Friday, 9 June 2017

ድሉን ጠብቆ ለመዝለቅ !!



          
                                                           ታከለ አለሙ
የግንቦት ሀያ ድል ሲታሰብ በሀገር ደረጃ አብሮ ያመጣቸው ሰፋፊ ስኬቶችና ድሎች አብረው ይዘከራሉ፡፡ኢትዮጵያ በፈጣን የኢኮኖሚ ልማትና እድገት ውስጥ እንድትራመድ ያስቻላት በሀገር ደረጃ ብዙ ተብለው የሚገለጹ ድሎች ባለቤት ለመሆን የበቃችው ግንቦታውያኑ ባመጡት ስርነቀል ለውጥ ነው፡፡አዲሱ ሕገመንግስት የፕሬስ ነጻነትን በኢትዮጵያ እውን እንዲሆን አውጆ ሳንሱር በሕግ እንዲወገድ አድርጎአል፡፡ ይህን ተከትሎም በኢትዮጵያ ታሪክ አይነተ ብዙ የግል ፕሬሶች ሕጋዊ ፈቃድ አግኝተው ለማበብ ችለው ነበር፡፡እንደዛሬ ቁጥራቸው ተመናምኖ በጣት የሚቆጠሩ ሳይቀሩ፡፡
አንዱና ትልቁ የግንቦት ሀያ ትሩፋት ተደርጎ የሚወሰደው የፕሬስ ነጻነት ዛሬ ቀድሞ በነበረበት ደረጃ ላይ አይደለም ያለው፡፡ይህ ሊያሳስብ የሚገባው ጉዳይ የሆነው ዳግም የኃሊት ጉዞ በመጀመሩ ነው፡፡ኢህአዴግ ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል፡፡መድበለ ፓርቲ ስርአት የተፈጠረው ለመጀመሪያ ግዜ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን በሕጋዊ መልኩ አደራጅተው ሕጋዊ ፈቃድ ወስደው እንዲሰሩ ያስቻለው በዚሁ ስርአት ነው፡፡ ምን ያህል ውጤታማ ሁነዋል የሚለው ራሱን ችሎ ጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚገባ ነው የሚሆነው፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ አምስት አመቱን እየጠበቀ ብሔራዊ ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡ በአንደኛውና በሁለተኛው ዙር ምርጫ ተቃዋሚዎች በሕዝብ ተመርጠው ፓርላማ ለመግባት የቻሉበት በዚህም የተለያዩ ሀሳቦችና ደማቅ ውይይቶች ሕዝብ ጆሮ ይደርሱ የነበረበትን ሁኔታ እናስታውሳለን፡፡ሊበረታታ ሊቀጥልም ይገባው የነበረ ነው፡፡
በተካሄደው ብሔራዊ ምርጫ ማግኘት የሚገባንን ድምጽ ገዢው ፓርቲ በኃይል ነጥቆናል፤ምርጫው የተጭበረበረ ነው የሚለው የተቃዋሚዎች ድምጽ ተሰምቶ የነበረ ቢሆንም ምርጫው ግዜውን ጠብቆ መካሄዱ ራሱን የቻለ አንድ በሀገር ደረጃ የሚወሰድ እድገትና ለውጥ ነበር፡፡ሀገሪቱ መከተል የጀመረችውን የነጻ ገበያ ኢኮኖሚ ተከትሎ የሀገር ውስጥና የውጭ ኢንቨስተሮች በስፋት ሀብታቸውን በሀገሪቱ ማፍስስ መቻላቸውም የግንቦት ሀያ ድልና ውጤት ነው፡፡
በዚህም መሰረት በርካታ የውጭ ሀገር ባለሀብቶች በተለያየ ዘርፍ ኢንቨስት ለማድረግ ኢትዮጵያን ካላት የአየር ንብረት ሰፊ የሰው ኃይል አስተማማኝ ከሆነው ሰላምና  ጸጥታዋ በመነሳት ቀዳሚና ተመራጭ ሀገር አድርገዋታል፡፤ብዙ በሆኑ መስኮች በማእድን በጨርቃጨርቅ ወዘተ ዘርፎች ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆነ የአውሮፓና የኤሽያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት አድርገዋል፡፡እያደረጉም ይገኛሉ፡፡
