ይነበብ
ይግለጡ
የዘመን ጉርምቢጥ ላይ ደርሰናል፡፡ስለትልቅዋ ሀገር ማሰብ
ሳይሆን ወደጎጥ እየወረድን ወደመንደር እሳቤ እየተንሸራተትን
የነበረ አብሮነታችን መተሳሰባችን ፍቅራችን አንድነታችን በሚያሳዝን ሁኔታ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ወድቆአል፡፡ ይሄን ክፉ ደዌ
ይሄን ክፉ በሽታ በሕዝቡ ውስጥ ነፍስ እንዲዘራ እግር አውጥቶ እንዲራመድ ያደረጉት ሁሉ በትውልድ በሀገር በታሪክ ፊት ደግመው ደጋግመው ሊያፍሩ ይገባቸዋል፡፡
በልዩነት ውስጥ ያለውንና ለብዙ ሺህ ዘመናት የኖረውን
በማይበጠስ የታሪክ የትውልድ የደም የስጋ ትስስር የተለሰነውን ኢትዮጵያዊ ማንነት ሲሸረሽሩትና ሲያደሙት ሲያቆስሉት
ኖሩ፡፡ቢያስቡት አልተሳካላቸውም፡፡በሕዝቡ መካከል ያለውን ጥንታዊና የቆየ የጋራ ሕብር ስሜት መከባበር መረዳዳት መተሳሰብ በጋራ
የመኖር ባሕል በኃዘኑም በደስታውም በአብሮነት ቆሞ ስንትና ስንት ዘመናትን ያሳለፈውን ሕዝብ እርስ በእርሱ እንዲባላ እንዲናቆር
እንዲፋጅ ይህን ሴራ ሆን ብለው ሲያዛምቱት የኖሩት ጠባቦችና የትምክህት ኃይሎች ናቸው፡፡
በዘርና በጎሳ የተመሰረተ ጠባብ አስተሳሰብ ሌላውን በጥላቻ
አይን መመልከት መፈረጅ እኛ ብቻ ነን የሚል የድንቁርና አስተሳሰብ ዛሬም ነገም ለኢትዮጵያ ሰላምና እድገት ለሕዝቦችዋም አብሮነት
አይበጅም፡፡በሕብረተሰብ እድገትና ለውጥ ውስጥ ቋሚና ዘላቂ ሁኖ ዝንተ አለም የሚኖር ምንም ነገር የለም፡፡ሁሉም ያልፋሉ፡፡ቋሚና
ዘላቂ ሆነው በየትውልዱ ፈረቃ የሚቀጥሉት ሀገርና ተከታታይ የሆነው ትውልድ ብቻ ነው፡፡
ጠባብነትና ትምክህት የመጨረሻው በአለማችን ላይ ያለ አስከፊ
በሽታ ነው፡፡ሀገር አውድሞአል፡፡ታላቅ ደም አፋሶአል፡፡የሚገርመው ይህ ሁሉ አልፎ አልፎም ሕዝቡ ቀድሞ ወደነበረው አንድነቱና
መተሳሰቡ ተመልሶ በሰላም ሲኖር ነው የታየው፡፡የዚህ ቫይረስ ተሸካሚዎች በረዥሙ ሊያስቡ ካልቻሉ ሀገርና ትውልድ ይዘው
ይጠፋሉ፡፡
የሰው ልጅ ሁሉ እኩል ነው፤ወንድምና እህት ቤተሰብም ነው
በሚለው ታላቅ አክብሮትና መተሳሰብ መደጋገፍ በአብሮነት ነው የሚኖረው፡፡አሜሪካ የመላው አለም ሕዝብ በስደት ሄዶ በጋራ ለፍቶ
ያቆማት በሂደትም ለታላቅነት ያደረሳት ሀገር ነች፡፡የጠባብነትና የትምክህት በሽታ የለባትም፡፡ይህን ሀገርና ትውልድ ገዳይ የሆነ
በሽታ ሌላ ያልተጠበቀ አደጋ ከማስከተሉ በፊት መከላከል ግድ ይላል፡፡
ወደዚህ መንደርደሪያ የወሰደን በሰሞኑ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም
ለአለም የጤና ጥበቃ ድርጅት ዋና ዳይሬክተርነት ውድድር ቀርበው በነበረበት ሰአት በውጭ በሚኖሩ ጽንፈኛና አክራሪ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የተንጸባረቀው አሳፋሪ ሁኔታ
