ኢዛና ዘመንፈስ
የሳዑዲ ዓረቢያው መንግስት የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው ስደተኞች ሀገሩን
ለቀው እንዲወጡ ያስቀመጠው ቀነ ገደብ እያለቀ ነው፡፡ በዚህ መሰረትም ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ወደሀገራቸው እንዲመለሱ የማድረግ
ጥረት በተጠናከረ መልኩ እየተካሔደ ስለመሆኑ ነው የፌዴራሉ መንግስትና እንዲሁም የክልል መስተዳድሮች ከሚሰጡት ማብራሪያ መረዳት
የሚቻለው፡፡
አሁንም ድረስ ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ከሚገኙት የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው
ኢትጵያውያን ዜጎች መካከል ወደ አገር ቤት ለመመለስ ፈቃደኝነትን ያሳዩት ከአርባ ሺህ እምብዛም እንደማይበልጡ ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡
ይህ ማለትም ደግሞ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩት ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው ዜጎቻችን፤ የሳዑዲ ዓረቢያው መንግስት ያስቀመጠው ቀነ
ገደብ ከማለቁ በፊት ያቺን ሀገር ለቀው ለመውጣት ዝግጁ እንዳልሆኑ የሚያስገነዝብ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስትና
የየክልሎቹ የመስተዳደር አካላት፤ የጋራ ግንዛቤ ሊጨብጡባቸው የሚገባ መሰረታዊ ነጥቦች ሆነው ስለሚሰማኝ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት
ያላቸው ምክንያቶች አንስቼ የራሴን አስተያየት እሰጥ ዘንድ ተገቢ መስሎኛልና ነው እኔም ብዕር ከወረቀት ማገናኘቴ፡፡
እናም ከዚህ አኳያ መነሳት ያለበትን መሰረተ ሃሳብ አንስተን ለመወያየት
ስንሞክር፤ በቅድሚያ ወደ አዕምሯችን የሚመጣው ጥያቄ፤ ለመሆኑ ለምንድነው ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ከሚገኙትና ግን ደግሞ ሕጋዊ የመኖሪያ
ፍቃድ ከሌላቸው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አብዛኞቹ ቀነ ገደብ ከማለቁ በፊት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ የፈለጉ የማይመስሉት? የሚለው
ነው፡፡ ይህን የምልበት ዋነኛ ምክንያት ደግሞ፤ የባለፀዋ ዓረባዊት ሀገር መንግስት ከሁለት ወር በፊት ለመላው የዓለም ማህበረሰብ
ይፋ ያደረገው ቀነ ገደቡ ሲያልቅ፤ የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸውን የውጭ ዜጎች ሁሉ ከያሉበት እያደነ በመያዝ የሚያጉርባቸው 98 ያህል
አዳዲስ እስር ቤቶች እንደተዘጋጁም ተነግሯል፡፡ ይሁን እንጂ የኛዎቹ ወገኖች ይህን የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት ይፋዊ ማስጠንቀቂያ
ከቁብ የቆጠሩት አለመምሰላቸው ከማስገረምም አልፎ እጅጉን የሚያሳስብ ወቅታዊ ጉዳይ ስለመሆኑ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡
ምንም እንኳን ሳዑዲ ዓረቢያ ለ90 ቀናት የሚቆይ ገደብ ማስቀመጧን ካሳወቀች
