Monday, 6 February 2017

ህገ መንግሥቱና የኃይማኖት እኩልነት




አባ መላኩ

ኢትዮጵያውያን ያለፈውን አስከፊ ድህነትና ኋላ ቀርነት ጠንቅቀው ያውቁታል። እናም ያ ታሪክ ተመልሶ እንዲመጣ አይፈቅዱም። የአገራችንን የህዳሴ ጉዞ በማሰናከል ዜጎቿ በድህነትና በኋላ ቀርነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀው ትናንት ወዳለፉት ድቅድቅ ጨለማ የመመለስ ተግባር በማንኛውም ዘንድ ተቀባይነት የለውም።

ዛሬ ላይ በአክራሪነትና ፅንፈኝነት ላይ የሚኖረን ትግል ለአፍታም ቢሆን አይቀዛቀዝም። ኢትዮጵያውያን በአክራሪዎችና ፅንፈኞች ላይ የሚወስዱት ሕጋዊ እርምጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ ሄዷል።  

ዕንፈኞች በአገር ውስጥም ሆነ  በውጭ የሚገኙ ፀረ ሠላም ኃይሎችን በማስተባበር የሞት የሽረት ትግል ሲያደርጉ ይስተዋላል። በአገር ውስጥ አንዳንድ ፅንፈኛ ተቃዋሚዎች አፍራሽ ሚዲያዎችን በመጠቀም ጭምር በቅብብሎሽና በቅንጅት ፀረ ሠላም ተግባራትን ሲፈፅሙ ይታያል።  

በአገሪቱ ለረዥም ጊዜ የቆየው የመቻቻል እና አብሮ የመኖር እሴት እንዲቀጥል የኃይማኖት ተቋማቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በስፋት ሊሰጡ ይገባል።   ከጥንት ጀምሮ በኃይማኖቶች መካከል ያለውን የመቻቻልና አብሮ የመኖር እሴት ለማስቀጠል እያንዳንዱ የኃይማኖት ተቋማትና የእምነቱ ተከታዮች አገራዊ ኃላፊነት አለባቸው። በተለይ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በሠላም እምነቱን እንዲያራምድና ለፀጥታ መሰናክል የሆኑ አካላትን ቀድሞ እንዲከላከል ለማድረግ  ለእምነቱ ተከታዮች በሠላም ዙሪያ የሚሰጠው ትምህርት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

ሙስሊሙ ኅብረተሰብ አክራሪነትን ለመከላከልና የአገሪቱን ሠላም ለማስጠበቅ ከመንግሥት ጎን በመሰለፍ  የፀረ ሽብር ዘመቻን እየደገፈ ይገኛል። በመሆኑም በርካታ የሽብር ተግባራትን ማክሸፍ ተችሏል። በኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ የተገነባው ተቻችሎና ተከባብሮ በሠላም የመኖር እሴት ለማስቀጠል በአሁኑ ወቅት የሚታዩ ኃይማኖትን ሽፋን ያደረጉ ተግባራትን ለመዋጋት የኃይማኖት ተቋማት በሥነ ምግባር የታነፀ ዜጋ ከመፍጠር አንፃር ትልቁን ድርሻ ወስደው ሊሰሩ ይገባል።

መንግሥት ኃይማኖትን ሽፋን በማድረግ ህገ መንግሥታዊ  መብቶችን የሚጥሱና የህዝብን ሠላም የሚነሱ አካላት ላይ በተለያየ ጊዜ ሕጋዊ እርምጃ ቢወስድም በህገ መንግሥቱ  የተመለሱ ጥያቄዎችን እንዳልተመለሱ በማንሳት ሽብርን ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ አካላት መከሰታቸው አልቀረም።
በኃይማኖት ስም አልፎ…አልፎ በአገራችንም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ አገራት እየተፈፀመ ያለው የአሸባሪነት ተግባር   እየተስፋፋ መጥቷል  ለማለት ባያስደርፍር ብቅጥልም እያለ በማድረስ ላይ ያለው ጉዳት ሙሉ በሙሉ መግታት እንዳልተቻለ  እሙን ነው። በአንዳንድ የአፍሪካም ሆነ የአውሮፓ አገራት የኃይማኖት አክራሪነት እንቅስቃሴ ከተጀመረ  ዓመታት ተቆጥረዋል።

