Wednesday, 3 May 2017

ተፈጥሮን የመመለስ ስራ !!



      
                                                           ይነበብ ይግለጡ
በሀገራችን የሚካሄደው የተፈጥሮ ጥበቃ ስራ ብዙ ርቀት መሄድ ያለበት ቢሆንም ለረዥም አመታት በተከታታይ ሳይቋረጡ የተሰሩት ስራዎች ከፍተኛ ለውጥና ውጤት አስገኝተዋል፡፡ ድርቅንና የተፈጥሮ አየር መዛባትን በዘላቂነት ለመከላከልና ለመመከት የሚቻልበት ብቸኛው ሁነኛ መፍትሔ የተፈጥሮ ጥበቃ ስራን አጠናክሮ መስራት ነው፡፡
የተፈጥሮ ጥበቃ ስራ ሰፊ መስኮችን ያካትታል፡፡በዋነኛነት የተፈጥሮን የአየር ንብረት መሬቱ፣ ደኑ፣ ውሀውና አራዊቱ ተፈጥሮ በሰጠቻቸው ቤት ውስጥ እንዲሆኑ ማስቻል የተፈጥሮን አረንጓዴነት ወደነበረበት ሁኔታ ለመመለስ የሚደረገው ስራና ጥረት ነው፡፡ ስኬታማ የሚሆነው ሕዝብና መንግስት በጋራ በሚያደርገው ርብርብ ነው፡፡
የተፈጥሮ መሬት ሳይራቆት ቀድሞ ተፈጥሮ በሰጠችው መልኩ እንዲሆን ማድረግ ነው የተፈጥሮ ጥበቃ ስራ፡፡ለድርቅና ረሀብ ለተለያዩ ተፈጥሮአዊ አደጋዎች መከሰት ዋናው ተጠያቂ የሰው ልጅ ነው፡፡ ከጫካና ደኖች መመንጠር ጀምሮ መሬቶችን ማራቆት ወደ በረሀማነት እንዲለወጡ ማድረግ ከዚህም ባለፈ ከበለጸጉ ሀገራት ከባድ ኢንዱስትሪዎች የሚለቀቀው በካይ የኬሚካል ጋዝ በተፈጥሮ የአየር ንብረት ላይ ይህ ቀረው የማይባል መዛባትና አደጋ እንዲከሰት አድርጎአል፡፡
ለዚህ ነው ታዳጊ ሀገራት ከበለጸጉና ካደጉ ሀገራት ጋር ይህንኑ በተመለከተ በአለም ላይ ስለተከሰተው የአየር ንብረት መዛባትና ተከትሎ ስለመጣው የሰውን ልጅ የከፋ አደጋ ላይ የጣለ ችግር ምክክርና ድርድር ውስጥ የገቡት፡፡በእኛም ሀገር የነበረው የደን ሽፋን ተመናምኖ መሬቱ ወደ በረሀማነት ተለውጦ ኖሮአል፡፡ይህ ከግንዛቤ እጥረት ሰዎች የፈጠሩት ችግር ቢሆንም ያስከተለው ችግር በቀላሉ የሚመከት የሚመለስ አልሆነም፡፡
በደኖች መመንጠርና መመናመን የዱር አራዊትና እንሰሳት አእዋፋት ጭምር መኖሪያቸውን ለቀው ወደጎረቤት ሀገራት የተሰደዱበት፤ከየተራራው ስር ይፈልቁ የነበሩትና ትውልድን ያስተናገዱት ምንጮች የደረቁበት፤ሰብል ዘርቶ ለማብቀል ያልተቻለበት ከፍተኛ የውኃ እጥረት ችግር የተከሰተበት ይህንንም ተከትሎ በሰው ሕይወትና በእንሰሳት ላይ የሞት አደጋ በብዛት የተከሰተበት ችግር ተደጋግሞ መከሰቱ መታየቱ ከዚሁ የተፈጥሮ የአየር ንብረት መዛባት ከፈጠረው አደገኛ ችግር ጋር የተያያዘና የተቆራኘ ነው፡፡ጓሳው መነመነ ደኑ መነመነ የሚለውም ሀገርኛ አባባል ተመንጥሮ በማለቁና በመራቆቱ እንኳን የዱር አራዊት የሰው ልጅም ሊጠቀመበት አለመቻሉን የሚገልጽ አባባል ነው፡፡
ይህንን በተከታታይና በማያባራ መልኩ መልኩን እየቀያየረ በተፈጥሮ የአየር ንብረት መዛባት ምክንያት በሀገራችን ሲከሰት የኖረውን ዛሬም ያለውን ችግር በዘለቄታው መቅረፍ የሚቻለው የተፈጥሮ ጥበቃ ስራን አጎልብቶ በመስራት ብቻ ነው፡፡
ተፈጥሮ በራስዋ መንገድ ከምትፈጥረው ጫና ውጪ በአብዛኛው ለድርቅና ለረሀብ ለውሀ መጥፋትና ለድርቅ መስፋፋት ምክንያት የሚሆኑት የሰው ልጅ በራሱ በሚፈጥረው ችግር መነሻነት የሚመጡና የሚከሰቱ ናቸው፡፡ በተለይም በካይ የከባድ ኢንዱስትሪዎች ጭስ ልቀት አየሩን ከመበከሉ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ችግሮች ሰፊ ናቸው፡፡ይህንን ለመከላከል የሚቻለው ምድርን ጥንት ወደነበረችበት አረንጓዴነት ለመመለስ በመስራትና ተፈጥሮን በነበረችበት በመጠበቅ በመንከባከብ ብቻ ነው፡፡
