Monday, 6 February 2017

የትውልዱን የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎ ማሳደግ የህብረቱ ቁልፍ ተግባር ሊሆን ይገባዋል !!



ዮናስ

የአፍሪካ ህብረት 28 የመሪዎች ጉባኤ በህብረቱ መዲና፤ አዲስ አበባ ላይ ከሰሞኑ ተካሂዷል። የጉባኤው ዋነኛ አጀንዳም የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥን የተመለከተ እንደነበርም መረጃዎች አመላክተዋል።  
የአፍሪካ ወጣቶች ሁለገብ ተሳታፊነታቸውና ተጠቃሚነታቸው ካልተረጋገጠ የአፍሪካ ቀጣይ ዕድል ጥያቄ ውስጥ  ይገባል፡፡ አህጉሪቱን ከጦርነትና ከግጭት የጸዳች ለማድረግ የሚኖረው ብቸኛ አማራጭም ይኸው እና የወጣቶች ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት ያደረገ የመሪዎች ርብርብ በመሆኑ የዘንድሮው ጉባኤ ትክክለኛውን አጀንዳ መሰረት ያደረገ  ነው ብሎ ለመናገር ይቻላል። 
አፍሪካውያን እርስ በርስ መጋጨትንና ሙስናን አስወግደው መልካም አስተዳደርና ዘላቂ ልማት በማስፈን ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል በማንገስ  ወጣቱ ትውልድ ሚናውን እንዲያበረክት የሚያደርግ ፖሊሲዎች ማውጣት እስካልቻሉ እና ይህንንም በአስቸኳይ በተግባር ላይ ካላዋሉ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የአህጉሪቷ ችግር ወደከፋ ደረጃና ወደእርስ በእርስ ጦርነት ማምራቱ አይቀሬ ለመሆኑ በየሃገራቱ ፍንጮች እየታዩ በመሆኑም ጭምር ነው የዘንድሮው አጀንዳን ተገቢና ወቅቱን የጠበቀ ነው የሚያስብለው።
አሁን ሁሉም የአፍሪካ ልጆች ሳይጠራጠሩ የሚያምኑት አንድ ነገር ቢኖር አፍሪካ በወጣት ልጆቿ መታነፅ እንዳለባት መሪዎቹ  አምነው ካልሰሩና ጠንካራ መሰረት እስካልጣሉ ድረስ በቅርብ ጊዜ ውስጥ አህጉሪቱ ውድቀት ሊያጋጠማት የሚችል እንደሆነ ነው
ሌላኛውና ወጣቶችን ታሳቢ ላደረገው አጠቃላይ የአህጉሪቱ መርህ ምክንያት የሚሆነው በአፍሪካ ያለው ትውልድ አብዛኛው 15 እስከ 64 ዕድሜ ክልል የሚገኝ አምራች ሃይል መሆኑ ነው ። ስለሆነም ሃገራት እንደሃገር እና አፍሪካም እንደአህጉር ለወጣቶች የሙያ ስልጠና በመስጠት አቅሙን በማሳደግና በማደራጀት አምራች የሚሆንበትን እድል መፍጠር እና በዚህም የትውልዱን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎ ማሳደግ  ይገባል ።  