ቀደም ሲል በሶማሊያ ጠንካራ ይዞታ መስርቶ የነበረው አልሸባብም በኢትዮጵያ የሽብር ተግባራትን በተለያየ ጊዜ ለመፈፀም ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል።  ግንቦት ሰባት፣ ኦብነግና ኦነግ  የሚባሉ ቡድኖችም አልሸባብና የኤርትራ መንግሥት በሚሰጧቸው መመሪያ መሠረት የኢትዮጵያን ሠላም ለማደፍረስ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ።

እነዚህ የሽብር ቡድኖች በዋናነት ኢትዮጵያ ላይ አነጣጥረው እየሰሩ እንደሆነ እሙን ነው። የእነዚህ ቡድኖች ዋና ዓላማም የአገሪቱን የልማት፣ የሠላምና የዴሞክራሲ እንቅስቃሴን ማኮላሸት እንደሆነ ካለፉት 25 ዓመታት እንቅስቃሴያቸው ለመረዳት ይቻላል። በአገሪቱ እየተካሄዱ ባሉ ትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ ያነጣጠሩ ጥረቶች ቢያደርጉም በኅብረተሰቡ ጥረት መክሸፍ ችለዋል። ከዚህም አልፈው በንጹሃን የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ቀላል የማይባል የሽብር ተግባር ፈጽመዋል።  