ነው፡፡ኢትዮጵያ ከትልቅነት ታሪክዋ ወደ ድህነት ተረጂነት ተመጽዋችነት አዘቅት የወረደችው በእርግጥ የውጭ ኃይሎች እጅና ሴራ
በአብዛኛው ቢኖርበትም ዋናው የሀገራችን ውድቀት መንስኤ የራስዋ ልጆች ናቸው፡፡ዝንተ አለም በእርስ በእርስ ጦርነትና መባላት
በሚደረጉት ጦርነቶች መንስኤነት ነው ሀገሪቱ ውድቀት ውስጥ ገብታ
የኖረችው፡፡
ስለሀገርና ስለጋራ ትልቅነት ከማሰብ ይልቅ በጎጥና በመንደር
ማሰብ እርስ በእርስ መባላት ነው ሀገሪቱን ገድሎአት
የኖረው፡፡ይህንን ለዚህ ዘመን የማይመጥን ልክፍትና በሽታ ዛሬም አልተገላገልነውም፡፡እያገረሸ ዳግም የሀገር አደጋ ሁኖ
ተከስቶአል፡፡በአጭሩ ሳይሆን በረዥሙ ማሰብ ተስኖናል፡፤ከእኛ በኃላ የነበሩ ሀገራት ሁሉ ቀድመውን ሲሄዱ ከፊት መስመር ሲገኙ
እኛ በአለም የጥንታዊነት ታሪክ የፊተኞቹ የነበርነው ወደኃላ የቀረንበት ምስጢር ይሀው ነው፡፡ከዚህ የሞተ አስተሳሰብ መውጣት ካልቻልን
ለሀገራችን ለሕዝቡም አስፈሪ አደጋነቱ ይቀጥላል፡፡
ሲሆን ሲሆን ከአንዲት በቀደመ ታሪክዋ በድህነትና በኃላቀርት
በተረጂነት ከምትታወቅ ዛሬ ደግሞ የተሻለ ተስፋ ሰንቃ በልማትና በእድገት አለምን እያስደመመች ካለች ሀገር ከኢትዮጵያ አንድ
ሰው ብቁ ሆኖ ተገኝቶ በአለም መድረክ ለውድድር ሲቀርብ እንደ ዜጋም እንደ ሀገርም እንደሕዝብም ደስታችን የላቀ መሆን ይገባው
ነበር፡፡ዶ/ር ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን ብቻ አይደለም ወክለው የተወዳደሩት፡፡መላውን አፍሪካና የአፍሪካን ሕዝብ ጭምር ነው፡፡አፍሪካ
ከዚህ ቀደም የአለም የጤና ድርጅትን በአለም መድረክ ላይ ለመምራት አልበቃችም፡፡
ለዚህ ነው የመላው አለም መገናኛ ብዙሀን የመጀመሪያው አፍሪካዊ
በመሆን የአለም የጤና ድርጅትን በዋና ዳይሬክተርነት ለመምራት በአብላጫ ድምጽ መመረጣቸውን አቢይ ዜና አድርገው ለአለም
ያሰራጩት፡፡
ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም የአለም የጤና ድርጅት
ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተመረጡት በሙያቸው ባሳዩት ብቃትና ችሎታ በሀገራቸውም በጤናው ዘርፍ ስርነቀል ለውጥ ለማምጣት
በመቻላቸው ከዚህም ባለፍ በወባ በሽታ ላይ መፍትሄ ማስገኘት የቻሉ ተመራማሪ ሳይንቲስት በመሆናቸው ነው፡፡
የአለም ታላላቅ መሪዎች የነበሩ ስለብቃታቸው ምስክርነት
ሰጥተዋል፡፡ድፍን አፍሪካ በታላቅ ወገናዊ ስሜትና ፍቅር ለእኒህ ኢትዮጵያዊ ታላቅ ድጋፋቸውንና ድምጻቸውን
ሰጥተዋል፡፡ተወዳዳሪዎቻቸውን በከፍተኛ ደምጽ ማሸነፍ ችለዋል፡፡ይሄ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ከልብ ያስደሰተ ድል ነው፡፡
