቶሎሳ ኡርጌሳ
ራሳቸውን በሰብዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ታዛ ስር ጠልለው የሚንቀሳቀሱ የምዕራቡ ዓለም ፅንፈኛ የኒዮ ሊበራል ተቋማት በሀገራችን ላይ የሚሰነዝሩት የተለያዩ ስሞታዎችና አሉባልታዎች ጋብ ያለበትን ጊዜ አላስታውስም። ፅንፈኛ ተቋማቱ መነሻው ምንም ሆነ ምን አንድ ጉዳይ ሲሰሙ ከያሉበት ጎሬ ብቅ እያሉ ተከታታይነት ባለው ዘመቻ መልክ የሀገራችንን ገፅታ ጥላሸት ለመቀባትና የጀመርነውን የልማት ተምሳሌት መስመር ለማጥላላት የማይቆፍሩት ጉድጓድ የለም። እነዚህ አክራሪ ኒዮ ሊበራል ሃይሎች ስማቸውን ‘አምንስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂዮማን ራይትስ ዎች፣ ሲፒጄ…ወዘተ’ እያሉ ስማቸውን ይቀያይሩ እንጂ ፍላጎታቸውም ይሁን ማንነታቸው አንድ ነው። በአንድ ዓይነት ቋንቋና በአንድ ዓይነት ፍላጎት የነቀፌታ በትራቸውን ይሰነዝራሉ፤ በጫጫታ መልክ ክሳቸውን ይደረድራሉ። እናም በዚህ ፅሑፌ የእነዚህን ፅንፈኛ ኒዮ-ሊበራል ሃይሎች ፍላጎትና ማንነት ለመቃኘት እሞክራለሁ።
እንደሚታወቀው አክራሪ ኒዮ-ሊበራሎቹ የሚያቀነቅኑት የኒዮ ሊበራሊዝም ፖለቲካል- ኢኮኖሚ ስርዓት ህግና ስርዓትን ከማስከበር ውጭ በኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ፍጹም ጣልቃ እንዳይገባ የሚከለክል ቀመር ያለው ነው። ሁሉንም ነገር ለባለ ሃብቱና ለገበያው የሚሰጥ መረን የለቀቀ ፍልስፍና መሆኑም እውነት ነው። እነርሱ የሚዘምሩለት ቀመር ሚሊዮን ድሆችንና ጥቂት ቱጃሮችን የፈጠረ መሆኑ ማንም የሚገነዘበው ይመስለኛል። እናም የእነርሱ ስርዓት መንግስት ዳር ቆሞ ጥርሱን ከመንከስ በስተቀር ምንም እንዳያደርግ ያስገድዳል። ይህ አስገዳጅነትም በዓለም ላይ ሁሉ እውን እንዲሆን ጽንፈኛ ሃይሎቹ ተግተው ይሰራሉ። የኒዮ ሊበራሊዝም ፍልስፍና ግን ከሁሉም ሀገራት ጋር አብሮ አሄድም።
በተለይም በአፍሪካ ውስጥ ለአራት አስርት ዓመታት ያህል ተሞክሮ ያልሰራ አስተሳሰብ ነው። በዚህም ሳቢያ ዛሬ ላይ አፍሪካዊያን ኒዮ -ሊበራሊዝምን በመቃወም የራሳቸውንና ከታሪካቸው፣ ከባህላቸውና ከነባራዊ ሁኔታቸው ጋር የሚጣጣም የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመዘርጋት ተገደዋል። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራትም ውጤታማ እየሆኑ ነው። አክራሪ ኒዮ-ሊበራሎችን የሚያስቆጣቸውና በየወቅቱ በጫጫታ መልክ ሪፖርት እንዲያወጡ የሚያደርጋቸውም ይኸው በራስ አስተሳሰብ የመመራትና እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት የኒዮ-ሊበራሊዝምን አስተሳሰብ ‘እንደ ወረደ’ ሳይቀበሉ በራሳቸው መንገድ ልማታቸውን ማሳለጣቸው፣ ለሌሎች ታዳጊ ሀገሮችም ምሳሌ መሆናቸው ነው።
እርግጥ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት የሚከተሉት ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመ ርዕዮተ ዓለም የባህር ማዶ ከበርቴዎችን መዝባሪነት የሚፈቅድ አይደለም። የታዳጊ ሀገራትን ህዝቦች ርካሽ ጉልብትና ድንግል መሬት እንዲሁም የተትረፈረፈፊ ማዕድን ለመዛቅ ምቹ መደላድሎችንም አይፈጥርም። ታዲያ ይህን ለህዝብና ለሀገር የሚወግን አስተሳሰብ ኒዮ ሊበራሎቹ አይወዱትም። አዎ! እነ አምንስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂዮማን ራይትስ ዎችና ሲፒጄን የመሳሰሉ አክራሪ የርዕዩተ ዓለም አራማጆች በኒዮ -ሊበራሊዝም አገልጋይነታቸው አይወዱትም—ይህን የታዳጊ ሀገራትን አካሄድ። የሚያመጡት ለውጥ ባይኖርም፤ የርዕዮተ ዓለሙን ልዕልና የበላይነትን ለማንገስ የመግለጫ ጫጫታቸውን ይዘረጋሉ።
