Wednesday, 13 July 2016

ከመቀመጫው በስተጀርባ



ዮናስ

ባለፈው ሰሞን አገራችን ድምፅ ከሰጡ 190 የአባል አገራት የ185ቱን ይሁንታ በማግኘት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና መመረጧ እና ይህም መቀመጫ እ.ኤ.አ. ከ2017 እስከ 2018 አፍሪካን በአለም መድረክ ላይ የምትወክልበት እንደሆነ ይታወቃል ፡፡ ይህ ትርክት ከመቀመጫው በስተጀርባ ያሉትን ቁም ነገሮች የሚቃኝ ሲሆን፤ ይልቁንም በእነዚህ ሁለት የውክልና ዓመታት ውስጥ አባልነታችን ስለአገራችን እና አፍሪካ ያለውን ፋይዳ የሚያሄስ ይሆናል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በፀጥታው ምክር ቤት ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ካላቸው አምስቱ የዓለማችን ኃያል አገሮች (አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ታላቋ ብሪታንያና ፈረንሳይ) ጋር በመሰብሰብ፣  በዓለማችን ላይ ወሳኝ የሰላምና የደኅንነት ጉዳዮች ላይ ድምፅ በመስጠት ለመሳተፍ የሚያበቃትን ድምፅ ያለምክንያት እንዳላገኘች መቼም መገመት አይከብድም ። ከሁሉ በፊት ግን፤ ይህ መቀመጫ በየትኛውም መመዘኛ ብንወስደው የኢትዮጵያ መንግሥት ተደማጭ እና ተመራጭ የመንግስት ቁመና መላበሱን ጠቋሚ ነው። የተደማጭነት እና የተሰሚነት ቁመና ከመንግሥታት መልካም ባሕሪያት የሚመነጨውን ያህል ከዓለም ዓቀፉ የኃይል አሰላለፍ ጋርም ተዛማጅነት እንዳለው አጠያያቂ አይደለም። ስለሆነም ይህ ትልቅ ኃላፊነት የተገኘበትን ሚስጥር መመርመር ተገቢ ይሆናል፡፡
የመጀመሪያውን ምርመራ ስናደርግ የሚገኘው ውጤት በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ላይ ከተጋረጡት ሽብርተኝነት፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ የአደንዛዥ ፅዕ ዝውውርና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ጋር የተያያዘ፤ በዚህና በመከላከሉ ረገድ  አገራችን የተጫወተችው እና እየተጫወተች ያለው ሚና አመርቂ መሆኑን የተመለከተው ነው ፡፡  እንደ አልቃይዳ፣ አልሸባብ፣ ቦኮሃራምና አይኤስ ዓይነት ፅንፈኛ ቡድኖች በዓለማችን ሰላምና መረጋጋት ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ የሚገኙ መሆኑና በተለይም አገራችን በምትገኝበት ቀጣና የመፈርጠማቸውን ያህል ጉዳት ያለማድረሳቸው ምክንያት አገራችን በመሆኗ የተሰጠ መቀመጫ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡  
ይህ ማለት ግን፤ አሸባሪ ቡድኖቹን ጨምሮ ህገወጥ የሰዎች እና የገንዘብ አዘዋዋሪዎቹ አክትሞላቸዋል ማለት ሳይሆን የተጠናከረ ትግል እንደሚያስፈልግ የሚያመላክት ነው። ስለሆነም፤ ይህን የተወሳሰበ እና  ለፀጥታው ምክር ቤት ቁልፍ የሆነ ችግር በተለይ መናኻሪያ ከሆናቸው ቀጣና ለማስወገድ ከኢትዮጵያ ውጭ ሌላ ሊታሰብ አይችልም፡፡
ባልተረጋጋው ቀጣና ውስጥ ሆና ሰላሟን በማስጠበቅ፤ በእድገት ጎዳና ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ የዚህ ምክር ቤት አባል መሆኗ እነዚህን እና ከላይ የተመለከቱትን የዓለማችንን እና የአህጉራችንን ችግሮች የመዋጋትና ወሳኝ የሆኑ የመፍትሔ ሐሳቦችን በማቅረብ ብሎም ድምፅ በመስጠት ለአኅጉራችንም ሆነ ለዓለማችን ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ ማበርከቷ ሳይታለም የተፈታ ነውና መቀመጫው የሚገባት እንደሆነ ድምጽ በሰጧት አባል አገራት ዘንድ የተሰላ ይመስላል፡፡ ከላይ የጠቀስናቸው ችግሮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በዋነኝነት እየጐዱ ያሉት የአፍሪካን አገሮች የመሆኑን እውነታ ስናሰላ ደግሞ፤ የአፍሪካን ጥቅም የማስጠበቅ ወሳኝ ሥራ ከኢትዮጵያ ውጪ የማንም ሊሆን እንደማይችል አሁንም ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ወቅታዊውን የኢትዮጵያ መንግሥት ከቀደሙት ሁለቱ መንግሥታት የተለየ የሚያደርጉት ሁለት መሰረታዊ ነጥቦች ስላሉ ነው።