እንደተባለውም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለዶክተሩ ድልና ስኬት
መጫወት የሚገባትን ሚና በዲፕሎማሲው መስክ ተጫውታለች፡፡ስኬታማም ሆናለች፡፡የዲፕሎማሲው ስኬት ድልና ውጤትም ነው፡፡ያሸነፈችው
ኢትዮጵያ ነች፡፡ከምርጫው ውጤት በኃላ በአለም አደባባይ ገኖ ሲጠራ የዋለው ስም የኢትዮጵያ ነው፡፡ኢትዮጵያዊው ዶክተር ቴዎድሮስ
የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳሬክተር ሆነው ተመረጡ የሚለው ዜና አለምን ዳር አስከዳር ሸፍኖታል፡፡
የአሸነፈችው አፍሪካ ነች፡፡
ኤድስ አፍ አውጥቶ ስንትና ስንቱን ዜጋ በቀጠፈበት የሞት
ጽልማሞት በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ባረበበት ወቅት ይህን ትውልድ የፈጀና የቀጠፈ በየቀኑ ለቀብር ያስወጣ የነበረ በሽታ በመከላከልና
በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ በማድረግ የእናቶችን ሞት በመቀነስ የጤና አገልግሎትን በመላው ሀገሪቱ በማስፋፋት ረገድ ቁልፉን ሚና
የተጫወቱት ዶ/ር ቴዎድሮስ ናቸው፡፡ለዚህ ታላቅ ስራ እውቅና ካልሰጠን ትልቅ ችግር ውስጥ ነን ማለት ነው፡፡ዶክተሩ እንዲመረጡ ያበቃቸው
የስራ ውጤታቸው እንጂ የገዥው ፓርቲ አባል ስለሆኑ አይደለም፡፡
ጎልቶ የወጣው በግለሰብነታቸው የሰጡትና ከአሁን በኃላም
ተመርጠው ባሉበት ቦታ በኢትዮጵያ ያሳዩትን ብቃትና ተሞክሮ በመላው አለም ላይ በስራ እንዲያውሉት የተሰጠ እወቅናም ጭምር
ነው፡፡በውድድሩ ወቅት ጽንፈኛ ኢትዮጵያውን ተቃዋሚዎች እጅግ አሳፋሪ በሆነ ተቃውሞና የስም ማጥፋት ዘመቻ ተጠምደው ከርመዋል፡፡
ሀገርን ሕዝብን ስርአትን መለየት ተስኖአቸው ጥላቻቸው አፍጥጦና
ገጦ ወጥቶአል፡፡እንደ ሀገር እንደ ሕዝብ እንደ ዜጋ ያሳፍራል፡፡አንገትም ያስደፋል፡፡በእርጋታ ቢያስተውሉት ኖሮ ኢሕአዴግን
መቃወም መብታቸው ቢሆንም ስርአቱን ወደዱትም ጠሉትም ኢትዮጵያ የሚለው ስም የእነሱም መታወቂያ ክብራቸውና የማንነታቸው መለያ ነበር፡፡ኢትዮጵያ
ለሚለው ስምዋ ብቻ በየትውልዱ ፈረቃ ስንትና ስንት የደም መስዋእትነት እንደተከፈለላት ስምዋ ሲጠራ የሚነዝራቸው ለሀገራቸው
ያላቸው ፍቅር ድንበርና ወሰን የሌለው በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕዝቦች ያሉ መሆናቸውን እነዚህ ሰዎች አያውቁም ማለት
አይቻልም፡፡
ዶክተሩ በአለም አደባባይ የተወዳደሩት ኢሕአዴግን ወክለው
አይደለም፡፡ታላቅዋን ሀገር ኢትዮጵያንና ኩሩና ጀግና ሕዝብዋን ወክለው ነው፡፡ይሄንን መናገር አስፈላጊም አልነበረም፡፡የጥላቻ
