Monday, 6 February 2017

የሁለት ጫፍ ጦርነት!!




                                             ይነበብ ይግለጡበአገሪቷ ቆላማ አካባቢዎች የደን ቃጠሎ እንዳይከሰት ጥብቅ ክትትል ሊደረግ ይገባል

በተፈጥሮ አየር መዛባት በሀገራችን የተከሰተውን ድርቅ ለመከላከል መንግስት ሰፊ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡አምና በተከሰተው ድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች አንዳንዶቹ መልሰው በማገገም ራሳቸውን የሚያግዙበት ሁኔታ የተፈጠረ ቢሆንም የዛኑም ያህል በያዝነው አመት የተከሰተው የድርቅ ችግር በተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶአል፡፡ ይህንን የድርቅ ችግር ለመከላከል የፌደራሉና የክልል መንግስታት ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡የሁለት ጫፍ ጦርነትም ውስጥም ነን፡፡በአንድ በኩል ድርቁን የመከላከል በሌላም በኩል የማልማት ስራውን የማስቀጠል፡፡
በረሀማ በሆኑ አካባቢዎች የውሀ ጉድጓድ ቁፋሮዎች በስፋት ተካሂደው ስኬታማ የሆኑባቸው አካባቢዎች የመኖራቸውን ያህል ፍንጭ ቢያሳዩም ፈጥኖ ውሀ ለማግኘት ባልቻሉ አካባቢዎች ድርቁ በተለይ በእንሰሳት ላይ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል፡፡በበረሀማ ቦታዎች ድርቅና ውሀ ጥምን ለመከላከል የሚችሉ ግመልን የመሳሰሉ እንሰሳት ካለውሀ ከ10 ቀን በላይ ለመቆየት ሲችሉ ሌሎች  ፍየል በግ ፈረስና አህያን ለመሳሰሉት ተፈጥሮ ይህን ስጦታ አልሰጠቻቸውም፡፡ለዚህ ነው ውሀ ካላገኙ የሚሞቱት፡፡ሰውም ውሀ ካላገኘ በሕይወት የመቆየት እድሉ የጠበበ  ነው፡፡
የፌደራሉና የየክልሎቹ መንግስታት በተለይ ውሀ በሌለባቸው አካባቢዎች ከሩቅ አካባቢዎች ውሀ በቦቴ በመውሰድ ለሕዝቡ በማዳረስ እለታዊ የምግብና የሕክምና ሌሎችንም እርዳታዎች በማድረስ ችግሩን ለመቅረፍ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡የቤት እንሰሳቶቹ በውሀ ጥም ተጎድተው ከማለቃቸው በፊት ወደሌሎች አካባቢዎች ተወስደው እንዲሸጡ በመደረግ ላይ ነው፡፡ ውሀ ባለበት አካባቢዎች ከገቡ ያለስጋት ለመኖር ያስችላቸዋል፡፡
የድርቁን ሁኔታ ለመከላከል ለእርዳታ ፈላጊዎችም በፍጥነት በመድረስ ረገድ መንግስት የራሱን ሰፊ ስራ እየሰራ ቢሆንም ድርቁን ለመከላከል ከ984 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ እንደሚያስፈልግ ገልጾአል፡፡ድርቁ በኢትዮጵያ ሶማሌ በኦሮሚያ በደቡብ ክልል የተከሰተ ሲሆን በድርቁ ተጎጂ የሆነው ሕዝብ ቁጥር 5.6 ሚሊዮን ነው፡፡
የፌደራል አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ መንግስት ድርቁን ለመከላከል ማድረግ ያለበትን ሁሉ እያደረገ ነው ሲሉ ለመገናኛ ብዙሀን ገልጸዋል፡፡ድርቁን ለመመከት ከሚያስፈልገው አጠቃላይ 948 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ክልሎችና ፌደራል መንግስቱ 75 ሚሊዮን ዶላር መመደባቸውን ይህም ለተጎጂዎቹ በሚደርስበት መልኩ እየተሰራበት መሆኑን ኮምሽነሩ ገልጸዋል፡፡
በግለሰብ ደረጃ ለእያንዳንዱ ሰው 15 ኪሎ ግራም ስንዴ፤ለነፍሰጡር ሴቶችና ሕጻናት 1.5 ኪሎግራም አልሚ ምግብ በነፍስ ወከፍ በመሰራጨት ላይ እንደሚገኝ ኮምሽነሩ ተናግረዋል፡፡በሀገሪቱ ደጋና ወይና አደጋ የአየር ንብረት አካባቢዎች ከፍተኛ የበልግ የመኽር ወቅት ምርት እንደሚገኝ የሚጠበቅ በመሆኑ ለተጎጂዎቹ የእርዳታ እህል በማቅረብ ረገድ አብዛኛው ግዢ ከሀገር ውስጥ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