በሀገራችን ውስጥ ሰፊ መሰረተ ልማት ዝርጋታ የተካሄደው ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ ደረጃቸውን የጠበቁ መንገዶች በአዲስ አበባና በክልሎች የተስፋፉት መካከለኛና ከፍተኛ ግድቦች የተሰሩት ከግንቦታውያኑ ድል በኃላ ነው፡፡
የግል ድርጅቶች ባንኮች ኢንሹራንሶች ኮሌጆች ትላልቅ የግል ካምፓኒዎች በሀገር ውስጥ የተስፋፉት ለዜጎችም የተለያዩ ስራዎች የተከፈቱት በዚሁ ዘመን ነው፡፡በእርግጥ የሕዛባችን ቁጥር ከተገመተው በላይ ማደግ ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የሚሰራውን ያህል በበቂ ሁኔታ ስራን ለማዳረስ አልቻለም፡፡አሁንም ወጣቱን የስራ ባለቤት ለማድረግ በመንግስት በኩል የአስር ቢሊዮን ካፒታል በጀት ተመድቦ ለሁሉም ክልሎች ተከፋፍሎ ወጣቱ የራሱ ስራ ባለቤት እንዲሆን ይህ ቀረው የማይባል ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ቀድሞ በነበሩት መንግስታት ከውጭ በነበረባት ከፍተኛ ጫና የተነሳ የአባይን ወንዝ በመገደብ ተጠቃሚ እንዳትሆን ከፍተኛ አለም አቀፍ ጫና እየደረሰባት አለምአቀፍ ብድር እንዳታገኝ በአባይ ወንዝ ውሀ ላይ ግድብ እንዳትሰራ ሲደረግ ኖሮአል፡፡ይህንን ትውልድና ሀገርን አንቆ ይዞ የኖረውን ማነቆ በጥሶ የጣለው በዚህም ኢትዮጵያ በአባይ ውሀ ላይ ታላቅ ግድብ እንድትሰራ መሰረቱን የጣለው ተጀምሮም ዛሬ የደረሰበት እንዲደርስ ያደረገው የግንቦታውያኑ ድል ውጤት ነው፡፡
ይህ ግድብ ሙሉ በሙሉ የተሰራውና ተሰርቶም የሚጠናቀቀው ያለምንም የውጭ እርዳታና እገዛ በራሳችን ገንዘብና ሀብት መሆኑ ሕጻናትን ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያለውን ያዋጣበት የከፈለበት እንጀመርነውም ለመጨረስ ይሄንኑ የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ስራው የሚጠናቀቅ በመሆኑ ታላቅ ብሔራዊ ኩራትና ክብር እንዲሰማን ያደረገ ነው፡፡የአባይን ግድብ ለመገደብ ኢትዮጵያ ድሀ ሀገር ስለሆነች አትችልም ብለው ተሳልቀው ነበር፡፤በድርቅ ተረጂዎችና በረሀብ የሚታወቁ ስለሆነ አባይን ለመገደብ በፍጹም አይችሉም ብለው አስብም ነበር፡፡
የግድቡ መሰረት ተጥሎ ግንባታው ሲጀመር ግብጽ ከፍተኛ መንጫጫት ነበር የፈጠረችው፡፤ለማስቆምም ጥረት አደርገዋል፡፡የግድቡን ግንባታ የጀመረው ባለቤቱና ዳር የሚያደርሰውም ሕዝቡ ስለሆነ ሰሚና አድማጭ አላገኙም፡፡ግንባታው ለአንዲት ደቂቃ ስራው ሳይደናቀፍ እነሆ ዛሬ ላይ ደርሶአል፡፡ሌሎችም ከፍተኛ ግድቦች ተገንብተዋል፡፡የኢትዮጵያን የማደግ ተስፋ በግላጭ የመሰከሩ ናቸው፡፡የግል ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች በስፋት ተስፋፍተዋል፡፡
ቀድሞ አራት የነበሩት የሀገራችን ዩኒቨርስቲዎች ዛሬ ከ35 በላይ አድገዋል፡፡በጤናውም መስክ በአለማችን ውስጥ እጅግ አሰፈሪ ሁኖ የተከሰተውን የኤችአይ ቪ ኤድስ በሽታ ለመግታት ሀገራችን ባወጣችው የጤና ፖሊሲ ውስጥ አካታ ሰፊና ያልተቋረጠ ዘመቻ በማድጓ አሳሳቢውን ችግር ለመቀልበስና አደጋውን ለመቀነስ ችላለች፡፡የእናቶችንና የሕጻናትን ሞት ለመቀነስም የቻለች ሀገር ነች፡፡