ይሁንና የኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ እያካሄደ ያለውን ዘላቂ ልማት የማረጋገጥና ድህነትን የመዋጋት ተግባር በጠላቶቿ እንዳይጓተትና እንዳይደናቀፍ አስፈላጊ መሠረታዊ ጥንቃቄና ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
የኢትዮጵያ መንግሥትና ህዝብ የሁሉም ዓይነት ችግሮች መንስዔ የሆነውን  ድህነትን ለማጥፋትና በአገሪቱ ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ብሎም  ዘላቂ ልማትን ለማምጣት የሚያስችል ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ይሁን እንጂ አሸባሪዎች በተለያየ መልክ የአገሪቱን ሠላም ለማደፍረስ ከመንቀሳቀስ አልተቆጠቡም።  ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተስፋፋ የመጣው የኃይማኖት ለምድ የለበሰ የጥፋት አጀንዳን የማሳካት አባዜ በሰፊው እየተስተዋለ መጥቷል። 
ይህ በኃይማኖት ስም እየተፈፀመ ያለው ሥውር የሽብር ተግባር የአገሪቱን ሠላም ለማደፍረስ በውጭና በአገር ውስጥ ኃይሎች ድጋፍ የተቀነባበረ እንደሆነ ይታመናል።  የኢትዮጵያ ልማት፣ ሰሠላምና ዴሞክራሲ የእግር እሣት የሆነባቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶች አገሪቱን ወደ ብጥብጥ ለማስገባት የሚያስችል ማንኛውንም መንገድ ከመጠቀም አይቆጠቡም። በአገሪቱ በኃይማኖት ስም የሚንቀሳቀሱ አፍራሽ ኃይሎችን በመመልመልና የገንዘብና የቁሳቁስ አቅርቦትን በማሟላት ብጥብጥን ለማንገስ ደፋ ቀና ካሉ ዓመታት ተቆጥረዋል።
በአገሪቱ በተለያየ ወቅት የተለያዩ የሽብር ተግባራትን እየፈፀሙ ያሉ ጽንፈኞች በዓለም ዙሪያ ከሚንቀሳቀሱ አሸባሪዎች ጋር የጠበቀ ቁርኝት በመፍጠር በሌሎች አገራት የተሰራባቸው ሠላም የማደፍረስ ዘዴዎችን በመጠቀም በአገራችን ተመሳሳይ ሁኔታ ለመፍጠር ያልተቆጠበ እንቅስቃሴ ለማድረግ ይጥራሉ።
በኢትዮጵያ የሃኃይማኖት እኩልነትና ነጻነት ከተረጋገጠ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል።  ቀደም ባሉት ሥርዓታት የነበረው ‘አንድ አገር አንድ ኃይማኖት’ የሚል አሠራር ከሥር መሠረቱ ተንዶ በአገሪቱ ማንኛውም ዜጋ በነጻነት የፈለገውን ኃይማኖት የሚያመልክበት ሥርዓት ተገንብቷል።
ከዚህ አንጻር በቀደሙት ሥርዓታት የተለየ ጭቆናና በደል ይደርስበት የነበረው የእስልምና እምነትም የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ባረጋገጠለት መብት መሠረት መስፋፋት ችሏል። ህዝበ ሙስሊሙም ያለምንም ተጽዕኖ ኃይማኖታዊ ተልዕኮውን በመፈፀም ላይ ይገኛል። 
በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ የኃይማኖት ነጻነት ተረጋግጧል። ከኃይማኖት ጋር በተያያዘ ሊነሳ የሚችል የእኩልነትና የነጻነት ጥያቄ እንደሌለ እሙን ነው።  ጉዳዩ ከሁለት አሥርተ ዓመታት በፊት መቋጫ አግኝቷልና። የኃይማኖት እኩልነትና ነጻነት በሕገ መንግሥቱ ተረጋግጦ ተፈጻሚ ሆኗል። በሕገ መንግሥቱ መሠረት ‘መንግሥት በኃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤ ኃይማኖትም በመንግሥት ተግባራት ውስጥ እጁን አያስገባም’።
የኃይማኖት ነጻነት በተገቢው መልክ በተረጋገጠባት ኢትዮጵያ የአንድ ኃይማኖት የበላይነት እናነግሳለን፣ የእኛን እምነት በሌላው ላይ በአስገዳጅ እንጭናለን የሚል ቡድን ቦታ አይኖረውም።
ሕገ መንግሥቱ ለዜጎች የሰጠውን የኃይማኖት ነጻነት መተላለፍ ከቶ አይቻልም። ኢትዮጵያውያን በኃይማኖት መቻቻል ለዓለም ህዝቦች አብነት ናቸው። ህዝበ ሙስሊሙ ከህዝበ ክርስቲያኑ ጋር ተደጋግፎና ተቻችሎ ለዘመናት ዘልቋል። በደስታም ሆነ በሃዘን ሳይለያይ የዘለቀው ይህ ህዝብ አሁንም አንድነቱና መቻቻሉ እንደተጠበቀ ይሁን እንጂ ይህንን ጠንካራ ሰንሰለት ለመበጠስ ያልተቆጠበ ጥረት እያደረጉ የሚገኙ ጥቂት ጽንፈኞች ሰርገው እየገቡ ኅብረተሰቡን ለመበጥበጥና ሠላሙን ለማናጋት ጥረት ከማድረግ አልተቆጠቡም።
ጽንፈኞች ይህንን ጠንካራ ሰንሰለት በመበጠስም በእስልምናና በክርስትና ኃይማኖት ተከታዮች መካከል መቋጫ የሌለው ግጭት ለማቀጣጠል ቀላል የማይባል ጥረት ያደረጉ ቢሆንም በሕዝቡ ጠንካራ ቁርኝት፣ በኃይማኖት አባቶች አስተምህሮና መንግሥት  በወሰዳቸው በሳል እርምጃዎች ምክንያት ሳይሳካላቸው  ቀርቷል።
ይህ ሙከራ መኮላሸቱን ሲያውቁ እስልምና አማኞችን ወደ አንድ እምነት ማምጣት አንድ የእስልምና እምነት ብቻ እንዲኖር ማድረግ የሚል እንቅስቃሴ መጀመር አማራጭ አድርገው ነበር መንቀሳቀስ የጀመሩት።
ሁሉም ኃይማኖቶችና እምነቶች በራሳቸው ቆመው በነጻነት መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ሕገ መንግሥቱ ይደነግጋል። ዜጎች የመረጡትንና የፈለጉትን ኃይማኖት ያለምንም ተጽዕኖ ማምለክ ችለዋል።  ይህንን ሕገ መንግሥታዊ መብት ለመናድ ነው ወሃቢያ በተባለው የእስልምና እምነት ስም እየተንቀሳቀሱ ያሉ ጥቂት ሽብርተኞች የእስልምና ኃይማኖት አማኞች ውስጥ መከፋፈልን ለመፍጠር የሚጥሩት። የኛን እምነት ብቻ ተከተሉ። እኛ ከያዝነውና ከምናምንበት እምነት ውጭ ሌላ ኃይማኖትና እምነት አይኖርም በሚል ጽንፈኛ ሃሳብ ታውረው ፍጹም ፀረ ዴሞክራሲ በሆነ መንገድ የኅብረተሰቡን ሠላም ማደፍረስን የመረጡት። ሆኖም ቀደም ሲል በነበረው እንቅስቃሴ ህዝበ ሙስሊሙ የአክራሪዎቹ እንቅስቃሴ ከእምነቱና ከኃይማኖቱ ተልዕኮ የራቀ በመሆኑ ሊቀበለው አልቻለም።

