Thursday, 28 July 2016

የህዳሴው ግድብ፣ የትክክለኛ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ውጤት



አባ መላኩ

ኢትዮጵያ ባለፈው ሁለት አሥርት ዓመታት የተከተለችው  ኢኮኖሚክ ዲፕሎማሲን መሠረት ያደረገው  የውጭ  ግንኙነት  ፖሊሲ በአገራችን አስተማማኝ  ሠላም በመስፈኑ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ዕድገት ማስመዝገብ አስችሏል። የኢትዮጵያ መንግሥት በሚከተለው ትክክለኛ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ሳቢያ በቀንዱ ብቻ ሳይሆን በመላ አፍሪካ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል። በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት የወጣ መረጃ  እንደሚያመለክተው  በተባበሩት መንግሥታት  ጥላ ሥር ከሚንቀሳቀሱ የሠላም ማስከበር ሠራዊት ካበረከቱ የዓለም አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በቀዳሚነት ስትጠቀስ ከዓለም ደግሞ በሁለተኛነት ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አመልክቷል።

ግብፅ የአካባቢውን አገራት በኢኮኖሚያዊም ሆነ በማህበራዊ ጉዳዮች በበላይነት እመራዋለሁ ስትል ብትቆይም የቀጠናውን አገራት በጥቅም ሊያስተሳስር የሚችል አንዲት ፕሮጀክት እንኳን ማበርከት ሳትችል ለዘመናት ኖራለች። ኢትዮጵያ ለሁለት አሥርት ዓመታት መረጋጋት በመቻሏና በተለይም ባሳለፍነው አሥር ዓመት ተከታታይና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ በመቻሏ የቀጠናውን አገራት በጋራ ሊያስተሳስራቸው የሚችል ፕሮጀክት ተግባራዊ ማድረግ ችላለች። ህዝቦች በጋራ ጥቅም የሚተሳሰሩ ከሆነ የአካባቢው ሠላም አስተማማኝና ቀጣይነት ይኖረዋል።
ግብፃዊያኖች በበጎ አልተመለከቱትም እንጂ የላይኞቹ የተፋሰስ አገራት ግንቦት 24/2010 በኢንቴቢ ኡጋንዳ ያደረጉት ስምምነት የጋራ ተጠቃሚነትን በማስፈን በአየር መዛባት ሳቢያ በተጨባጭ እየታየ ያለውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግ እየቀነሰ የመጣውን የወንዙን የውኃ መጠን መታደግ ላይ ያተኮረ ነበር። በቀጣይ በላይኞቹ የተፋሰስ አገራት በተለይ ዋንኛው የውኃ መገኛ በሆነው ተራራማው የኢትዮጵያ መልካ ምድር ውጤታማ የሆነ የአካባቢ ጥበቃ ካልተከናወነ የአባይ ወንዝ ደህንነት ቀጣይነት እንደማይኖረው ግብፃዊያኖች ሊያውቁት ይገባል።

አገራችን ለአፍሪካ ቀንድ የሠላምና መረጋጋት ካበረከተችው አስተዋጽኦ ባሻገር የአካባቢው አገሮች በኢኮኖሚ ጥቅም እንዲተሳሰሩ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነች ትገኛለች። ከእነዚህ ፕሮጀክቶች መካከል የታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በዋነኛነት የሚጠቀስ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት የታላቁን የህዳሴ ግድብ ሲያቅድ በዋነኛነት ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚሰጠውን ጥቅም ታሳቢ ቢደረግም የጎረቤት አገሮችም በተለይ የሃብቱ ቀጥታ ተጋሪ የሆኑት ሱዳንና ግብፅ የሚያገኙትን ጠቀሜታም ከግምት እንዲገባ በማድረግ ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት የሚገነባቸው ፕሮጀክቶች በጎረቤት አገራት ላይ ጫና የማይፈጥሩ  መሆናቸውን ስለሚተማመን  የትኛውም የተፋሰስ አገራት እስካሁን አድርገውት በማያውቁት ሁኔታ የዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ፕሮጀክቱን እንዲገመግሙ ሁኔታዎችን አመቻችቷል።

ግብጽም ሆነች ሱዳን በአባይ ላይ በርካታ ፕሮጀክቶችን ሲያከናውኑ ለላይኞቹ የተፋሰስ አገራት  ፕሮጀክቶቻቸውን ማስገምገም ይቅርና የሚመለከታቸው የተፋሰሱ አገራት እንኳን እንዲያውቋቸው አድርገው አያውቁም። ይህ የሚያመላክተው የኢትዮጵያ መንግሥት የሚከተለው የውጭ ፖሊሲ ግልጽና የተፋሰሱ አገራትን በጥቅም ሊያስተሳስር የሚችል ፕሮጀክቶችን እየተገበረ እንደሚገኝ የሚያሳይ ነው።