አንደኛው፤ የሚከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከቀደምት መንግሥታት በመሰረታዊ አስተሳሰብ የተለየ መሆኑ ነው። ይህም ሲባል፣ የቀድሞ መንግሥታት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መነሻና ማጠንጠኛ፣ በአፍሪካ ቀንድ የሚገኙ ጎረቤት አገሮችን ፖለቲካዊና ወታደራዊ አቅም እንደ ስጋት መውሰዳቸው ነው። አሁን ያለው መንግሥት የሚከተለው መንገድ፣ በአገር ውስጥ ካለው ተጋላጭነት ወይም ድህነት እና በአፍሪካ ቀንድ በሚገኙ ጎረቤት ሀገሮች ውስጥ ካለው ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ቁመና በላይ የትኛው አስጊ ነው የሚለውን የመዘነ ነው። በውጤቱም፣ በአገር ውስጥ ያለው ተጋላጭነት እስካልተቀረፈ ድረስ የትኛውም ኃይል አስጊ ሆነ አልሆነ መመከት በሚያስችል ቁመና ላይ መገኘት አይቻልም፤ የሚል መሰረታዊ ዕሳቤ የያዘ መሆኑ ተመራጭ እና ተደማጭ እንድትሆን አስችሏታል።
ኢትዮጵያ ከአሁን በፊት እ.ኤ.አ. ከ1967‑1968 እንዲሁም ከ1989‑1990 የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና ማገልገሏ ይታወሳል፡፡ ያም ሆኖ ግን፤ በዚያን ወቅት በዓለማችን ላይ የነበሩት ችግሮች በአሁኑ ወቅት ከሚታዩት ችግሮች ጋር የሰማይ እና የምድር ያህል ልዩነት ያላቸው መሆኑም በተመሳሳይ ይታወሳል፡፡ አሁን ያለው እውነታ ግን በዓለማችን ላይ የሚታዩ ችግሮች መልካቸው ተቀይሮ፣ ውስብስብነታቸውም ተጠናክሮ ዓለምን ዳር እስከዳር እያመሱ መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም አገራችን ከእራሳችን ባሻገርም ለአፍሪካ ብዙ የሚጠበቅባት መሆኑ አያጠያይቅም።
የኢትዮጵያ ሰላም የማስከበር ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ውስጣዊ ተጋላጭነትን ከሚያስወግድ   አስተሳሰብ በመፍለቁ በሌሎች አገሮች ተመራጭ መሆኑ ተገቢ ነው። በዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ዘንድም እውቅና ቢሰጠው ተገቢና ዘመኑ የሚጠይቀውን መርህ መሰረት ስላደረገ ነው። በዓለም ደረጃም ሶስተኛዋ የሰላም ማስከበር ኃይል አዋጪ መሆኗ ከመቀመጫው በስተጀርባ የሚገኝ ቁም ነገር ነው። ከዚህም በተጨማሪ በአካባቢ ለውጥ እና በዓለም የኢኮኖሚ ቀውሶች ዙሪያ፤ በተለይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ያቀረቧቸው አማራጭ ሃሳቦች ለአሁኑ የኢትዮጵያ መንግሥት በዓለም ዓቀፍ መድረክ ተቀባይነት እንዲጨምር መደላደል ፈጥረውለት አልፈዋል። አሁን ያለው አመራርም፣ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዎችን ርቀት በመጠበቅ በተገቢ ሁኔታ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑም በተመሳሳይ ከመቀመጫው በስተጀርባ ያለ እውነታ ነው ።
የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት፤ ቀጥሎም በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ አገሮች ነፃነት እንዲረጋገጥ  ኢትዮጵያ የተጫወተችውን ሚና የሚያውቁ አገራት ዛሬም በዙሪያቸው ከከበቧቸው ችግሮች ለመላቀቅ መቀመጫውን ቢፈቅዱላት የማይገርም እና የሚገባ ነው፡፡