በኃይማኖት ስም በአማኞች መካከል ተሰግስገው የእስልምና ኃይማኖትን የሚሰብኩ ለሕዝበ ሙስሊሙ የሚያስቡና ለኃይማኖታዊ ተልዕኮ የቆሙ በመምሰል ድብቅ አጀንዳቸውን የሚያራምዱ ጽንፈኞችን ኅብረተሰቡ ቆርጦ ተነስቷል። እነዚህ ቡድኖች ሕዝበ ሙስሊሙን መቋጫ ወደሌለው ግጭት ማስገባትና በሂደትም የእስልምና ኃይማኖትን ለማጥፋት የተነሱ መሆናቸው ድርጊታቸው መስክሯል።

እስላም ሠላም፣ ፍቅርና መቻቻል ነው የሚል ኃይማኖታዊ ተልዕኮ አንግበው ለሚንቀሳቀሱ የእስልምና አባቶች አክራሪው ኃይል በማንኛውም ወቅት የሽብር ሰለባ ሊያደርጋቸው እንደሚችል በማስፈራራት ፀጥ ረጭ ብሎ የአሸባሪዎቹን እምነት እንዲቀበል ተጽዕኖ ለማሳደር እንደሆነ ታውቋል።
አክራሪዎች ቀደም ሲል በተለያየ ጊዜና ቦታ ሲፈጽሟቸው የነበሩ የሽብር ተግባራትና ለመፈፀም አቅደው የከሸፉባቸውን የሽብር ሙከራዎችን በምናይበት ጊዜ በአገራችን ያለውን ሠላም፣ ዴሞክራሲና ልማት በማወክና በግርግር ለመጠቀም በማቀድ ነበር።
በመላ አገሪቱ የሚገኝ ማንኛውም ሠላም ወዳድ ዜጋ በኃይማኖት ስም ሥውር የፖለቲካ አጀንዳ የሚያራምዱና በኃይማኖት አባቶች እንዲሁም በሌሎች ንጹኃን ዜጎች ላይ የሽብር ጥቃት የሚፈጽሙ አካላትንጥብቆ ይቃወማል። ኢትዮጵያ ለብዙ ዘመናት የተለያዩ ኃይማኖቶች በጋራ ተከባብረውና ተቻችለው የሚኖሩባት፣ የኃይማኖት አባቶች የሚከበሩባት እንዲሁም ለሌላው ዓለም የሠላምና የመቻቻል ተምሣሌት መሆኗ  ይታወቃል የህዝቦች የእምነት ነጻነትና እኩልነት ተከብሮ፣  መንግሥት በኃይማኖት፣ ኃይማኖትም በመንግሥት ጣልቃ የማይገቡበትና መንግሥታዊ ኃይማኖት የማይፈቀድበት ህገ መንግሥት ያላት አገር ሆናለች።
ይሁንና ሕገ መንግሥቱን በሚጻረር መልኩ  እየተስተዋለ ያለው የኃይማኖት አክራሪነት እንቅስቃሴ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ መንግሥት እየወሰደ ያለውን እርምጃ ማጠናከር እንዳለበት ኅብረተሰቡ እየገለፀ ይገኛል።
አገሪቱ የጀመረችው የእድገት ግስጋሴን ለማደናቀፍና የህዝቦቿን ሠላም ለማደፍረስ በኃይማኖት ስም ሥውር የፖለቲካ አጀንዳ የሚያራምዱ አካላትን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ አጥብቆ ይቃወማል። ለሠላም ለመቻቻልና ለእድገት ከመሥራት ይልቅ ልዩነትንና የኃይማኖት አክራሪነትን የሚሰብኩ፤  በኃይማኖት ስም ኃይማኖትን ለማጥፋት የተነሱ ሽብርተኞች በኢትዮጵያ ቦታ ሊኖራቸው አይገባም።

No comments:

Post a Comment