በጤናው ረገድ ብዙ ሆስፒታሎችን ከፍተኛ ክሊኒኮችን በአዲስ አበባና በክልሎች አስፋፍታለች፡፡ሕዝቡ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ተጠቃሚ እንዲሆን አስችላለች፡፤ የግል ሆስፒታሎችና ክሊኒኮችም በብዛት ተስፋፍተዋል፡፡አየር መገዳችን በብዛት የዘመናዊ አውሮፕላኖች ባለቤት ለመሆን የበቃበት ተመራጭና ተወዳዳሪነቱ በአለም ደረጃ የጎላበት የስታር አሊያንስ አባል የሆነበት በተደጋጋሚ በአፍሪካና በአለም ደረጃ የተሸለመበት ውጤት ነው የተመዘገበው፡
በአዲስአበባ ታሪክ ለመጀመሪያ ግዜ ቀላል የሆነ የከተማ የባቡር አገልግሎት የተዘረጋበት ይሀው የባቡር አገልግሎትም ወደ ክልሎች የሚስፋፋበት ሁኔታም የተፈጠረበት ነው፡፡ረዥሙ የባቡር መስመር አገልግሎት የሆነው የጅቡቲ አዲስ አበባ ባቡር መስመር አገልግሎት በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ስራ ይጀምራል፡፡
በግብርናውም መስክ በሀገር ደረጃ ታላቅ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡አርሶአደሩንና አርብቶ አደሩን ስለዘመናዊ እርሻ የማስተማሩና የማሳወቁ ስራ በሰፊው በመሰራቱ ከፍተኛ  ለውጥ ተመዝግቦአል፡፡የመስኖ ልማትን በመጠቀም ድርቅን ለመከላከል ከማስቻሉም በላይ የጓሮ አትክልትን በማልማት ለራሱና ለቤተሰቡ ከማዋል አልፎ ወደገበያም በማቅረብ ተጠቃሚ ለመሆን ችሎአል፡፡ተራቁቶ የነበረውን የሀገሪቱን መሬት በደን ለመሸፍን በበርካታ አመታት በተሰራው የተፈጥሮ ጥበቃ ስራ አግጥጠው የነበሩ ተራሮች ዛሬ ላይ በደን ተሸፍነዋል፡፡
ጠፍተው የነበሩ መኖሪያ አጥተው ተሰደው የነበሩ የዱር አራዊቶችና አእዋፋት ወደተፈጥሮ ቦታቸው እየተመለሱ ይገኛሉ፡፡ይሀው በየአመቱ በእቅድ የሚሰራው የችግኝ ተከላና የደን እንክንካቤ ስራ በተጠናከረ መልኩ የቀጠለ ሲሆን በሀገር ደረጃ ትርጉም ያለው ለውጥ በማስገኘት ላይ ይገኛል፡፡ትምሕርትን በሀገር ደረጃ በሰፊው ለማስፋፋት በተደረገው ርብርብ ዛሬ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በከተማና በገጠር የሚገኙ ወጣቶች በትምህርት ገበታቸው ላይ ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵ ዘመናዊ አለምን የሚያዳርሱና የሚያካልሉ ከፍተኛ የመሸከም አቅም ያላቸው የንግድ መርከቦችም ባለቤት ነች፡፡የመከላከያ ሠራዊትዋ የራሱን ብሔራዊ ድንበርና የአየር ክልል ከማስከበርም አልፎ በአለም አቀፉ የሰላም ማስከበር ግዳጅ ላይ ተመራጭ በመሆኑ የተባበሩት መንግስታትን ተልእኮ በመወጣት ረገድ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ኢትዮጵያ በአለም በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ከሚገኙት አስር ሀገሮች አንድዋ በአፍሪካ ደረጃም በገነባቻቸው ግዙፍ መሰረተ ልማቶች የውጭ ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ደረጃ ለመሳብ በመብቃትዋ በቀዳሚነት ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት ዋና መቀመጫ የአውሮፓ ሕብረት ጽሕፈት ቤት ከኒውዮርክና ከቤልጂየም ቀጥሎ ሶስተኛዋ መቀመጫ ሀገር ለመሆን የበቃች በአፍሪካ ቀንድ ተሰሚና ተደማጭ ተጽእኖ አሳዳሪ ሀገር ለመሆን የበቃች ነች፡፡ እነዚህ ሁሉ ታላላቅ ድሎች የግንቦታውያኑን ድል ተከትሎ የተገኙ የሀገር ትሩፋቶች ናቸው፡፡