የጫጫታው መንገድ ግን ቀጥተኛ አይደለም። ተዘዋዋሪ ነው— በዘመናዊ እጅ አዙር የቅኝ አገዛዝ ዘዴ። ይኸውም ርዕዮተ ዓለሙን የሚያቀነቅኑ፣ ነገር ግን በስም እንደ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ዓይነት መብቶችን በመልካምነት ስያሜ የታጠቁ ዘማቾችን በታዳጊ ሀገራት ላይ እንዲሰማሩ ተደርጓል። የእነዚህ ሃይሎች ዋነኛ መገልገያዎች በየሀገሩ ያሰማሯቸው ተቃዋሚዎችና ሲቪክ ማህበራት ናቸው። እነዚህ ማህበራት በሀገሪቱ ውስጥ እንዳሻቸው እንዲፈነጩም የውጭ ድጋፍ በመስጠት በቀጥታና በተዘዋዋሪ የእነርሱ ምንደኛ እንዲሆኑ ያደርጓቸዋል። ይህን ሃቅ ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር ለማያያዝ ምርጫ 97ትን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።
እንደሚታወቀው በምርጫ 97 ወቅት የክርስቲያን ተራድኦ ድርጅቱ (CRDA) አመራር ሆነው ውስጥ ለውስጥ ግን ሂዩማን ራይትስ ዎችን ለመሳሰሉ አክራሪ ኒዮ-ሊበራል ሃይሎች ሲሰሩ እንደነበሩትና ዛሬ ያ ውለታቸው ታይቶ የአክራሪው ተቋም የምስራቅ አፍሪካ ክፍል አመራር ለመሆን የበቁት አቶ ዳንኤል በቀለ ሲያደርጉት እንደነበረው የነውጥ ጥረት ዓይነት ዕውን እንዲሆን ይሻሉ።
እነ አቶ ዳንኤል ያኔ የጎዳና ላይ ነውጥ አቀጣጣይ የነበረውን ቅንጅት የተሰኘ ጽንፈኛ ተቃዋሚን ሲደግፉ እንደነበር ይታወቃል። ይህ ሁኔታቸውም በሀገራችን የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ አክራሪ ኒዮ ሊበራሎች በተዘዋዋሪ እንዲገቡና የቀለም አብዮትን ለማራመድ ዕድል ፈጥሮላቸው እንደነበር አይዘነጋም፤ ህግና ስርዓትን በማስከበር ሂደት ፍላጎታቸው ሳይሳካ ቀረ እንጂ። ታዲያ ይህ በሀገራችን ላይ የታየ ተጨባጭ ዕውነታ የአክራሪ ኒዮ-ሊበራሎቹ ፍላጎት ምን ያህል በርዕዩተ-ዓለም ፍላጎት ላይ የተመረኮዘ መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል።  
በእኔ እምነት የዚህ ሁሉ የአክራሪ ኒዮ ሊበራል ሃይሎች ርብርብ ርካሽ ጉልበት፣ ያልተበላ ድንግል መሬትና የተፈጥሮ ሀብትን ከታዳጊ ሀገራት የመመዝበር ሱስና በሰው ሃብት የመበልፀግ ህልም ነው። በዚህም ሳቢያ ለመልማትና ለመንቃት የሚወተረተሩ ህዝቦችን ለመደፍጠጥ ተኝተው አያድሩም። የለማና የሰለጠነ ህዝብ ለመገዛት ስለማያጎነብስ ያን ስጋት ከወዲሁ ለማምከን ይዋትታሉ።
ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ታዳጊ ሀገራት እያስመዘገቡት ያለው ፈርጀ ብዙ የልማት እመርታ፤ ካረጀ ካፈጀው የፖለቲካ ንግዳቸው ጨርሶ ስለሚያወጣቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና የአካባቢ ጥበቃ ወይም ተቆርቋሪነት ጭንብልን አጥልቀው ፕሮጀክቶችንና የልማት ስራዎችን ያውግዛሉ። ያልታሰሩ ጋዜጠኞችን ታስረዋል በማለት ከእኛ ኢትዮጵያዊያን በላይ ለኢትዮጵያዊያን ተቆርቋሪ በመምሰል ደረታቸውን ይደቃሉ። የአዞ እምባቸውን ያነባሉ።