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ግብፃዊያን በአባይ ወንዝ ላይ ሙሉ ለሙሉ ጥገኛ መሆናቸውን ከግምት በማስገባት በተፋሰሱ ላይ እኩል ተጠቃሚነት ይኑር የሚል መርህ ይተግበር ሳይሆን ፍትኃዊ የውኃ ሀብት አጠቃቀምን እንተግብር፣ ግብጻዊያን ወንድሞቻችን ሳትጎዱ በድህነት የኖረው ኢትዮጵያዊ መብራት ያግኝ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት ለግብፃዊያን ወንድሞቻችን እንዳሰብንላቸው እነሱም ለእኛ ሊያስቡልን ይገባል።    


አባይ የተፋሰሱ አገራት የጋራ ሀብት ነው። ይሁንና ግብጻዊያን ፖለቲከኞች አባይ የግብጻዊያን ንብረት ብቻ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲያውጁ በመኖራቸው ሳቢያ በግብጻዊያን መካከል የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። ከወንዙ 85 በመቶ በላይ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ ለዘመናት ከወንዙ ምንም ድርሻ ኖሯት አያውቅም። ይሁንና የኢትዮጵያ መንግሥት ውኃውን እኩል ልካፈል ወይም እኩል ድርሻ ይሰጠኝ የሚል መርህ አልተከተለም። ይልቁንም የኢትዮጵያ መንግሥት መርህ “ፍትሃዊ የውኃ ክፍፍል”  የሚል ነው።

የአባይ ጉዳይ በየትኛውም መስፈርት በፍጥጫ፣ በማስፈራራት ወይም በሌላ አካል በሚመጣ ጫና በተፋሰሱ አገራት መካከል ዘላቂ ሠላም ሊሰፍን አይችልም። በተፋሰሱ አገራት መካከል ዘላቄታዊ ሠላም ሊሰፍን የሚችለው የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ እንደሚገልፀው በተፋሰሱ አገራት መካከል “ፍትሃዊ የውኃ ክፍፍል”  ማስፈን ሲቻል ብቻ ነው።

አባይ የተፋሰሱ አገራት የጋራ ሃብት ሊሆን የሚችለው የተፋሰሱ አገራት ይህን ሃብት በጋራ በማልማት የኢኮኖሚ ጠቀሜታ የሚያገኙበት እንዲሁም የጋራ ሃብታቸውን ቀጣይነት እንዲኖረው በጋራ መንከባከብ ሲችሉ ብቻ ነው። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም ላይ እየተከሰተ ባለው የአየር ንብረት ቀውስ ሳቢያ በላይኞቹ የተፋሰስ አገራት ጠንካራና ዘለቄታዊነት ያለው የአካባቢ ጥበቃ ካልተከናወነ በስተቀር የአባይ ህልውና አደጋ ላይ ይወድቃል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት አሥርት ዓመታት ሰፊ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ በማከናወኑ በአገሪቱ ባሉ ተፋሰሶች ተሻሽለዋል። በሁሉም የአገሪቱ ክፍል የደን ሽፋን ተጨባጭ ለውጥ አሳይቷል። በርካታ ምንጮች አገግመዋል። በመሆኑም የወንዞች ፍሰት መሻሻል አሳይቷል። ከዚህ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው አባይ ነው።

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት የኢትዮጵያ ጂኦግራፊካል አቀማመጥ ሸለቆማና ተራራማ በመሆኑ የታላቁ የህዳሴ ግድብ እየተገነባ ያለው ጥልቀት ባለው ሥፍራ በመሆኑ በአነስተኛ ቦታ ላይ እጅግ ከፍተኛ ውኃ የሚጠራቀም በመሆኑ ትነትን በከፍተኛ ሁኔታ መቆጣጠር ስለሚያስችል የውኃ ብክነትን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ያስችላል። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ግብጻዊያን ፖለቲከኞችና ምሁራኖች ለህዝባቸው የሚያቀብሉት መረጃ  ከእውነታ ጋር የሚጋጭ ነበር።   