ጀምሮ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ፤ እዚያች አገር ውስጥ የሚገኙትና የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው
ዜጎቻችን ዕድሉን እንዲጠቀሙበት ለማድረግ ያለመ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ የሚካድ ባይሆንም ቅሉ፤ እስካሁን ድረስ አዋጁን ተቀብለው
ሕጋዊ ምላሽ የሰጡት ወገኖቻችን ቁጥር በጣም ጥቂት መሆኑ ግን ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም፡፡ ከዚሁ የተነሳም “ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ
በሕገ ወጥ መንገድ የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ዜጎች ምናልባትም እስከ አምስት መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ይሆናሉ ተብሎ የሚገመት ሆኖ ሳለ፤
አርባ ሺህ ያህሉ ብቻ ናቸው ለመመለስ ፍቃደኝነትን ያሳዩት መባሉ ምንን ያመለክታል?” የሚለው ነጥብ እያነጋገረ ያለው፡፡
እንግዲያውስ በዚህ ጥያቄ ዙሪያ የየራሳቸውን አስተያየት ሲሰነዝሩ ከሚደመጡት
ወገኖች መካከል አብዛኞቹ የሚስማሙበት ምላሽ “መንግስት ከሳዑዲ ዓረቢያ ተባረው ለሚመጡት ዜጎቻችን የሚሰጠው ትኩረትና የሚያደርገው
ድጋፍ አናሳ በመሆኑ ምክንያት አገራችን ሔደን ከምንቸገር እዚሁ ጠግበን እየበላን ብንታሰር ይሻለናል ብለው እንዲያምኑ አስገድዷቸዋል”
የሚል ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህን የመከራከሪያ ነጥብ ሲያነሱ የሚደመጡት አስተያየት ሰጭዎች ሃሳባቸውን በምክንያት አስደግፈው ለማቅረብ
ሲሞክሩ የሚስተዋሉበት አግባብም ደግሞ “ለአብነት በ2006 ዓ.ም የሳዑዲ ዓረቢያ መንግስት በወሰደው ህገ ወጥ ስደተኞችን የማባረር
እርምጃ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለተደረጉት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ቃል የተገባላቸውን ያህል ትኩረት መስጠት ስላልተቻለ ሁሉም
እንደገና ተመልሰው በሕገ- ወጥ መንገድ ለመሔድ እንደተገደዱ ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት” የሚል ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡
እኔ በግሌ ከዚህ አኳያ የሚገለፅ ቅሬታ ያላቸው ወገኖች የሚያነሱትን የመከራከሪያ
ሃሳብ የሰማሁት፤ በተለይም ዛሚ 90.7 ኤፍ.ኤም.ሬድዮና እንዲሁም ደግሞ ፋና 98.1 ሬድዮ ጣቢያዎች፤ ከሰሞኑ አየር ላይ ካዋሉት
በሳዑዲው ጉዳይ ዙሪያ የሚያጠነጥን የአድማጮቻቸው የቀጥታ ስርጭት ውይይት ላይ ነው፡፡ ይልቁንም ደግሞ አንዲት በቅርቡ ከሳዑዲ ዓረቢያ
እንደተመለሱ የተናገሩ የገርጂ ነዋሪ ሴት “… ማን ያርዳ የቀበረ” እንደማለት የሚቆጠር ቅኝት ያለውን አስተያየት ሲሰጡ የተደመጡበት ተመሳሳይ ሃሳብ፤ በእርግጥም “ሕገ-ወጥ ስደተኞች ናችሁ”
ተብለው የሚባረሩ ወገኖቻችንን የምንቀበልበት አግባብ መጤን እንዳለበት የሚያመለክት ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡
በግልፅ አነጋገር፤ ከዚህ ቀደም የሳዑዲ ዓረቢያው መንግስት በወሰደው ተመሳሳይ
ሕገ-ወጥ ስደተኞችን ከሀገሩ የማባረር እርምጃ ምክንያት ለተመለሱት ኢትዮጵያውያን ዜጎች እዚህ ከመጡ በኋላ ይደረግላቸዋል የተባለው፤
በሀገር ውስጥ ሰርተው እንዲኖሩ የሚያበረታታ ድጋፍ ከቃል ያለፈ ሳይሆን ቀርቶ “የማዝነው አንተ ስለዋሸኸኝ አይደለም፤ ይልቅስ እኔ
ዳግመኛ ላምንህ ስለማልችል እንጂ” የሚያሰኝ አሉታዊ ውጤት ማስከተሉን ነው የአስተያየት ሰጭዎቹ ቅሬታ የሚያመለክተው፡፡ ስለዚህም
እንደኔ መረዳት ከሆነ፤ አሁን ላይ እየተስተዋለ ያለውን ተጠቃሽ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ይቻል ዘንድ፤ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ
የተፈፀሙ የአምና - የካቻምና ስህተቶቻችንን ሁሉ፤ በማያሻማ መልኩ አምኖ መቀበልና እንዲሁም እንደማደገሙ ማረጋገጥ ይጠበቅብናል
ባይ ነኝ፡፡
ይህን ስልም ደግሞ፤ እዚሁ አገር ውስጥ ተፍጨርጭረው ድህነትን ለማሸነፍና
ለኢትዮጵያ የህዳሴ ጉዞ መሳካትም ጭምር የየራሳቸውን ዜግነታዊ በጎ አስተዋፅኦ ለማበርከት ከመጣር ይልቅ በባሌም፤ በሞያሌም፤ በሶማሌም
ድንበር አቋርጠው እየወጡ ወደየትም ሲሰደዱ በሚስተዋሉት ወጣት ዜጎቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን ፈርጀ ብዙ ጉዳት ስለማስቀረት ሲነሳ፤
ፈፅሞ ቸል መባል የማይኖርበት ቁልፍ ነጥብ መስሎ የሚሰማኝ ጉዳይ፤ በተለይም የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን ትርጉም ላለው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም
ስለማዋል አስፈላጊነት ሀገራዊ የጋራ መግባባትን መፍጠር እንደሚጠበቅብን መተማመን የሚያሻ መሆኑ ነው፡፡ ያን የማድረጉ ጥረት የሚጀመረውም፤
ይህቺን የጋራ ቤታችን ናት የምንላትን ሀገራችንን የሚመለከት ማንኛውም ርዕሰ ጉዳይ ሲነሳ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በዕኩል የኃላፊነት
ስሜት የመሰለውን የመፍትሔ ሃሳብ የማቅረብ ሕገ-መንግስታዊ መብትና ግዴታውን ይወጣ ዘንድ የሚጋብዝ ተጨባጭ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ሲቻል
እንጂ እንዲሁ ስለፈለግን ብቻ አይደለም፡፡ ስለዚህም እንደኔ እንደኔ አሁን በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙትን የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው
ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ያለመጥረት እየተደረገ ያለበት አግባብም ዘላቂ መፍትሔ በሚያመጣ መልኩ
መቃኘት ይጠበቅበታል፡፡
በዚህ ረገድ ጉዳዩን እንደመልካም አጋጣሚ ልንጠቀምበት እንደምንችልም ጭምር
አስተያየታቸውን የሚለግሱ ሰዎች አሉ፡፡ እናም እንደነርሱ እምነት ከሆነ፤ በተለይም ተገቢው የክትትልና የቁጥጥር ስራ ሰንሰለት ባለመዘርጋቱ ምክንያት ወደ የመንግስት ካዝና መግባት ይገባው
የነበረውን መጠነ ብዙ የህዝብ ሀብት፤ ጥቂት የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ መሪ ተዋናይ ግለሰቦች የሚመዘብሩበት አሰራር ላይ
