Friday, 9 June 2017

ወደ እምዬ ተመለሱ!!



     
                                  ይነበብ ይግለጡ
በስደት ሳኡዲ አረቢያ የምትገኙ ዜጎቻችን ከምንለው በላይ የሚሰማችሁንና የምትሉትን  እናውቃለን፡፡ስራ የለንም፤ ቤተሰብ በምን እንረዳለን፤ስራ አጥ ሆነን እስከመቼ እንገፋለን ተመልሰን ያን የድህነት ኑሮ አናየውም፤የትም ሄደን የሚመጣውን ፈተና፤ለመቀበል ዝግጁ ነን:ወደሀገራችን ምን ይዘን እንመለሳለን ምንስ ልንሰራ እንሄዳለን ወዘተ የሚል ስሜት በውስጣችሁ እንደሚንከባለል እናውቃለን፡፡
ኢትዮጵያን የመሰለ ወድ ሀገራችሁን ጠልታችሁ እንዳልሆነም ይገባናል፡፡ፈተና የሆነባችሁ ስራ ሰርቶ ለመኖር አቅም ማጣቱና ስራ ፈቶ የሚገፋው ሕይወት ነው፡፡የኢኮኖሚ ስደት ከስደትም የከፋው አይነት መሆኑን ታውቃላችሁ፡፡ከሀገር በሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ግፊት ቤተሰብ ነገን አስቦ ለልጆቹም ሕይወት እየሳሳ ጭምር ተጨንቆና ተጠቦ ተበድሮና ተለቅቶ ከሚከፍለው ከፍተኛ ገንዘብ ጀምሮ በሕገወጥ መንገድ የሚደረገው ፈተናና መከራ የተሞላበት ጉዞ ወድ ዋጋ እንደሚያስከፍል ሁሉም ሰው ያውቀዋል፡
በባሕር ሰምጠው የቀሩትን በአውሬ የተበሉትን ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡በሕገወጥ መንገድ የሚደረግ ስደት ሁሉ ከፍተኛ የመንፈስና የአካል ዋጋ ያስከፍላል፡፡አብዛኛው ሕጋዊ መታወቂያና መለያ ስለማይኖረው አደጋ ሲፈጠር ከሌሎች ተለይተን ስለምንታወቅ ብቻ ነው ኢትዮጵያዊ መሆናችን የሚለየው፡፡
እዚህ ድረስ በሕይወታችሁ የተደቀነ አደጋን ይዛችሁ ነው የምትዞሩት፡፡ወደየመን ለመድረስ ባሕር ሲያቋርጡ ወደ ኢጣሊያ ለመሻገር ላምባዱሳ ወደብ ለመድረስ ምን ያህል ዜጎቻችን ሰምጠው እንደቀሩ ሁላችንም እናውቃለን፡፡መከረኛው ስደትና እንጀራ ፍለጋ ያንከራተታቸው ወንድሞቻችን ሊቢያ ላይ እንደከብት በአይሲስ አንገታቸው ሲታረድ የሀዘናችንን ጥልቀትና የተሰማንን የመረረ ሀዘን ዛሬም መቸም አንረሳውም፡፡
ለአይቃይዳም ሆነ ለአይሲስ እስከ አለም ፍጻሜ ድረስ የማንተኛው የተከበረች ሀገርና ለአለም የሚተርፍ ወገን እያላቸው በሰው ሀገር በበረሀ ላይ ወንድሞቻችንን ልጆቻችንን እንደ ከብት አርዶ ደማቸውን ስላፈሰሰው ነው፡፡አንደርስላቸው ነገር ሁኖ እንጂ ጥቃት የሚገባን እንኳን አልነበርንም፡፡ይሄም ከአንጀት ያስለቅሰናል፡፡የእናቶቻችን መቀነት አንጀታቸው ድረስ ሰልስሎ እስኪገባ ድረስ ሀዘናቸው በርትቶ ከመኖር ሞትን የተመኙበት ልጆቼን መልሱልኝ ሲሉ ሀገርን በእንባ ያራጩበት የሀዘን ቀን ዛሬም ከፊታችን አልጠፋም፡፡የዚህ ሁሉ መነሻው ሕገወጥ ስደት ነው፡፡በሕገወጥ ስደት ውስጥ ዜጎች ሕጋዊ ዋስትና ጥበቃና የሕግ ከለላ የላቸውም፡፡