ድርቁ ወቅትና ግዜን እየለዋወጠ የሚከሰት በመሆኑ ለዛሬውም ሆነ ለወደፊቱ በአስተማማኝ ሁኔታ መከላከል የሚቻልባቸው ስራዎች በሁሉም ክልሎች በስፋት በመሰራት ላይ ይገኛሉ፡፡የጥልቅ ውሀ ጉድጓድ ቁፋሮ፤ወንዞችን ጠልፎ ለመስኖ ልማት እንዲውሉ የማድረግ፤በዝናብ ወቅት ዝናብ የማቆርና የማስቀረት ወደመሬት ሰርጎ እንዲገባና ለአካባቢው እርጥበት እንዲፈጥር የማድረግ ስራ፤ደኖችን የማልማት በረሀማነትን የሚከላከሉ የእጸዋት ዝርያዎችን የማስፋፋት፤ በተቆፈሩ ጥልቅ ጉድጓዶች ውሀዎችን በዝናብ ወቅት የማከማቸት ወዘተ እጅግ ብዙ ብዙ ስራዎች በሁሉም ክልሎች በመንግስት በኩል እየተሰሩ ሲሆን ከፍተኛ ውጤቶችም አስገኝተዋል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር ባለሙያዎች አርሶ አደሩን ስለዘመናዊ ግብርና የመሬትና የአፈር አጠቃቀም የውሀ ማቆር ውሀን በአግባቡ መጠቀምን አስመልከቶ በየወቅቱ የሰጡት ትምህርትና ስልጠና ድርቁ ቢከሰትም ከፍተኛና መሰረታዊ ለውጦችን በቆላማው በደጋውና በወይናደጋው የሀገራችን አካባቢዎች ለማስመዝገብ ችሎአል፡፡የሚጠበቀው ይህንኑ ጥረት አጠናክሮና አጎልብቶ መቀጠል ብቻ ነው፡፡
የተፈጥሮ የአየር ንብረት ለውጥና መዛባት በአለም ዙሪያ አይነቱ የተለያየ አደጋ ያስከትላል፡፡ለሰውና ለከብቶች የሚሆነውን ውሀ ማድረቅ የመሬት መሰነጣጠቅ፤በሌላው አካባቢ ደግሞ ከፍተኛ ጎርፍና የውሀ ማጥለቅለቅ፤የመሬት መደርመስና ናዳ፤,የአየሩ የሙቀት መጠን ሲጨምር በደኖች ላይ የሚከሰተው የእሳት ቃጠሎና ሌሎችም በአየር መዛባት የሚከሰቱ ሕዝብን ለጉዳቱ ተጋላጭ የሚያደርጉ ችግሮች ናቸው፡፡
ከሰሞኑ በሀገራችን ቆላማ ስፍራዎች የደን ቃጠሎ ሊከሰት ስለሚችል ጥብቅ ክትትል ማድረግ የሚገባ መሆኑን የአካባቢ ደን ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር በመግለጫው ማስጠንቀቂያ በመስጠት  ሳስቦአል፡፡ በአንዳንድ ቆላማ አካባቢዎች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የደን ቃጠሎ ተከስቶ በሕብረተሰቡና በጸጥታ ኃይሎች ጥረት እንዲጠፋ መደረጉን አስታውቆአል፡፡
የደን ቃጠሎው ከወቅቱ ደረቅ የአየር ሁኔታ ጋር ተያይዞ በቀጣይም ሊከሰት የሚችል መሆኑን በመግለጽ አስፈላጊው ክትትል እንዲደረግ አሳስቧል፡፡ባለድርሻ አካላት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት የደን ቃጠሎ እንዳይነሳ የቅደመ መከላከል ስራ መስራት እንዳለባቸውበደኖች አካባቢ ለሚኖሩ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተያያዥነት ላላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ግንዛቤ ማስጨበጥ እንደሚገባ፤የደን ቃጠሎ መከላከያና መቆጣጣሪያ ግብረኃይል,በየደረጃው ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን፤ሕብረተሰቡ የደን ቃጠሎ ሲነሳ ለሚመለከተው አካል በፍጥነት ማሳወቅ እንዲሁም ቃጠሎውን በማጥፋት ተሳታፊ መሆን እንዳለበትም ሚኒስቴሩ በሰጠው መግለጫ አስታውቆአል፡፡
ለደን ቃጠሎ ተጋላጭ የሆኑ ስፍራዎችን መለየትና ተቀጣጣይ እፅዋቶችን ማጽዳት፤  ቃጠሎውን ለመከላከል አስፈላጊ የሆኑውሀ መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች ዝግጁ ማድረግ እንደሚገባ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገልጾአል፡፡አንዱ ድርቁን ከሚያባብሱት ሁኔታዎች ውሰጥ ይሄን መሰሉ ተፈጥሮአዊ ክስተት መሆኑ ይታወቃል፡፡ለመከላከል እንዲቻል ተገቢ የቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡
ድርቁን በመከላከል ረገድ ከሚሰራው ስራ አንዱ  የአፈርና ውሀ  እቀባ ሲሆን በዚህም በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶአደሮች ተጠቃሚ ሁነዋል፡፡የሰሜን ወሎ አርሶ አደሮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በወልዲያ አካባቢ ከዚህ ቀደም በተሰሩ የአፈርና ውሀ እቀባ ስራዎች ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያገኙበት በመሆኑ ልማቱን አጠናክረው መቀጠላቸውን በሰሜን ወሎ ዞን የሚገኙ አርሶ አደሮች ለመገናኛ ብዙህን ገልጸዋል፡፡በአካባቢው የአፈርና ውሀ እቀባ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡ዋድላ ወረዳ የጋሸና ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ባለፉት ዓመታት በተሰራው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ የተራቆቱ ተራሮች በደን ተሸፍነዋል ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል በተሰራው የአፈርና ውሀ እቀባ ስራ ጠፍተው የነበሩ የእፅዋትና የሳር ዝርያዎች ተመልሰው በቅለዋል፡፡ደርቀው የነበሩ ምንጮች መፍለቅ ጀምረዋል፡፡በጉባላፍቶ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ካሳ ከተማ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በተካሄደ የተፋሰስ ልማት የተሰራ እርከን የክረምት ዝናብን በመያዝ በአካባቢው ይደርስ የነበረውን የጎርፍ መጥለቅለቅና የአፈር መከላት እንዲቀር አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡
በዞኑ ግብርና መምሪያ የደንና አግሮፎሬስትሪ ባለሙያ አቶ መሀመድ አብደላ በዞኑ የአፈርና ውሀ እቀባ ስራ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው በዚሁ ስራ በልማት ቡድን የተደራጁ 411ሺህ 778 አርሶ አደሮች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን ልማቱ 525 ተፋሰሶችን መሰረት በማድረግ 12ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለማከናውን ታቅዶ እስካሁን 10 ሄክታር መሬት ላይ ስራው መከናወኑን ገልጸዋል፡፡
የማሳና የተራራ ላይ እርክን፤ ክትር፤ የመስኖ ውሀ ጠለፋ፤ የውሀ ማሰባሰቢያ ኩሬዎችና የአርሶ አደሩን ዘላቂ ጥቅም የሚያረጋግጡ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎች በሰፈው እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡በሰሜን ወሎ ዞን ካሉ1766 ተፋሰሶች ውስጥ እስከሁን 50 በመቶ በላይ ለተፋሰስ ልማት ስራ ላይ መዋላቸው ታውቆአል፡፡በተከታታይ ዓመታት በተሰራው የተቀናጀ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ የዞኑ የደን ሽፋን ከነበረበት ከአንድ በመቶ ወደ 11 ነጥብ 3 በመቶ ማደጉን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በሌላም በኩል በተያዘው የበጋ ወቅት ከአንድ ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በተፋሰስ ለማልማት ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታውቆአል፡፡
የቢሮው ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ ባለፉት ስድስት ዓመታት በተከናወነ የተፋሰስ ልማት በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት ደርሶበት የነበረ 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት መልሶ ማገገሙንጉዳት የደረሰበትን መሬት በተፋሰስ አልምቶ ከሰውና እንስሳት ንክኪ ከልሎ የተለያዩ ሀገር በቀል የዛፍ ዝርያዎችን በመትከል የክልሉ የደን ሽፋን ከነበረበት 11 በመቶ ወደ 19 በመቶ ማደጉን አስታውቀዋል፡፡
በተያዘው ዓመት 3ሺህ760 በላይ ተፋሰሶችን በመለየት 1 ሚሊዮን 128 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችና የሰው ኃይል የመለየት  ስራ መከናወኑን ሀላፊው አስታውቀዋል፡፡የሚከናወነው የተፋሰስ ልማት በዋናነት በአየር ንብረት ለውጡ ሳቢያ የጎርፍ አደጋ ተጠቂ በሆኑ አካባቢዎች ትኩረት እንደሚያደርግ ታውቆአል፡፡
ማጠቃለያ
በአንድ በኩል በሀገራችን ላይ ድርቁን የመመከትና የመቋቋም ስራ መንግስት በስፋት እየሰራ ይገኛል፡፡,ለተጎጂዎች የምግብ የውሀ የህክምና እርዳታና የመሳሰሉትን በፍጥነት በማድረስ ስራ ተጠምዶአል፡፡በሌላም በኩል ወደፊት ሊከሰቱ የሚችሉ የተለያዩ የድርቅ አይነቶችን ቀድሞ ለመመከት የሚያስችል ሰፊ መሰረት ያለው የግብርና ስራ በሁሉም ክልሎች በመስራት ላይ ይገኛል፡፡የልማት ስራዎቹ በተለያዩ አካባቢዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡የሁለት ጫፍ በመካሄድ ላይ ነው፡፡,ድርቁን መመከት ልማቱን በስፋት ማካሄድ፡፡ › 

No comments:

Post a Comment