ኢትዮጵያ ለሌሎች ሀገራት ተምሳሌት እንዳትሆን ያላቸውን ድብቅ ፍላጎት “የሆዴን በሆዴ” በማለት በውስጣቸው በመያዝ “ይህች ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም” ይላሉ። ከቻሉም የቀለም ወይም የፍራፍሬ ምናምን አብዮት በማቀጣጠል ታዳጊ ሀገራትን ለመለብለብና ለማስለብለብ ይተጋሉ። ይህን የሚያደርጉበት ነባራዊ ምህዳር በሀገራት ውስጥ ከሌለ ደግሞ የሀገራቱን መልካም ገፅታ በቅጥፈት በሚለውሱት የኒዮ ሊበራሊዝም አስተሳሰብ አቀንቃኞች አማካኝነት ታዳጊ ሀገራትን ከለጋሽ ሀገራትና ተቋማት ጋር ለማቆራረጥ አቅደው ይሰራሉ፤ ይማፀናሉ፤ ይማልዳሉ። የእነርሱ አልፋና ኦሜጋ ፍላጎት መቋጫም ይኸው ነው።
እነዚህ አክራሪ ኒዮ ሊበራሎች “ከእኛ ርዕዩተ-ዓለም ውጪ ማደግ አይቻልም” የሚለውን እሳቤያቸውን ዕውን ለማድረግም ታዳጊ ሀገራት ካንገታቸው ቀና ማለት ሲጀምሩ ጭንቅላታቸውን በመግለጫ ጫጫታ ሊኮረኩሟቸው ይሻሉ። ይህን ፍላጎታቸውን ገቢራዊ ለማድረግም ባህር ማዶ ተቀምጠው የታዳጊ ሃገራትን የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ሃብት፣ ማዕድናትና ርካሽ የሰው ጉልበት ለመመዝበር የሚያስችል ምቹ ፖለቲካዊ አውድ አንዲኖር አብዝተው ይቋምጣሉ። እናም በግብራቸው አንድ፣ በስማቸው ግን የተለያዩ የሆኑ  ፀረ-ታዳጊ ሃገራት አክራሪ ኒዮ ሊበራል ተቋማትን አስምለውና አስገዝተው ያሰማራሉ።
ታዲያ ለእነዚህ ተቋማትና ለርዕዩተ- ዓለማቸው ምቹ መደላድል ባለመፍጠር የሃገራቸውን ሃብትና ማዕድን ላለማዘረፍ አሻፈረኝ የሚሉ የታዳጊ ሃገራትን በልቦለድ ወሬ ዘገባቸው ገጽታቸውን በማበላሸት ሀገራቱ ለልማት የሚውል የገንዘብ ዕርዳታና ድጋፍ የሚያገኙበት እድል እንዳይኖር እንዲሁም በገንዘብ ኃይል ለመጠምዘዝ ይተጋሉ። ለእነርሱ ታዛዥ ለመሆን ያልፈቀደ መንግስትና ህዝብ ይወቀሳል፤ የሪፖርት ጋጋታ ውሽንፍር ይወርድበታል። ህዝቡንና ሃብቱን አሣልፎ ለመስጠት ያላቅማማ መንግስት ደግሞ በተቃራኒው ይሞገሳል፤ ይወደሳል። ይህ ማንም ተሟግቶ የሚረታበት የዓለማችን ጥቁርና ነጭ ሃቅ ነው—ያገጠጠና ያፈጠጠ እውነት።
አዎ! ሀገራችንን እየገረፋት ያለው ይኸው የነባራዊው ዓለም እውነታ ነው። እናም ከህዝቡ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ታሪካዊ ዳራዎች ጋር የሚጣጣሙ ፖሊሲዎች ስትራቴጂዎችና የልማት ኘሮግራሞች በመንደፍ የአክራሪ ኒዮ-ሊበራሎችን አስተሳሰብ ፉርሽ ያደረገ አዲስ ፍልስፍና ነድፎ ውጤታማ መሆን የቻለው የሀገራችን ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት፤ የእነርሱን ርዕዩተ- ዓለም እንደወረደ ለመቀበል የሚፈቅድ አውድ ባለመፍጠሩ ይወቀሳል— በኘሬስ ነፃነትና በሰብአዊ መብቶች ጥሰት ስም።  
አክራሪዎቹ ሊዮ ሊበራሎችም የእነርሱን ምኞትና ህቡዕ አጀንዳን ለማሳካት ፈቃደኛ የሆነ ትውልድና መንግስት ማግኘት ባለመቻላቸው የመንግስትን ገጽታ ለማጉደፍ ስዕለት ያለባቸው ይመስል እየተፈራረቁ የሚያሰሙት አሉባልታም መነሻውና መድረሻው ይኸው ነው። እናም የትኛውም አካል ቢሆን የእነርሱን ፍላጎትና ማንነት በመረዳት በተለያዩ ስያሜዎች ውስጥ ራሳቸውን ሸሽገው በተለያዩ ወቅቶች በሀገራችንም ይሁን በሌሎች ታዳጊ ሀገራት ላይ የሚሰነዝሯቸውን ወቀሳዎችንን ማጥላላቶችን መገንዘብ ይኖርበታል ባይ ነኝ።

No comments:

Post a Comment