ማንም እንዳሻው ሲጫወትባቸው ውብ እህቶቻችንን ለወሲብ ንግድ እንደ ቁም ከብት ሲሸጣቸው ሲለውጣቸው የሰውነት ክብራቸው ተገፎ ወይ ሀገሬ እስኪሉ ድረስ የምድር ሲኦልን ያዩበት የተፈተኑበት ሁኔታ ብዙ ነው፡፡ የግድ የጉልበት ስራ ከአቅም በላይ እንዲሰሩ እየተገደዱ በግፍ እየተገደሉ ከፎቅ እየተወረወሩ ብዙ አሰቃቂ ድርጊቶች በወገኖቻችን ላይ ተፈጽሞአል፡፡ ምኑን አንስተን ምኑን እንደምንተወው ይጨንቃል፡፡
በደቡብ አፍሪካ በስደት በሚኖሩ ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመውን እጅግ ሰቅጣጭ ግፍና በደል አንረሳም፡፡የሚያኮራ የታጋድሎና የጀግንነት ታሪክ ባለቤት የሆንን ሕዝብ ነን፡፡ ለደቡብ አፍሪካውያን በጨለማ ዘመናቸው መጠለያ መሸሸጊያ ዋሻ ሁነን ያለንን አካፍለን ከቅኝ አገዛዝ  ነጻ እንዲወጡ የምንችለውን ሁሉ ያደረግን ነን፡፡
በአለም ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ የቅኝ ገዢ ፋሽስት ሠራዊት በጥቁር ሕዝብና በጥቁር አፈር ላይ ድል የተመታበት ታላቅ ታሪክ ባለቤቶች ነን፡፡የሰው ልጅ በመጀመሪያ የኖረባት የተገኘባት ምድር ባለቤት ነን፡፡ቀደምት የስልጣኔ ምንጭ ጥንታዊ ከሚባሉት የአለማችን ሀገሮችም አንድዋና የመጀመሪያዋ የእኛዋ ኢትዮጵያ ነች፡፡በተለይ በዚህ ዘመን ድህነትን ታሪክ አድርጎ ለማስቀረት ሀገራችን ታላቅ እመርታዊ ለውጥ በማስመዝገብ ላይ ገኛለች፡፡

በአፍሪካ ቀዳሚ በአለም አስረኛ በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ከሚገኙ ሀገሮች ተርታ ተሰልፋለች፡፡ታላቅ ተስፋና ጉዞን የሰነቀች በእድገት ጎዳና የምትገኝ ሀገር ነች፡፡በብዙ መልኩ ኢትዮጵያ ተለውጣለች፡፡ሰፊ የስራ መስኮች እየተከፌቱ ይገኛሉ፡፡ለውጭ ኢንቨስተሮች ተመራች ሀገር በመሆንዋ ሰፊ የስራ እድሎች እየተከፈቱ ይገኛሉ፡፡ካለውም  በላይ ወደፊት የበለጠና የላቀ ተስፋ ከፊታችን አለ፡፡
ዜጎቻችን ሕገወጥ ስደትን ይህንንም ተከትሎ የሚመጣውን ውርደት ፈተናና መከራ ማቆም ይችላሉ፡፡ምን አለኝ ሀገሬ ማለት መቻል አለባቸው፡፡የእናቶችና የአባቶችን ለቅሶና እንባ መጥረግ የምንችለው ምንም ይሁን ምንም በሀገራችን ላይ ሰርተን ለማደግ ለመለወጥ እንችላለን ብለን ስንወስን ብቻ ነው፡፡ ሕገወጥ ስደት ይብቃ፡፡የሀገር ውርደት ይብቃ፡፡
ከሀገር ወጥቶ ሰርቶ ለመኖር ከተፈለገም በሕጋዊ መንገድ መንግስት አውቆት ለስራ ቢወጡ የሕግ ጥበቃና ከለላ ይኖራቸዋል፡፡ውርደት መከራ ፈተና አይደርስባቸውም፡፡ የሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎችና ሻጮች የወሲብ ንግድ ነጋዴዎች መጫወቻ አይሆኑም፡፡ የሳኡዲ አረቢያ መንግስት በሕገወጥ መንገድ ሀገሬ ውስጥ የገባችሁ በሰጠሁት ምህረት መሰረት ሀገሬን ለቃችሁ ውጡ ብሎአል፡፡የተሰጠው ይህ የምህረት ገደብ ሊያበቃ በጣት የሚቆጠሩ ሳምንታት ብቻ ቀርተዋል፡፡