በሀገራችን በሁሉም ክልሎች በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠረውን ሕዝብ በማስተባበርና በማሰማራት ሰፊና ግዙፍ የተፈጥሮ ጥበቃ ስራ እየሰራች ትገኛለች፡፡የተራቆቱ መሬቶችን እንዲያገግሙ ለማድረግ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የችግኝ ተከላ ስራዎች ለበርካታ አመታት ተተክለው የነበረውን የቀድሞ ገጽታና ውበት መመለስ ችለዋል፡፡
ይሄው የተፈጥሮ ጥበቃ ስራ በአዲስ አበባ፤በአማራ፤በኦሮሚያ፤በትግራይ፤በደቡብ፤ በአፋርና በቤኒሻንጉል ክልልና በሌሎችም ጭምር በስፋት ተሰርቶአል፡፡እየተሰራም ይገኛል፡፡ የተፈጥሮ ጥበቃ ስራ በያዝነው አመት በስፋት በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ተጠናክሮ ቀጥሎአል፡፡የአፈር መሸርሸርን ለመግታት የእርከን፤የችግኝ ተከላ፤የመስኖ ልማት ስራዎች፤ ያልተጠበቀ ዝናብ ቢዘንብ የውኃው ድንገተኛ ፍሰት አደጋ እንዳያስከትል ይልቁንም አደጋውን ቀልብሶ ጠቀሜታ ላለው የመስኖ ስራ እንዲውል ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ ስራዎች በባለሙያዎች ድጋፍ ተሰርተዋል፡፡
የውሀ ጉድጓዶችን በስፋት የማዘጋጀት፤ውኃው ወደመሬት ውስጥ ሰርጎ እንዲገባና እርጥበት እንዲፈጥር የማድረግ ስራዎች  በስፋት ተሰርተዋል፡፡በተለይም አሁን ወደ ክረምቱ ወራት እየተጠጋን በመሆኑ በሜትሪዮሎጂ መረጃዎች በመደገፍ ለአርሶአደሩ ጠቃሚ መረጃዎች እንዲያገኝ የማድረጉ ስራ በሁሉም ክልሎች በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በሀገራችን አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ የእለታዊ የአየር ትንበያዎች ተጠቃሚ እንዲሆን ማስተማርና ማሳወቅ በእርሻውም ሆነ ሊፈጠር በሚችለው የተፈጥሮ የአየር ንብረት አደጋ  ግንዛቤ እንዲያገኝ እንዲጠነቀቅ የሚከሰቱትን ሁኔታዎች አስቀድሞ አንዲከላከል ያስችለዋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ከጥር  ወር ጀምሮ  20 ወረዳዎች  ሲካሄድ የቆየው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ  የዘመቻ ሥራ  67 በመቶ መጠናቀቁን  ክልሉ በቅርቡ የገለጸ ሲሆን ይህም የተፈጥሮ ጥበቃ ስራው በተጠናከረ መንገድ እየተሰራ ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡ሲካሄድ  በቆየው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ 138 ሺህ ነዋሪዎች  ተሳትፈዋል፡፡የሕዝቡ ንቅናቄ  ይህን ስራ ለማሳካት ወሳኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ከዘመቻው ሥራ  በፊት  ለወረዳ አመራሮችና  የግብርና  ኤክስቴንሽን ሠራተኞች  የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና መሰጠቱ ስራውን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ በመሆኑ በሁሉም ከልሎች በተመሳሳይ መንገድ ነው እየተሰራ ያለው፡፡በተፈጥሮ  ሀብት ጥበቃ የዘመቻ ሥራው ለመጪው  ክረምት  ዝግጅት  የሚሆኑ  የእርከን፣የችግኞች እንክብካቤ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ በቤኒሻንጉል ክልል  እስካሁን  ድረስ  በአጠቃላይ  በተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ የዘመቻ ሥራ  ይሸፈናል ከተባለው   42  ሔክታር መሬት  ውስጥ  28 140 ሔክታር መሬት የሚሆነው  ተሸፍኗል፡፡
