ይነበብ ይግለጡ
ዋናው ኦዲተር በዘንድሮው አመት ለፓርላማው ባቀርበው
አጠቃላይ የመንግስት ተቋማትን የፋይናንስ አሰራር ጉድለቶችን የተመለከተው ሪፖርት እንደ ሀገርና
እንደ ሕዝብ ሲታይ አስደንጋጭ ነው፡፡ እጅግ ከፍተኛ የሆኑ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የመንግስትና የሕዝብ ኃብት ብክነትና የገባበት
አለመታወቅ፤ በአሰራር ዝርክርክነት፤ ከደምብና መመሪያ ውጭ በመስራት፤ በስራ ላይ ለሌሉ ሰራተኞች በስራ ላይ እንዳሉ ተቆጥሮ
ለበርካታ ግዜያት ደመወዝ መክፈል፤ መንግስታዊ ፕሮጀክቶች ውል በተገባበት ግዜ ባለመጠናቀቃቸው ያለምንም ስራ ለባንክ የሚከፈለው
የቢሊዮን ብር ወለድ ሌላም ብዙ ጉዳዮችን ማንሳት ይቻላል፡፡
መንግስት እንደ መንግስትነቱ የሚወቀሰው ፈጥኖ እርምጃ
ባለመውሰዱና እንዲታረም ባለማድረጉ ነው፡፡ በተዋረድ መንግስት የሰጣቸውን የውክልና ስልጣን ይዘው ተቋማትን የሚመሩና
የሚያስተዳድሩ ሰዎች አይነ አውጣ በሆነ መንገድ ሀገርና ትውልድ አውዳሚ የሙሰኞችና የኪራይ ሰብሳቢዎች የጥገኞች ዘረፋ
ያለምሕረትና ያለይሉኝታ እርስ በእርስ በመመሳጠር በሀገሪቱ ሀብት ሲጫወቱበት በቀድሞውም የፓርላማ ሪፖርት ጠቅላይ ኦዲተሩ
ተመሳሳይ ሪፖርት ሲያቀርብ የተወሰደ እርምጃ አልነበረም፡፡ ለዚህም ነው ሁኔታው እየተባባሰ የመጣው፡፡
ከሰሞኑ ይህን ባደረጉ አንዳንድ ተቋማት ላይ የፌደራል
ፖሊስ ኮሚሽን ከጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጋር በመሆን የምርመራና የማጣራት ስራ መጀመሩ ይፋ ሆኖአል፡፡ በጣም የዘገየ ቢሆንም አሁንም
እርምጃ መውሰድ መጀመሩ የሚበረታታ ነው፡፡ የጠቅላይ ኦዲተሩ ሪፖርት ግልጽና የማያሻማ ነው፡፡ ለሀገርና ለሕዝብ ሀብት ያለውን
ኃላፊነትና ተቆርቋሪነት በማሳየት የድርሻውን ሀገራዊ ግዴታ ተወጥቶአል፡፡
ከቀድሞ ጀምሮ እንደነዚህ አይነት ሀገራዊ ክብደት
ያላቸው በልማቱና በእድገቱ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ የሚያደርጉ የገንዘብ ጉድለቶችና ብክነቶች በተጨባጭ መድረሳቸው ሲረጋገጥ ፈጥኖ
እርምጃ መውሰድ የነበረበት መንግሰት መሆን ነበረበት፤ የሚተች የሚወቀሰውም በዚህ ነው፡፡
መስተካከልና መታረም ላለባቸው የአሰራር ድክመቶች
የደንብና መመሪያ ጥሰት በሕግ ከተፈቀደው ውጭ በማን አለብኝት መስራትን ለመሳሰሉት ፈጻሚዎቹ በሕግ ተጠያቂ ተደርገው ቢሆን ኖሮ
እዚህ ደረጃ ላይ ባልተደረስም ነበር፡፡
አልፎ ተርፎ የሌባ አይነደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ
እንደሚባለው ከነዚሁ ተቋማት ውስጥ ገንዝብ ባክኖአል ተብሎ ስማችን ጠፍቶአል በሚል አዲስ ዘመን ጋዜጣን ፍርድ ቤት እስከ
መክሰስ የደረሱ አሉ፡፡ ዛሬም ጋዜጠኞቹ ፍርድ ቤት እየተመላለሱ ነው፡፡ አሳፋሪና ነውረኛ ድርጊት ነው፡፡ ይህ ሲባል በተቋሙ
ውስጥ የሚሰሩት ሁሉንም ማለት አይደለም፤ ከገንዘብ ኃላፊነትና ከመሳሰሉት ጋር የሚሰሩትን በተመለከተ ተቋሙ በራሱ ሰራተኞች
አቤቱታ ሲቀርብበት ኃላፊዎች ሲያስተባብሉ መኖራቸው ምን ያህል አስገራሚና አይን አውጣነት እንደነገሰ ለማሳየት ነው፡፡
ተቋሙ ለአመታት ኦዲት ተደርጎ እንደማያውቅ የተለያዩ
ሪፖርቶች ሲቀርቡ ነበር፡፡ ኃላፊ የተባሉት ሲያስተባብሉ ኖሩ፡፡ ጭርሱንም ከእነሱው ብሶ ፍርድ ቤት ክስ መሰረቱ፡፡ ከእዛው
