Wednesday, 17 May 2017

ድርቁን ከዚህም በላይ መቋቋም ይቻላል!




                                                          ታዬ ከበደ
በኤልኒኖ የአየር ንብረት ለውጥ ተፈጥሮአዊ ክስተት ሳቢያ በድርቅ ከሚጠቁት ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነች። በዚህም ምክንያት አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጋ  ህዝብ ለድርቅ ተጋላጭ ሆኗል። ይሁንና መንግስት የለጋሾችን እጅ ሳይጠብቅ ከመጠባበቂያ የእህል ክምችትና ከራሱ በጀት ችግሩን በመቋቋም ላይ ይገኛል። ይህም የተከሰተው ችግር ወደ ረሃብነት እንዳይሸጋገር አድርጓል። ዛሬም ቢሆን የተፈጠረውን ችግር ከዚህ በላይ መቋቋም የሚያስችል አቅም ተገንብቷል።
ለዚህ አቅም መገንባት ዋነኛው ጉዳይ ላለፉት ዓመታት መንግስትና ህዝብ በድህነት ላይ ባካሄዱት ዘመቻ ችግርን መቋቋም የሚያስችል አቅም በመገንባታቸው ነው። መንግስት ይህን አቅም ተጠቅሞ በሀገር ውስጥ ልማትን ለማካሄድ ከሚያደርገው ርብርብ ባሻገር፤ ድንገተኛ አደጋ በሚከሰትበት ወቅትም አደጋውን መቋቋም የሚያስችል ጠንካራ አቅም ገንብቷል። ለድርቅ አደጋ የተጋለጡ ዜጎችን ለመታደግ መንግስት ማናቸውንም ተግባራት ያከናውናል፤ በማከናወን ላይም ይገኛል። መንግስት የችግሩን ስፋትና ጥልቀት አስቀድሞ በመገንዘብ የተፈጠረውን ሁኔታ ለመቋቋም በዜጎችና በኢኮኖሚው  ላይ ሊደርስ የሚችለውን  ጉዳት ለማስቀረት የሚያስችል አቅጣጫ ቀይሶ ተግባራዊ እያደረገ ነው።
እርግጥ በተፈጥሮ የአየር መዛባት ምክንያት በሀገራችን የድርቅ አደጋ ሲከሰት አዲስ ነገር አይደለም። ይህ ደግሞ በተፈጥሮ ችግር ምክንያት የሚከሰት ጉዳይ በመሆኑ ምንም ማድረግ አይቻልም። ሆኖም ይህ በየጊዜው ሀገራችንን የሚጎበኛት የድርቅ አደጋ ወደ ረሃብነት እንዳይቀየር መንግስት ብርቱ ጥረት አድርጓል።
እንደሚታወቀው ባለፉት ዓመታት የመንግስት ትኩረት ምንም ዓይነት የአየር ንብረት መዛባትና ድርቅ  ቢያጋጥምም፤ ህዝባችን  የማይራብበት ሁኔታን በመፍጠር ላይ ሲረባረብ ቆመቆየቱ አይዘነጋም። የኤልኒኖ አደጋ በተከሰተበት ወቅትም አደጋውን በመቀልበስ የልማት አጋር ሀገራትን ድጋፍ እምብዛም ሳያገኝ ችግሩ ወደ ረሃብነት ሳይቀየር መቋቋሙ ይህን ጥረቱን አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑን ከማንም የተሰወረ ጉዳይ አይመስለኝም።
በእኔ እምነት መንግስት ከአጭር ጊዜ አኳያ በተፈጥሮ ችግር ምክንያት የሚከሰተውን የድርቅ አደጋ ለመከላከል በፍጥነት በመድረስና ዕርዳታ ማድረግ እንዲሁም ድጋፉ ልማታዊ  በሆነ አኳሃን ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረጉ ለዜጎቹ ያለውን የኃላፊነትና የተጠያቂነት መንፈስ ስሜትንና ቁርጠኝነትን የሚያሳይ ነው።
ለነገሩ እንኳንስ አሁን የሀገራችንን የአደጋ ተጋላጭነት አቅምን በማጎልበት ላይ በሚገኘው የልማት ስትራቴጂ ምክንያት ከፍተኛ ዕድገት እየተመዘገበና በድርቅ ነባራዊ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነን ረሃብ እንዳይፈጠር ማድረግ በተቻለበት በአሁኑ ወቅት ቀርቶ፤ የኢፌዴሪ መንግስት የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ገደማ 14 ነጥብ 5 ሚሊዮን ያህል ህዝብ ለምግብ እጥረት በተዳረገበት ወቅት እንኳን ድርቁ ወደ ረሃብ እንዳይሸጋገር ብርቱ ጥረት አድርጎ ተሳክቶለት እንደነበር የምንዘነጋው እውነታ አይደለም።
ይህ ሁኔታ ደግሞ ዝም ብሎ የተፈጠረ ሊሆን እንደማይችል ከማንም የተሰወረ ሊሆን የሚችል አይመስለኝም— መንግስት ቀደም ባሉት ጊዜያት የአርሶና የአርብቶ አደሩን ህይወት ለመለወጥ ካከናወናቸው ተገቢ ተግባራት የመነጨ እንጂ። እርግጥም የኢፌዴሪ መንግስት የአርሶና የአርብቶ አደሩ ኑሮ እንዲሻሻል ተገቢውን ትኩረት ሰጥቷል። በዚህም አርሶ አደሩ ከራሱ ተርፎ ለገበያ በማምረት ተጠቃሚ የሚሆንበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ፣ ሀገሪቱም ከግብርናው ዘርፍ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ለማድረግ የሚያስችል የለውጥ ጎዳና እንዲፈጠር አድርጓል። ለዚህ ስኬት በመንግስት በኩል የተወሰዱት እርምጃዎች በቂ ማሳያዎች ናቸው ማለት ይቻላል።