በአጠቃላይ በመላው ሀገሪቱ  በተካሄደው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ሔክታር በላይ መሬት መሸፈኑን የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ገልጾአል፡፡ በሚኒስቴሩ ከፍተኛ የተፋሰስ ልማት ባለሙያ የሆኑት አቶ ኃይለሚካኤል አየለ የአፈርና ውኃ ጥበቃየደን ተከላ ሥራዎች አገሪቱ ለአየር ንብረት ለውጥ አደጋ እንዳትጋለጥ የድርቅና የጎርፍ አደጋዎች እንዳይከሰቱ ለማድረግ ከፍተኛ ድርሻ ያለው መሆኑን ለመገናኛ ብዙሀን  ገልጸዋል፡፡
በያዝነው አመት 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሔክታር በበለጠ መሬት ላይ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ ለማከናወን ታቅዶ የስነ አካላዊ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ስራ በመስራት 167 በመቶ በተግባር ላይ ማዋል መቻሉ የተገኘውን ከፍተኛ ውጤት ያሳያል፡፡
በሕዝብ ንቅናቄ ስራው ላይ ከስልጠና ጀምሮ በቂ ዝግጅትመደረጉ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠረውን ሕዝብ ዳር እስከ ከዳር በማንቀሳቀስ ከተጠበቀው በላይ ለመስራት ተችሎአል፡፡ ሕዝብን ያማከለ ያሳተፈ ስራ ሁሌም ለውጤት እንደሚበቃ ማሳያ ነው፡፡
በሕዝብ ንቅናቄው 6 ሽህ 706 ተፋሰሶች ላይ በተከናወነው የተፈጥሮ ኃብት ልማት ስራ 19 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች መሳተፋቸው የተገለጸ ሲሆን ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሔክታር በላይ የተጎዳና ቦረቦር መሬት ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ በመከላከል እንዲያገግም ማድረግ ተችሎአል፡፡
ከተፈጥሮ ኃብት ልማትና ጥበቃ ስራው ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ 200 ሺህ መሬት አልባ ወጣቶችና ሴቶችን በማደራጀት ያገገሙ ተፋሰሶችን አልምተው እንዲጠቀሙ እቅድ መያዙ የተገለጸ ሲሆን ይህም ሕብረተሰቡን በማሳተፍ የተሻለ ውጤት ያለው ስራ ለመስራት የሚያስችል ነው፡፡ ሕዝቡ እራሱንና ቤተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ያስችለዋል፡፡
የተፈጥሮ ኃብት ልማት ስራዎች በመላው ሀገሪቱ በስፋትና በጥልቀት መካሄድ ከጀመሩበት ግዜ ጀምሮ የተራቆቱ ተራሮችና መሬቶች ወደቀደመው መልካቸው እየተመለሱ ይገኛሉ፡፡ ጠፍተው የነበሩ እጽዋት ተመልሰው በመብቀል ላይ ሲገኙ ተሰውረው የነበሩ አእዋፋት የዱር እንሰሳትም ወደ ቦታቸው መመለስ ይዘዋል፡፡ይህ ትልቅ ለውጥና ስኬት ነው፡፡














No comments:

Post a Comment