አካባቢ ተጠያቂነትን ከማስከተሉ በፊት በሚል ከሀገር የወጡ እንዳሉም ሰራተኛው ይናገራል፡፡ ጠቅላይ ኦዲተር ያደረገው ኦዲት
ያፈጠጠውን ብክነት ይፋ አደረገው፡፡ አንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ለሀገርና ለሕዝብ እውቀትን በመስጠት ለማገልገል ተተኪውንም
ትውልድ በስነምግባር እንዲታነጽ የማድረግ ከሙስናና ከኪራይ ሰብሳቢነት የነጻ እንዲሆን ከፍተኛውን ሀገራዊ ኃላፊነት የመወጣት
ግዴታም አለበት፡፡ ግን እየሆነ ያለው ሌላ ነው።
በእርግጥ ይህ ጉዳይ የሚመለከተው ጥቂትና ነውረኛ
የሆኑ የራሳቸውን ሀገርና የመንግስትና የሕዝብን ሀብት እንደጠላት
ገንዘብ በመቁጠር አይን አውጣ በሆነ ዘረፋ ላይ የተሰማሩትን ብቻ ነው፡፡
ለሀገርና ለሕዝብ ይጠቅማሉ ተብሎ መንግስት ከውጭ
መንግስታት ጋር በመነጋገር ሀገራችን ላይ እንዲሰሩ የታቀዱና ከፍተኛ የመንግሰት በጀት የፈሰሰባቸው የተለያዩ ፕሮጀክቶች እንዴት
ተቆርጥመው እንደተበሉ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ያለው ሰራተኛ የሚያውቀው ብዙ ምስጢር አለው፡፡ ከሀገርና ከሕዝብ
ይልቅ ለዛውም መንግስት አቅም በፈቀደ ሁሉን አሟልቶ ከፍተኛ ደመወዝ፤ የውሎ አበል፤ ቤት፤ ምርጥ መኪና ሰጥቶ ለሀገራችሁና ለሕዝባችሁ
ስሩ ያላቸው ሰዎች ናቸው በእንዲህ አይነት ወራዳ ተግባር ውስጥ ተዘፍቀው የሕዝብና የመንግስትን ሀብት ግጠው ሲመዘብሩት የሚታየው፡፡
ሀገርና ሕዝብን አገልግሉ ሰርታችሁ ለውጡ የተባሉና
በመንግስት ከፍተኛ አመኔታ የተጣለባቸው ሰዎች በእንዲህ አይነት የሀገርና የሕዝብ ኃብት ዘረፋ ላይ ተሰማርተው ሲገኙ
የመንግስትንም የሕዝብንም አንገት የሚያስደፋ ነውረኛ ድርጊት ነው፡፡ ድሮ ፈሪሀ እግዚአብሄር፤ ፈሪሀ ሕዝብ፤ ፈሪሀ ሀገር
የሚባል ትልቅ የሞራል ዋጋ የነበረው ጨዋነት በሀገራችን ነበር፡፡
ዛሬ ላይ ግን በከፍተኛ ደረጃ ተሸርሽሮአል፡፡ ለሀገርና ለሕዝብ ማሰብ ሳይሆን ሩጫው ዘርፎና ነጥቆ ለመክበር ብቻ ነው፡፡ በዚህ
መልኩ እስከየት ድረስ መሄድ ይቻላል የሚለው ሲታይ ያስፈራል፡፡ ለመንግስትም ቢሆን ጉዳዩ አስቸጋሪና ውስብስብ እንደሆነ
ይታወቃል፡፡ ግን ደግሞ ሕዝብን ይዞ ማሸነፍ ይቻላል፡፡
ዋናው ኦዲተሩ በሪፖርቱ የገንዘብ ጉድለቶችንና
ብክነቶችን ያሳያል፡፡ የጠቅላይ ኦዲተር ዋና መስሪያ ቤት ያለውን
ተጨባጭ ማስረጃ በባለሙያዎች አጣርቶ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ማቅረቡ ሊመሰገንና ሊበረታታ የሚገባው ነው፡፡ በዘንድሮው ሪፖርቱ ግዙፍ
የሆነ የገንዘብ ጉድለት የፋይናንስ አሰራር ዝርክርክነት እንዳለ
በማስረጃ አሳይቶአል፡፡ በአንድ ድሀ ሀገር አቅም ይህን ያሕል ግዙፍ ገንዘብ በውል ባልታወቀ ምክንያት ከአመት አመት መሻሻል
ባላሳየበት ሁኔታ ሲባክን የት እንደገባ ሳይታወቅ ተድበስብሶ ሲቀር ገንዘቡን ለማስመለስ ወይንም ተጠያቂ የሚሆኑትም እንዲጠየቁ ማድረግ የሚገባው መንግስት ነው፡፡
ከ2003 አ/ም ጀምሮ ዩኒቨርሲቲዎች ችግር አለባቸው
እየተባለ ሪፖርት ሲቀርብ ኖሮአል፡፡ ይሁን እንጂ ይህን
በተመለከተ በፊት በነበሩት ግዜያት ፓርላማውም ከመስማት ያለፈ ያሳለፈው ውሳኔ አልነበረም፡፡ በሕዝብም ዘንድ ግርታ የፈጠረው