ወጣቱ በኢንዱስትሪ ዘርፍና በተለይ ደግሞ በትላልቅ የመንግስት ማኒፋክቸሪንግ ፕሮጀክቶች በማሳተፍ የተለያዩ ክህሎቶች ቀስሞ እንዲወጣ ጊዜና ጉልበቱን በስራ እንዲያሳለፍማድረግ ረገድ ትልቅ ሃላፊነት ሊሸከም ይገባው የነበረው ህብረት እስከዛሬ መዘግየቱ ቢቆጭም አረፈደምና አያንገበግብም፡፡
የአፍሪካ አህጉር መሪዎችም ሆኑ ጉባኤተኞቹ  ወጣቶችን በመንግስታዊ መዋቅሮች በማሳተፍ የስራ ልምድ እንዲቀስሙ ማድረግ እና ወደ አመራር እንዲመጡ ማስቻል ይጠበቅብናል ሲሉ በአንድነት መናገራቸውም ይህንኑ ስጋት የሚያረጋግጥና ስለአህጉሪቱ ሰላምና ብልጽግና ብቸኛው አማራጭ ይኸው የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎ ማሳደግ ስለሆነ ነው ።
በእርግጥ አህጉሪቱ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በሰላምና ጸጥታ ረገድ አንጻራዊ  መሻሻሎች አሳይታለች፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ሃገራት በነጠላ ለወጣቶቻቸው ፖሊሲ በመቅረጽ እና ወደተግባር በመለወጥ በመንቀሳቀሳቸው ነው።አሁን ደግሞ ብዙም አስቸጋሪ ነገር የለም።ከህብረቱ የሚጠበቀው ይህን ተሞክሮ ማስፋት ነው።
አህጉሪቱ 2063 የበለጸገችና የለማች አፍሪካ ለማየት የነደፈችውን ራዕይ ለማሳካት በሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ላይ ሰላምን ማስፈንና ማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ሰጥታ መስራት የምትችለው ወጣቶቿን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎ ማሳደግ ስትችል ብቻ ነው ፡፡ 
የህብሩቱ ጉባኤ በአህጉሪቱ ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ ወጣቶችን ለማሳተፍ መወሰኑ ለአህጉሪቱ ትልቅ ትርጉም አለው ። ከላይ በተመለከተው አግባብ በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት ቢኖርም አብዛኛው ያልተማረና ያለስራ የሚኖር በመሆኑ የወደፊቷ  አፍሪካ ዕጣ ፈንታ ባለቤት የሆነውን አምራች ሃይል ማዕከል ያደረገ ሥራ የህብረቱ ቁልፍ ተግባር ሊሆን ይገባል ፡፡
ለዚህ ደግሞ ከህብረቱ መቀመጫ ሃገረ ኢትዮጵያ ተሞክሮ መውሰድ ይገባል ። በአለም አቀፉ ድርጅትም ሆነ በምጣኔ ሃብታዊ አለም አቀፍ ተቋማት ዘንድ ኢትዮጵያ ወጣቶችን ያሳተፈ ስራ በመስራት ቀድማ የምትጠቀስ ናትስለሆነም ለወጣቱ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር የስራ ባለቤት ማድረግ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆንማስቻልን ልምድና ተሞክሮ አዲስ አበባ ላይ ያለው የህብረቱ ጽ/ቤት ወደመላው የአህጉሪቱ አባል ሀገራት ማስፋት ቁልፉ ተግባር ሊሆን ይገባዋል፡፡ 
እነዚህን ተግባራት ወደመሬት ማውረድ እንዲቻል ደግሞ አፍሪካ አንድነቷን የሚያረጋግጥ ፣ልማቷን የሚያፋጥን ሰላሟን የሚያሰፍን ጠንካራ አመራሮች ጎን ለጎን ማምረት ይጠበቅባታል፡፡ከወትሮው በተሻለ መነቃቃት ላይ ያለችውና የሌሎችን ቀልብ በመሳብ ዓለም ዓቀፍ ተደማጭነቷ እየጨመረ የመጣችው አህጉር ተደማጭነቷ ዘላቂነት የሚኖረው በዚህ መልኩ ብቻ መሆኑንም ጉባኤተኞቹ በአንድነት መስማማታቸውም ስለዚህ ነው። መምጣቱንም ጠቁመዋል፡፡