በዚያች ሀገር ከመቶ ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ ይታመናል፡፡በሕጋዊነት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የተመዘገቡት እጅግ በጣም ጥቂት ናቸው፡፡ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ዜጎቻችን በሰላም ወደሀገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ሳኡዲአረቢያ ድረስ በመሄድ ዜጎቻችንን እያነጋገሩ በፍጥነት ወደሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ራሱን የቻለ ከፍተኛ መንግስታዊ ቡድን ተቋቁሞ ቦታው ላይ በመገኘት እየሰራ ነው፡፡
መንግስት ለዜጎቹ የሰጠውን ልዩ ከበሬታና ትኩረት ያሳያል፡፡የሚደነቅ የሚበረታታም ስራ ነው፡፡የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከሳኡዲ አቻቸው ጋር ወደውጭ ለስራ በህጋዊ መነገድ የሚሄዱትን ዜጎች በተመለተ ሕጋዊ ውል ተፈራርመዋል፡፡ይህም የሚያሳየው ዜጎቻችን እዚያች ሀገር ሄደው መስራት ከፈለጉ በሕጋዊ መንገድ መንግስት አውቆት ሄደው መስራት ይችላሉ፡፡አንዳችም አይነት ጉዳትም ሆነ ውርደት አይደርስባቸውም፡፡የደላሎችና በሰው ንግድ ላይ የተሰማሩ ሰዎች መጫወቻ አይሆኑም፡፡
በዜጎች ላይ ችግር ቢፈጠር የሚከራከረው የሚናገረው መንግስት ነው፡፡ዜጎቼ ተበድለዋል ተንገላተዋል፤ደመወዝ አይከፈላቸውም ወዘተ ብሎ ስለእነሱ የሚናገረው መንግስት ነው የሚሆነው፡፡ይሀው መንገድ አንድ ሺህ አንድ ግዜ ይመረጣል፡፡ከዚህ ውጭ ያለው አካሄድ በሙሉ በአደጋ የተሞላ ነው፡፡አደጋው የገዘፈም ነው፡፡
የሳኡዲ መንግስት በሀገሩ ሕግና ደንብ መሰረት በሕገወጥ መንገድ በግዛቴ ውስጥ የምትገኙ የምትኖሩ ውጡልኝ የማለት መብት አለው፡፡በዚህ ማንም መከራከር አይችልም፡፡እንደ ሀገር እኛም በሕገወጥ መንገድ ሳይታወቅና ሕጋዊነት ሳይኖራው ወደሀገራችን መሬት ገብተው የሚኖሩ ካሉ በሕገወጥነት መያዝ ማሰር ከሀገር ማስወጣትም መብቱ ነው፡፡
ሳኡዲ አረቢያ ያደረገችው ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡እንዲያውም ብዙ ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሳኡዲ መንግስት የምሕረት ግዜ አዋጅ አውጥቶአል፡፡ይህን ጉዳይ አለም እንዲያውቀው አድርጎአል፡፡በኃላ ላይ ክርክርና ጭቅጭቅ እንዳይፈጠር ወቀሳና ከሰሳ እንዳይመጣ አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ነን የሚሉ ወገኖች ጩሀት እንዳያስነሱ በጥንቃቄ ታስቦበት የተሰራ ስራ ነው፡፡