ፖለቲካ ሀገርና ትውልድ ገዳይ ነው፡፡አይበጀንም አይጠቅመንም፡፡ በእርግጥ ኢሕአዴግን በመደገፍ ስም በየማሕበራዊ ድረገጹ የከፋ
ዘረኝነትን ሲያራምዱና ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጭ ጸያፍ ስድብ ሲነዙ የሚጽፉትንና የሚናገሩትን እስከማጣት የደረሱ አቅላቸውን
የሳቱ ብስለትና ማስተዋል የሚባል ነገር ጭርሱንም ያልፈጠረባቸው ጨዋነት የጎደላቸው ግለሰቦች ታይተዋል፡፡ይሄም አይጠቅምም፡፡መዘዙ
ብዙ ነው፡፡
እነዚህ ግለሰቦች ኢሕአዲግንና የተሀድሶ ለውጡን አይወክሉም፡፡ታድሰናል
ቢሉም የተለመደው ጭቃቸው ውስጥ እየተርመጠመጡ ድርጅቱንም ከሕዝብ ጋር እያጋጩት ይገኛሉ፡፡ይህ ለኢሕአዴግም ትልቅ አደጋ ነው፡፡በየትኛውም
ጎራ ያለጽንፈኝነት የዘረኝነት ልክፍት ለኢትዮጵያና ለሕዝብዋ አይጠቅምም፡፡ኢሕአዴግም በራሱ ጎራ ውስጥ ያሉትን በሽተኞች አንድ
ሊላቸው ይገባል፡፡በሌላው ጎራ ሁኖ የሚጽፈው የሚጠየቀውን ያህል እነዚህ ኢሕአዴግን ከሕዝቡ ጋር ዳግም ሊያባሉት የተነሱትን
ትናንሽ አስተሳሰብ የተጠናወታቸውን ስለሰፊዋ ሀገርና ሕዝብ
ከማሰብ ይልቅ በመንደርተኝት እሳቤ የሚያቅራሩትን እንዲታቀቡ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ድጋፍ ሳይሆን የከረረ ተቃውሞ እንዲወለድ
ምክንያት እየሆኑ ነው፡፡
እሳት በማንደድ ጥላቻን በማዛመት ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ከፌስ
ቡክና ከድረገጾቻቸው ማየቱ ይበቃል፡፡ደጋፊ መሆን ምክንያታዊነትን በጨዋ መልኩ መግለጽና ማስረዳትን ይጠይቃል፡፡ዛሬ ለሀገራችን
የሚያስፈልገው በጎሳና በጎጥ እሳቤ መርመጥመጥ አይደለም፡፡ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች መብትና ክብር በዘላቂነት የተከበረባት
የጋራ ሀገር ለመፍጠር ነው እየተሰራ ያለው፡፡ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን በሚለው መሰረታዊ መርህ መሰረት ነው ኢሕአዴግ
የቀድሞ የሀገራችንን ታላቅነት ለመመለስ እየሰራ ያለው፡፡
ማጠቃለያ
ኢትዮጵያዊው ዶክተር ቴዎድሮስ አድሀኖም ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን
ወክለው በመወዳደር አሸንፈው የአለም የጤና ድርጅት ዋናዳይሬክተር ለመሆን በመብቃታቸው ደስታው የመላው ኢትዮጵያ ደስታው የመላው
አፍሪካ ሕዝብም ነው፡፡የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ አፍሪካዊ የአለም የጤና ድርጅት መሪ ሁነው በመመረጣቸው ድሉ ለኢትዮጵያ እጥፍ
ድርብ ድል ነው፡፡
No comments:
Post a Comment