በነገራችን ላይ የሞሮኮ ዳግም ወደ ህብረቱ አባልነት መመለሷና እንደ ቻይና ያሉ ያደጉ ሀገራት አፍሪካን  የኢንቨስትመንት መዳረሻ ማድረጋቸው የአህጉሪቱን ትንሳኤ ማሳያ ነው፡፡
የአፍሪካ ህብረት መሰረታዊ ውድቀት መነሻዉ የአፍሪካ ህብረት መሪዎች የሚወስኑዋቸዉ ዉሳኔዎችን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ አለመቻሉና አፍሪካዊያን በአፍሪካ ህብረት ዙሪያ ያላቸዉ የተዛባ አመለካከት፤የአፍሪካ ህብረት ለአፍሪካዊያን አስፈላጊ አይደለም የሚል አስተሳሰብ እንደሆነ ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡
ስለሆነም ስለአህጉሪቱ ሰላምና ብልጽግና መሪዎቿ እና ህብረቱ በአህጉሪቱ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ማተኮር ፤ በተለይም ወጣቶች ላይ ያዝ ለቀቅ እንዳይሆን መትጋት ፤ የአፍሪካ ህብረት ተቋማትም ቅድሚያ ለተሰጣቸው ጉዳዮች ቅድሚያ በመስጠት መስራት፤የአፍሪካ ህብረትን በፖለቲካዉ ዘርፍም ሆነ ተልዕኮን ለማስፈጸም በሚያስፈልጉ ደረጃዎች ሁሉ በብቃት ማስተዳዳርና አፍሪካዊያን በራሳቸዉ  የውስጥ አቅም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽንን ፋይናንስ ማድረግ ግድ የሚላቸው ሰአት ላይ ስለመሆናቸው አምነው በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ቀደም የህብረቱ 60 እና 70 በመቶ በላይ የሚሆነው ወጪ በውጭ ሃገር ለጋሾች ይሸፈን በነበረው አግባብ መቀጠል  ህብረቱን ለተለያዩ ጣልቃ ገብነቶች በተመሳሳይ ማጋለጡ ስለማይቀር ውሳኔው የጉባኤ ማድመቂያ ሆኖ ይቀራልና ነው።
ይህንን ከግምት ያስገባው የህብረቱ አዲስ የማሻሻያ ሰነድ ሁሉም አባል ሃገራት ከገቢ ንግድ ከሚያገኙት ዜሮ ነጥብ ሁለት በመቶውን ለህብረቱ እንዲያስገቡ የሚል ሃሳብ በማቅረብ ህብረቱ ላለበት የፋይናንስ ችግር መላን ዘይዷል። ይህም ለህብረቱ በአመት 1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እንዲያገኝ በማስቻል ራሱን ከውጭ ጥገኝነት ነፃ እንዲሆን ያደርገዋልና ሃገራት ማሻሻያ ውሳኔውን ባጸደቁት ልክ ለውሳኔው ተገዢ በመሆን ስለወጣቶች የገቡትን ቃል ሊያረጋግጡ ይገባል።
በእርግጥ የቀረበውን የማሻሻያ ሃሳብ ገለፃን ተከትሎ አፍሪካዊያን መሪዎች የቀረበውን የለውጥ ሀሳብ  ህብረቱን  ወደ አዲስና ትክከለኛ ጎዳና የሚወስደው፤ለህብረቱ ሀይል የሚያጎናፅፍና የተቋሙን አጀንዳ ከህዝቡ ጋር በማስተሳሰር አፈጻጻሙን የሚያሻሽል በመሆኑ በደስታ ተቀብለዉታል፡፡ያም ሆኖ ግን የእናቴ መቀነት ጠለፈኝ እንዳይመጣ መስራት ያስፈልጋል።
በዘንድሮውና 28 ጊዜ በአዲስ አበባ ላይ በተደረገው  ጉባኤ ላይ መራሄ መንግስታቱ በቀረበው የማሻሻያ ሰነድ ላይ ስምምነት ላይ ከመድረሳቸው በተጨማሪ የህብረቱን ኮሚሽን ሊቀመንበር በመምረጥ እንዲሁም ሞሮኮን 33 አመታት በኋላ ያቀረበችውን የህብረቱ አባልነት ጥያቄን የመቀበል ውሳኔን በማሳለፍ ቆይታቸውን በስኬት በማጠናቀቅ ወደ ሃገራቸው ተመልሰዋል።   

No comments:

Post a Comment