የተሰጠው የምህረት የግዜ ገደብ ካለፈ በኃላ በሳኡዲ መሬት የተገኘ የውጭ ዜጋ ሁሉ የሚዳኘው በወንጀለኛነት ነው፡፡ይታሰራል ተከሶ ፍርድቤት ይቀርባል፡፡እስር ቤት ይወረወራል፡፡ወይንም ወደ ሀገሩ ተጭኖ በግዴታ እንዲመለስ ይደረጋል፡፡በዚህ ትርምስ መሀል መጎዳት መደብደብ ሌላም አደጋ ሊከሰት እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ይህ አይነቱ ችግር ከመምጣቱ በፊት በክብር ወደ ሀገር መመለስ ሕጋዊ መስፈርቶችን አሟልቶ ተመልሶ እዛው ሀገር በመሄድ መስራት የሚቻልበት ሁኔታ መኖሩን የራሳቸው የሳኡዲ ባለስልጣናት እየተናገሩ ይገኛሉ፡፡
ይህንን እድል በአግባቡ አለመጠቀም የከፋ ችግር ያስከትላል፡፡ለምሳሌ በሕገወጥ መንገድ የወጡ ዜጎቻችን ፓሰፖርትና መታወቂያ የላቸውም፡፡አሁን መንገስት በሕገወጥ መንገድ ቢወጡም ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን እያረገገጠ 49 ሺህ ዜጎች ፓስፖርት እንዲያገኙ አድርጎአል፡፡በቀደመውም ዙርም ይሀው ሁኔታ ተደርጎአል፡፡ይህን ማግኘት ከቻሉ ወደሀገራቸው ተመልሰው ሲያበቁ ተመልው በሕጋዊ መንገድ ለስራ መውጣት ይችላሉ፡፡ የሚሻለው የሚበጀወም ይሀው ነው፡፡
በተረፈ በሰው ሀገር በግድ ልቀመጥ ልስራ የሚባልበት ሁኔታ መቼም አይኖርም፡፡ የተሰጠው የቀን ገደብ ከማለፉ ውዝግብ ውስጥም ከመገባቱ በፊት ወደ እናት ሀገር መመለስ ይበጃል፡፡ሳኡዲ አረቢያ በ1930ዎቹ የነዳጅ ዘይት ሀብት ከመገኘቱ በፊት ከአለማችን ድሀ ሀገሮች የመጨረሻዎቹ ተርታ የምትገኝ ነበረች፡፡
ዘመናዊ እውቀትና ትምህርት ስላልተስፋፋ በአብዛኛው ስራዎችዋ የሚሸፈኑት ዛሬም ድረስ በውጭ ዜጎች መሆኑ ይታወቃል፡፡ከቤት ሰራተኛነት እስከ ከፍተኛው የእውቀት መስክ ድረስ በውጭ ዜጎች ነው እያሰራች የኖረችው፡፡የአሁኑን ውጡልኝ ጥያቄ ያመጣው ስራዎች ሁሉ ቅድሚያ ለሳኡዲ ዜጎች ሊሰጥ ይገባዋል የሚል ፖሊሲ የፈጠረው ነው፡፡ሌላ አይደለም፡፡
እኛም ውብና ለምለም የሆነችውን ሀገራችንን ሰርተን ማልማት ማሳደግ ይጠበቅብናል፡፡ ኢትየጵያ ታላቅ የወደፊት ተስፋን የሰነቀች አሁንም በትልቅ የኢኮኖሚ እመርታዊ ለውጥ ውስጥ የምትገኝ ሀገር ነች፡፡ድህነት አዋራጅ መሆኑን የምናየው ስደትን ተከትሎ ከሚመጣው ሰብአዊ ክብርንና ማንነትን የሚያዋርድ የሚገፍ ተግባር በስፋት ሲፈጸም እያየን ስለሆነ ነው፡፡
ማጠቃለያ
ከድሕነት ለመውጣት ሀገራችን ትልቅ ትግል ይዛለች፡፡በስኬት ጎዳና እየተራመደችም ትገኛለች፡፡የእኛ መሰደድ አብቅቶና ታሪክ ሁኖ ሌሎች ስራ ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ የሚሰደዱበት ግዜ እንደሚመጣ በእርግጠኝት እንናገራለን፡፡አዋራጁ ስደት ይብቃ፡፡ ዜጎቻችን ወደ ውድ እናት ሀገራችሁ ተመለሱ፡፡ክፉውም ደጉም በሀገር ላይ ከወገን ጋር ይሻላል፡፡ሰርቶ ለመኖር የሚያስችሉ ሰፊ መሰረቶች እየተጣሉ ነው፡፡ለሀገራችሁ ለቤተሰባችሁ ውዶች ናችሁ፡፡ ወደ እምዬ ወደ እናት ሀገራችሁ ተመለሱ!!




No comments:

Post a Comment