ትልቁ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነጥብ የተገኘውን ሀገራዊ ስርነቀል ለውጥና የኢኮኖሚ እድገት መሰረተ ልማት ተከትሎ የዛኑም ያሕል በገዢው ፓርቲ ውስጥ አድፍጠውና ተሸሽገው ሕዝቡን በአስተዳደር በፍትሕ በሙስና በኪራይ ሰብሳቢነት በምዝበራ ያማረሩትን ኃይሎች አበጥሮ በማውጣት የሕዘቡን ጥያቄ ለመመለስ ኢሕአዴግ የጀመረውን የተሀድሶ ለውጥ አቅሙን አጎልብቶ ሕዝቡንም ከጎኑ አሰልፎ ከዳር የማድረስ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ሕዝቡ በስፋት እየጠበቀው ይገኛል፡፡
በራሱ በኢህአዴግ ቋንቋ የሞት የሽረት ትግል ተካሂዶ የተገኙትን ሰፊ መሰረት ያላቸው ሕዝባዊና ሀገራዊ ድሎችና ስኬቶች መጠበቅ ካልተቻለ አስቸጋሪና አሳሳቢ እንደሚሆን ይታወቃል፡፡ተሀድሶው ሂደትና በየደረጃው የሚከወን በመሆኑ ግዜን ይጠይቃል፡፡ የሕዝቡን ጥያቄዎች በቀጥታ መመለስ ችግሩን ይፈታዋል፡፡የአመለካከትና የአስተሳሰብ ለውጥ ሊያመጡ የማይችሉና ተቸክለው የሚገኙ የአለምንም ሆነ ሀገራዊ ለውጥና እድገቱን ማንበብ የማይችሉ ወገኖች የአዲሱ ለውጥ አካል ሊሆኑ አይችሉም፡፡በትላንት በሬ ያረሰና ያመረተ የለም እንዲሉ፡፡
ትላንትን ብቻ በማስታወስና በማወደስ የሚኖርበት ግዜ ማለፉን መረዳት ከተሳናቸው ሞጋችና ጠያቂ የሆነውን ትውልድ ጥየቄ መመለስ አይችሉም፡፡ለውጥ ከግዜ ጋር መብቃትን ይጠይቃል፡፡በልዩነት ውስጥ ያለን ውበትና ጠንካራ አንድነት ከማሳደግና ከማጉላት ይልቅ ሁሌም ልዩነትን አግዝፈው መከፋፈልን የሚሰብኩ ወገኖች የዚህ ትውልድ አባልም ሆነ አካል መሆን አይችሉም፡፡
የግንቦት ሀያ ድል ሕያው ሁኖ እንዲቀጥል ሙሰኞችን ኪራይ ሰብሳቢዎችን በመልካም አስተዳደርና በፍትሕ ላይ አድልዎና መድልዎ ሲፈጽሙ የኖሩትን በሕግ ተጠያቂ ማድረግ  ሕዝብ የሚደግፈው ተገቢ እርምጃ ነው፡፡
የሕዝብን ተሳትፎ ማሳደግ፤ሰፊ የፕሬስ ነጻነት እንዲኖር ማድረግ፤የተቃዋሚዎችን ሀገራዊ ተሳትፎ ማሳደግ፤ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች እንዲሳተፉ ሀሳብ እንዲሰጡ ማስቻል ማወያየት፤ የሲቪክ ማሕበራትን አቅም ማሳደግ ማገዝ ሀገራዊ አስተዋጽኦ በብዙ መልኩ እንዲያደርጉ ማስቻል፤በተለይ የፐብሊክ ሚዲያው ንቁ ሆኖ በሕዝቡ መደመጥና መከበር እንዲችል የሕዝቡን ሕይወትና ጉዳዮች አጉልቶ እንዲያሰማ ለችግሮችም መፍትሄ እንዲያስገኝ የማድረግ ብቃቱን ማሳደግ ወሳኝነቱ የጎላ ነው፡፡
በሕገ መንግስቱ የተከለከለውን ሳንሱር በእጅ አዙር ለመተግበር የሚሹትን ሕጉንና ሕገመንግስቱን በራሳቸው ግንዛቤ ብቻ እየተረጎሙ ትክክለኛ ነን የሚሉት አመራሮች ራሳቸውን እንዲፈትሹ ማድረግ ተገቢ ነወ፡፡በግልጽ ውይይት በማመን ለማንኛውም ችግር መፍትሄ ሊያስገኝ የሚችል ሚዲያ መገንባት ወሳኝ ነው፡፡
ማጠቃለያ
የግንቦት ሀያን ድል በቀጣይነት ለማስቀጠል ሕዝብን ያስመረሩትን መሰረታዊ የሆኑትን ሙስናን፤የኪራይ ሰብሳቢነትን፤የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ችግርን ከስሩ ነቅሎ በመጣል ነው፡፡የተጀመረው ተሀድሶ ከዳር እንዲደርስ ኢሕአዴግ በቁርጠኝነት ሊገፋበት ይገባል፡፡

No comments:

Post a Comment