ትርጉም ያለው የእርምት እርምጃ መውሰድ ከተቻለ፤ ከዘራፊዎቹ ሙሰኞች
ላይ በሚመለሰው ገንዘብ ብቻ ከሳዑዲ ዓረቢያ የሚመጡ ወገኖቻችንን የሚያቋቁም ዘላቂ ልማት መፍጠር አያዳግትም ባይ ናቸው አስተያየት
ሰጭዎቹ፡፡ በእርግጥም ደግሞ ከዚህ የተሻለ ተመራጭ የመፍትሔ አቅጣጫ መጠቆም የሚቻል አይመስልምና የአስተያየት ሰጭዎቹ ምክር ችላ
ሊባል አይገባም እላለሁ፡፡
ምክንያቱም፤ እርምጃው ያለአግባብ የተዘረፈውን የህዝብ ወይም ደግሞ የመንግስት
ሀብት ንብረት ማስመለስ ብቻም ሳይሆን፤ የኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካ ኢኮኖሚ በሚያሳድረው ፈርጀ ብዙ የመልካም አስተዳደር ችግርን
የሚያባብስ አሉታዊ ተፅእኖም ጭምር እየተማረሩ ሀገር ጥለው ለመሰደድ የተገደዱ ዜጎቻችንን ወደየ ትውልድ ቀያቸው እየመጡ ከህዳሴው
ዘመን ኢትዮጵያ ልማት እንዲቋደሱ የሚያደርግ እንደመሆኑ መጠን፤ ፍትሐዊነቱ ሀገራዊ መግባባትን እንደሚጋብዝ ይታመናልና ነው፡፡ ስለዚህ
በተለይም የቡና ንግድ ላይ የተሰማሩ “ኤክስፐርቶች” የሚፈፅሙት የታክስና ግብር ማጭበርበር እያስከተለ ያለውን ዓይነት ኪሳራ ጨምሮ፤
ሌሎችም የመንግስት የልማት ድርጅቶችና እንዲሁም ደግሞ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጭምር፤ በዋዛ ፈዛዛ ምክንያት የጥቂት ህሊና ቢስ
ግለሰቦችን ኪስ የሚያደልቡበት በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ገንዘብ፤ ለእንደዚህ ዓይነቱ የሀገሪቱን ዜጎች ሊያጋጥማቸው ከሚችል እንግልት
እና ማህበራዊ ቀውስ ለሚታደግ ቁምነገር ሲውል ማየት የጋራ መግባባትን መፍጠሩ እንደማይቀር ከወዲሁ መገመት ስለማያዳግት፤ ይታሰብበት
የሚል ነው የኔም አቋም፡፡
አለበለዚያ ግን፤ ዛሬም ልክ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ከሳዑዲ ዓረቢያ ተባረው
ስለመጡ ወገኖቻችን ተናግረን ሳናበቃ እነርሱ እንደገና በሕገወጥ መንገድ ተመልሰው እየሔዱ ጥረታችንን ውሃ ወቀጣ አድርገውት እንደማይቀሩ
ምንም ዓይነት ዋስትና የለንም፡፡ ስለሆነም፤ ሳዑዲት ዓረቢያ ውስጥ የሚገኙትን ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ዜጎች
ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ ለማድረግ ያለመ ጥረት ላይ የሚገኘው ብሔራዊ ግብረ ኃይል፤ የተጣለበትን ሃላፊነት ለመወጣት ይችል ዘንድ፤
የተመላሾቹን ወገኖች ችግር በዘላዊነት የሚቀርፍ መፍትሔ መስጠትን ያካተተ አቀባበል ሊያደርግላቸው እንደሚገባ ነው ለማስገንዘብ የምወደው፡፡
በተረፈ አንድም ዜጋችን ቢሆን ላልተገባ እንግልት መዳረግ አይኖርበትም የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡ እናም መጭው ጊዜ መላው ኢትዮጵያውያን
ህዝቦች ለጋራ የሀገራዊ የህዳሴ ጉዟችን ስኬት እጅ ለእጅ ተያይዘን የምንረባረብበት ብሩህ የፈጣን ልማት ዘመን እንጂ በሕገ-ወጥ
ስደት ምክንያት ለፈርጀ ብዙ ጉዳት ስንዳረግ የሚስተዋልበት እንደማይሆን ያለኝን ተስፋ እየገለፅኩኝ፤ ለዛሬ ያነሳሁትን ሃሳብ እዚህ
ላይ አበቃለሁ፡፡
No comments:
Post a Comment