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ለእርሻ የሚውል ሰፊ መሬት አላት። ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች በአርሶ አደሩ እጅ እንዳለ የሚታሰበው መሬት አነስተኛ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ካለችውም መሬት ቢሆን የሚያገኘው ምርት ዝቅተኛ ነው። አመራረቱም እጅግ ኋላ ቀር ሆኖ ቆይቷል።
ይህን ዕውነታ የተገነዘበው የኢፌዴሪ መንግስት ዘርፈ ብዙ የማሻሻል ጥረቶች አድርጓል። በውጤቱም አነስተኛ ይዞታ ባላቸው አነስተኛ የአርሶ አደሮችን ማሳ ላይ ለውጥ ማምጣት አይቻልም የሚለውን አስተሳሰብ ሰብሯል። አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች ትኩረት ከመስጠት ይልቅ ለሰፋፊ እርሻዎች ትኩረት መስጠትና ለውጥ ማምጣትን የሚሰብኩ ወገኖችን አፍ ማስያዝ የቻለ ትክክለኛ መስመርን በመከተል ውጤት ማምጣት ችሏል።
በአርብቶ አደሩም አካባቢ ተመሳሳይ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በመቅረፅና ቀደ ተግባር እንዲገባ በማድረግ ድርቅ ሊፈጥር የሚችለውን አደጋ በአያሌው መቀነስ ተችሏል። ከእነዚህ መንግስታዊ ጥረቶች ውስጥ የአርብቶ አደር የልማት ፓኬጆችን በመቅረፅ፤ አርብቶ አደሩ ከልማዳዊ የአኗኗር ባህል ወጥቶ ወደ ዘመናዊ ህይወት እንዲቀየር፣ ከአርብቶ አደሩ ጋር በመነጋገር ድርቅን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችሉ የመስኖ ልማት ስራዎችን በማስፋፋት ወደ ከፊል አርሶ አደርነት እንዲሸጋገር ብሎም ምርጥ ዝርያዎችን አግኝቶ ተጠቃሚነቱን እንዲያሳድግ፣ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር ውሃዎችን በአግባቡ የማሰባሰብ ስራዎችን እንዲያጠናክር፣ የመሰረተ ልማትና የሌሎች የልማት ዘርፎች ተቃሚ ይሆን ዘንድ በፍፁም ፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የሰፈራ ፕሮግራምን እንዲቀበል፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከርና በዚህም ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር የማድረግ ስራዎችን ማከናወኑና በማከናወን ላይ መሆኑ ጥቂት ተጠቃሽ ምሳሌዎች ናቸው።
እንደ እውነቱ ከሆነ ባለፉት ዓመታት የመንግስት ትኩረት ምንም ዓይነት  የአየር ንብረት  መዛባትና ድርቅ ቢያጋጥምም፤ ህዝባችን የማይራብበት ሁኔታን በመፍጠር ላይ ሲረባረብ ቆይቷል። እኔ እስከሚገባኝ ድረስ መንግስት ከአጭር ጊዜ አኳያ በተፈጥሮ ችግር ምክንያት የሚከሰተውን ድርቅ ለመከላከል በፍጥነት በመድረስና ዕርዳታ ማድረጉ  እንዲሁም ድጋፉ ልማታዊ በሆነ አኳኋን ጥቅም ላይ እንዲውል የክትትል አሰራርን መከተሉ አሁን ላለበት አቅም ያበቁት ይመስለኛል።
ዳሩ ግን አንዳንድ ወገኖች ይህን የመንግስትን የዕድገት ውጤት የሆነውን ችግርን በራስ አቅም የመቋቋም አቅምን ሊያኮሰምኑት ይፈልጋሉ። ይህ እሳቤያቸው ፈፅሞ ከእውነታው ያፈነገጠ ነው። እንደሚታወቀው በልማታዊውና ዴሞክራሲያዊው መንግስት የምትመራው ሀገራችን ላለፉት 15 ተከታታይ ዓመታት ባስመዘገበችው ዕድገት ችግሮችን እየተቋቋመች መጥታለች።
በእነዚህ ዓመታቶች ውስጥ ዓመንግስት ልማታዊ የግል ኢንቨስትመንቶችን በማበረታታትና የኪራይ ሰብሳቢነት አማራጮችን በማጥናት ለማስወገድ በመሞከርና በግሉ ዘርፍ የማይሰሩ የልማት ክንዋኔዎችን በመስራት፣ ያሉትን ውስን ሃብቶች መሠረታዊ ችግሮችን በሚፈቱበት የልማት ስራዎች ላይ በማዋል፣ የልማት ኃይሎችን በማቀናጀትና በመምራት፣ የህዝብ ተሳትፎን በማጎልበት እና የግል ኢንቨስትመንት በማበረታታት ፈጣን ቀጣይነትና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ዕድገትና ማህበራዊ ልማት ለማምጣት ተችሏል። ይህ አቅምም ወደፊትም ሊከሰት የሚችል ድርቅን ከዚህም በላይ መቋቋም እንደሚቻል የሚያረጋግጥ ነው።

No comments:

Post a Comment