ከላይ የተመለከቱት ችግሮች ዓለምን የተመለከቱ ቢሆንም አገራችንን ጨምሮ አህጉራችንን የሚፈትኑ የበርካታ ችግሮች ሰለባም መሆናችን ሰለአገራችን መቀመጫ ሊታወስ ይገባል።  አህጉራችን አፍረካ በተለያዩ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት  ልትደርስ ከምትችልበት የዕድገትና የብልጽግና ደረጃ ሳትደርስ ወደኋላ እየጐተተች ነው፡፡ ምንም እንኳን በአህጉሪቷ የሚገኙ አገሮች ከቅኝ ግዛት ነፃ ቢወጡም፣ በርካታዎቹ ግን አሁንም ከድህነትና ከእርስ በርስ ጦርነት ሊላቀቁ ያልቻሉ መሆኑ በግልጽ የሚታይ ነው፡፡
በዚህም ሳቢያ አህጉሪቷ በሰዎች ሕይወትና በንብረት ላይ በሚደርስ ጉዳት እየደረሰ ከፍተኛ ኪሳራ ውስጥ ትገኛለች። በመሆኑም አሁን ኢትዮጵያ  በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል በመሆን ባገኘችው ዕድል ቀደም ሲል የገነባችውን አቅምና ያደረጀችውን ተሰሚነት ጨምራ የአፍሪካን አጀንዳ ከምንም በላይ ቅድሚያ በመስጠት መሞገቷ ይጠበቃልና መቀመጫው ይገባታል ፡፡  
ከላይ እንደተጠቀሰው በአሁኑ ወቅት ሽብርተኝነት ለዓለማችን በተለይም ለጸጥታው ምክር ቤት ዋነኛው ራስ ምታት ነው ቢባልም፤ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ የአደንዛዥ ፅዕ ዝውውር፣ እንዲሁም ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ዓለማችን ከገጠሟት ፈተናዎች ሁሉ የላቁት መሆናቸው  ይታወቃል ፡፡  
ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ ደግሞ ለዚህ ችግር ተጋላጭ ከሆኑ አካባቢዎች አንዱና ዋነኛው መሆኑም ስለጉዳያችን እና ስለመቀመጫው አጽንኦት የሚሰጠው  መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ለዚህ ደግሞ መቀመጫውን በሶማሊያ ያደረገውና የአልቃይዳ ክንፍ የሆነውን አልሸባብ ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡ይህ ፅንፈኛ ቡድን የሶማሊያን ብሎም የአካባቢውን ሰላም የማወክ ተግባሩን ለዓመታት ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ፤ በኢትዮጵያና በጎረቤት አገሮች ያላሰለሰ ጥረት አልሸባብ በከፍተኛ ደረጃ ተዳክሟል። ይህንንም ድፍን ዓለም አረጋግጧል፡፡ይህን የአሸባሪ ቡድን በማዳከም ሥራ ላይ ደግሞ ግንባር ቀደሙን ሚና የተጫወተችው ኢትዮጵያ ስለመሆኗ በተመሳሳይ ዓለም የመሰከረው ነው ፡፡ በመሆኑም ይህንን ልምዷን በማካፈል በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ ተመሳሳይ አሸባሪ ቡድኖች የሚጠፉበትን ዘዴ ለመቀየስ ለአባል አገራቱም ሆነ ለምክር ቤቱ አስፈላጊነቷ አላጠያየቀምና መቀመጫው ተሰጥቷታል፡፡ 
ከዚህ ጋር ተያይዞ በዓለም መድረክ ላይ አገራችን መቀመጫው የሚገባት ስለመሆኑ የሚያጠይቅ ሌላም አስረጂ አላት ። ተመድ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ ለተለያዩ አገሮች ሰላም መስፈን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጓ በዓለም የታሪክ ድርሳናት ፤ በዓለም ማህበረሰብ ልቦና ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኙ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ለምሳሌ በኮሪያ፣ በኮንጐ፣ በላይቤሪያ፣ በብሩንዲ እንዲሁም በቅርቡም በሱዳንና በደቡብ ሱዳን ድንበር ሰላም አስከባሪ ኃይል በመላክ ሰላምን ለማስፈን ቁርጠኛ የሆነ አቋም እንዳላት አሳይታለች፡፡ ሰላም ለሰው ልጆች ህይወት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ ከዚያም ባለፈ ለአገር ዕድገትና ልማት ከፍተኛ የሆነ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጥርጥር የለውም፡፡ ኢትዮጵያም የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና ስለመመረጧ  ከምንም በፊት ለሰላም የቆመች አገር መሆኗ ሌላኛው ምክንያት ነው፡፡  


No comments:

Post a Comment