የሄው ነው፡፡ ዘንድሮ ግን ቁርጠኛ አቋሙን ገልጾአል፡፡
የፌደራሉ ጠቅላይ ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዲቢሶ
ባቀረቡት ሪፖርት መሰረት በፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶች በአጠቃላይ ከ763 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ጉድለት ተገኝቶአል፡፡
ከ5.2 ቢሊዮን በላይ ገንዘብ አልተወራረደም፡፡ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አልተሰባሰበም፡፡ ግንባታው ላልተጠናቀቀው
የማዳበሪያ ፋብሪካ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የባንክ ወለድ
ተከፍሎአል፡፡
የፌደራል ዋና ኦዲተር የፌደራል የመንግስት መስሪያ
ቤቶችን የ2008 በጀት አመት ሂሳብና ክዋኔ ኦዲት ለሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ባቀረበበት ወቅት ነው ይህ ከላይ የጠቀስነው
የተገለጸው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ ሪፖርቱ በርካታ የሂሳብ አያያዝ ጉድለቶች፤ የውስጥ ቁጥጥር ድክመቶች፤ አፈጻጸማቸው ከደንብና
መመሪያ ውጭ የሆኑ ሁኔታዎች መገኘታቸውንም በስፋት ይገልፃል፡፡
ዋና ኦዲተሩ በሪፖርታቸው የጥሬ ገንዘብ አያያዝና
አጠባበቅ ትክክለኛነትን ለማረጋገጥ ኦዲት ከተደረገባቸው ተቋማት መካከል
የአዳማ ሳይንስና ቴክኒዮሎጂ ፋካሊቲ የ144ሺህ 716
ብር የጥሬ ገንዘብ ጉድለት ተገኝቶበታል፡፡ በአዲስአበባ ኤርፖርት
ገቢዎችና ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት፤ በጅጅጋ ዩኒቨርሲቲ፤ በጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ፤ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፤ በአዲስ አበባ
ዩኒቨርሲቲ የገንዘብ ቆጠራው ከመዝገብ ጋር ሲነጻጸር የ379 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ጉድለት ተገኝቶበታል፡፡ በሀዋሳ
ዩኒቨርሲቲና በዲላ ዩኒቨርሲቲዎችም የ2.4
ሚሊዮን ብር ልዩነት እንዳለ ተረጋግጦአል፡፡
የሰነድ ሂሳብ በወቅቱ መወራረዱን ለማጣራት በተደረገ ኦዲት በ113 መስሪያ ቤቶች በ28 ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ውስጥ ብቻ ከ5 ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ በደንቡ መሰረት ሳይወራረድ ተገኝቶአል፡፡ ከዚህ
ተሰብሳቢ ውዝፍ ሂሳብ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት የብሔራዊ አደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ የአዲስ
አበባ ሳይንስና ቴክኒዮሎጂ ዩኒቨርሲቲ፤ የመንግስት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት፤ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር፤ የኢትዮጵያ
ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፤ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴርና በስሩ ያሉ ሰባት ተጠሪ ተቋማት፤ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን፤
ትምህርት ሚኒስቴር፤ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር እና ሶስት ተጠሪ ተቋማቱ፤ ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች
ኤጀንሲ ይገኙበታል፡፡
ጅማ፣ ደብረታቦር፣ ድሬደዋ፤ አዲስ አበባ፤ ወላይታ፤ ዲላ
እና ደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ በበአጠቃላይ 91 መስሪያ ቤቶች ለሰራተኞች አበልና ደመወዝ ደንብና መመሪያ ሳይከተሉ
በመፈጸም፣ ሰራተኞች መስክ ሳይወጡ የውሎ አበል በመክፈል፣ ሳይፈቀድ
የኃላፊነት አበሎችና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ክፍያ በመፈጸም፤ መስሪያ ቤቱን ለለቀቁ ሰራተኞች ለበርካታ ወራት የደመወዝ
ክፍያ መፈጸም፤ በሚመለከተው አካል ያልተፈቀደ ግልጽ
የሆነ መስፈርት በሌለው ሁኔታ ለሰራተኞች ማበረታቻ በመክፈልና በመሳሰሉት ምክንያቶች ከ98 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ሆኖአል፡፡ ጉድ በል ጎንደር ይሏል
ይህ ነው።
ዋናው ኦዲተር በመንግስት የተቀረጹ ፕሮግራሞችና
ፕሮጀክቶች የተመደበላቸውን በጀት በአግባቡ ስራ ላይ ማዋል/አለማዋላቸውን ለማረጋገጥ የክዋኔ ኦዲት መከናወኑን የገለጹት አቶ ገመቹ የያዩ የሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ
ግንባታን በ2006 አ/ም ለመጨረስ በ2004 ውል የተፈጸመ ቢሆንም
ፋብሪካው ዛሬም ድረስ አለመጠናቀቁን፤ ከአጠቃላይ
የፕሮጀክቱ የውል ዋጋ 11 ቢሊዮን 84 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር ውስጥ 5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ለተቋራጩ የብረታ ብረትና
ኢንጀነሪግ ኮርፖሬሽን መከፈሉን፤ የፋብሪካው ግንባታ ስራ
አፈጻጸም ገና 42 ነጥብ 31 በመቶ ላይ እንደሚገኝ፣ ዝቅተኛና በእቅዱ መሰረትም ያልተከናወነ መሆኑን፤ ግንባታው ባለመጠናቀቁ
ኮርፖሬሽኑ ከባንክ ለተበደረው ብድር እስከ የካቲት 2009 ድረስ ብቻ ብር 1ቢሊዮን 826ሚሊዮን 513ሺህ ብር ወለድ መከፈሉን ገልጸዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በተራዘመ ቁጥር ምንም ገቢ ሳያመነጭ ለባንክ
የሚከፈለው ወለድ በከፍተኛ መጠን ሊያድግና በፋብሪካው ዘላቂነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳድር እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡ ከጠቅላይ
አቃቤ ሕግና ከምክር ቤቱ ጋር በመሆን ከመመሪያ ውጪ የሚፈጸሙትን ማረም አስፈጻሚዎችም እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ እንዲሰራ ተወስኖ
በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንደሆን ደግሞ ህዝቡን ማሳተፍ ተገቢ ይሆናል፤ ሕዝቡም ዋና ኦዲተር ነውና፡፡