አባይ  ኢትዮጵያን፣ ሱዳንና ግብንፅ የሚያስተሳስር ይሁን እንጂ  የእነዚህ  አገራት ሥነ ምህዳራዊ አቀማመጥ የተለያየ ነው። ኢትዮጵያ ሸለቆማና ተራራማ የሆነ አቀማመጥ በመታደሏ አገሪቱ ለከፍተኛ የታዳሽ ኃይል ምንጭ ባለቤት እንደትሆን አድርጓታል እንጂ እንደግብጽና ሱዳን ለመስኖ የሚያገለግል መሬት እምብዛም የላትም። በአንጻሩ ሱዳንና ግብፅ ደግሞ የተሻለ የመስኖ ልማት ሊሰሩበት የሚችሉበት ሰፋፊ የእርሻ ሥፍራዎች የታደሉ ይሁኑ እንጂ እንደኢትዮጵያ በቀላል ወጪ የታዳሽ ኃይል ምንጭ ባለቤት መሆን አይቻላቸውም። የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ታሳቢ በማድረግ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በመተግበር የተፋሰሱ አገራትን በኃይል አቅርቦት ለማስተሳሰር እየሰራ ይገኛል።

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ለኃይል ማመንጫነት እንጂ ግብፃዊያን ፖለቲከኞች እንደሚሉት ኢትዮጵያ ውኃውን ለመቆጣጠር ሆነ ለመስኖ ልማት አይደለም። የኢትዮጵያ መልካዓ ምድር በተለይ አባይ በሚያልፍባቸው በዋነኛነት የሰሜንና የሰሜን ምዕራብ አካባቢዎች ተራራማና ሸለቆማ በመሆናቸው ወንዙ  በኢትዮጵያ ምድር ለመስኖ ልማት የሚሰጠው አገልግሎት እጅግም እንደሆነ ግብፃዊያን ፖለቲከኞች የሚያጡት አይመስለኝም። የኢትዮጵያ መንግሥት ወሰን ተሻጋሪ ወንዞች በዓለም አቀፍ ስምምነት መሠረት የሚተዳደሩ መሆናቸውን ከግንዛቤ በማስገባት የህዳሴው ግድብን ለኃይል ልማት እንጂ ለመስኖ እንዳልሆነም በተደጋጋሚ አሳውቋል።

ከዚህ ባሻገርም ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ እየተገነባ ያለበት ሥፍራ ሱዳን ድንበር አካባቢ እንደሆነ ይታወቃል። ከነዚህ እውነታዎች መረዳት የሚቻለውና ኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ እንደገለፀውና ዓለም አቀፍ የውኃ ኤክስፐርቶች የግምገማ ውጤት እንዳረጋገጠው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኃይል ማመንጫ እንጂ ለመስኖ አገልግሎት እንደማይውል እንዲሁም ፕሮጀክቱ በግብጽም ሆነ በሱዳን  ላይ ይህ ነው የሚባል ጫና እንደማያስከትል ያሳያል። እንግዲህ የታችኞቹ የተፋሰስ አገራት ላይ ከፍተኛ ጫና ሳይፈጥር ኢትዮጵያን ህዝብ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ፕሮጀክት  የኢትዮጵያ መንግሥት መገንባት መጀመሩ ሊያስመሰግነው ይገባል።


የታላቁ የህዳሴ ግድብ ለእኛ ኢትዮጵያዊያን የኃይል ማመንጫ ብቻ ሳይሆን የአገራችን መለያ መታወቂያ “ብራንድ’’ እንዲሆን እንፈልጋለን። በአገራችን በርካታ  ፕሮጀክቶች እየተካሄዱ ቢሆንም እኛ ኢትዮጵያዊያን ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ልዩ ትኩረት እንሰጠዋለን። ለዚህ ፕሮጀክት  ተማሪው፣ መምህሩ፣ ፖሊሱ፣ መከላከያ ሠራዊቱ፣ መንግሥት ሠራተኛው፣ ነጋዴው፣ አርሶ አደሩ፣ የከተማው ነዋሪው፣ በውጭ አገር ነዋሪነታቸውን ያደረጉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ብቻ ለአገሩ ቀና አመለካከት ያለው ሁሉ በሚችለው በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በቁሳቁስ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል። ይህ ትብብር ግድቡ እስኪጠናቀቅም የሚቀጥል ይሆናል።

በአገራችን ታሪክ እስካሁን ከታዩ የልማት ፕሮጀክቶች እንደ ህዳሴው ግድብ ያለ  የህዝብን ቀልብ የገዛና የሁሉም ህዝቦች አሻራ ያረፈበት ፕሮጀክት አልታየም። ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የአገራችንን ገጽታ የሚቀይር በህዝቦች መካከል “የይቻላል” ስሜት የፈጠረ ፕሮጀክት በመሆኑ የልማት ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝቦች መለያ ብራንድ ነው።








No comments:

Post a Comment