Thursday, 4 May 2017

ምን አለኝ ሀገሬ ??




                                    ይነበብ ይግለጡ
ሳኡዲ አረቢያ በ1930ዎቹ(እኤአ) ከአለማችን እጅግ ድሀ ሀገሮች ውስጥ አንድዋ ነበረች፡፡ የዘይት ሀብት ነው ያከበራት፡፤የተማረና ብቁ የሰለጠነ የሰው ኃይል አልነበራትም፡፡ዛሬም ብዙ የላትም፡፡ለዚህ የሚወቀሰው የሳኡዲ የትምህርት ስርአት ነው፡፡የሚያተኩረው ኃይማኖት ላይ ብቻ በመሆኑ፡፡የስደተኞች መብት በአሰቃቂ ሁኔታ ይጣሳል፡፡ሰብአዊ መብታቸው አይከበርም፡፡ሴቶች ይደፈራሉ፤ስደተኞች ይታሰራሉ፡፡ይደበደባሉ፡፡ ይገደላሉም፡፡ የሰውነት ክብራቸው ተገፎ እንዲዋረዱ ይደረጋል፡፡
ከስደተኞቹ ውስጥ አንዳንዶች ገፍተው እውነቱን በአደባባይ ለመግለጽ ሲበቁ ሌሎች ደግሞ ሕጋዊ ማስረጃ የለንም ከሀገር እንባረራለን በሚል በከፍተኛ ባርነት ውሰጥ የሚኖሩ እንዳሉ አልጀዚራን ጨምሮ የተለያዩ መገናኛ ብዙሀን ሲዘግቡ ቆይተዋል፡፡በሳኡዲ አረቢያ በስደት ገብተው የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከመቶ ሺህ በላይ ይገመታል፡፡የስደቱ መነሻ ሰርቼ እራሴንና ቤተሰቤን እለውጣለሁ የሚል  ቢሆንም እየደረሰባቸው ያለው ግፍና በደል ዘግናኝ በመሆኑ ስደትን በማቆም በራስ ሀገር ላይ ሰርቶ ለመለወጥና ሕይወትን ለማሸነፍ መትጋት የሚገባቸው ለመሆኑ  ግድ የሚል  ደረጃ ላይ ተደርሶአል፡፡
በመሰረቱ ሳኡዲ አረቢያ በ1930ዎቹ(እኤአ)እጅግ በአለማችን የመጨረሻ ደረጃ ከነበሩትና ከሚቆጠሩት ድሀ ሀገሮች ውስጥ አንድዋ የነበረች መሆንዋን ዊኪፒዲያ ፍሪ ኢንሳይክሎፒዲያ ይገልጻል፡፡ በሀገሪቱ የነዳጅ ሀብት ከተገኘ በኃላ ነው ወደሀብታምነት የተለወጠችው፡፡እንዲህም ሁኖ ሀገሪቱን ዳር ከዳር የሚያንቀሳቅሳት በስደት ስራ ፍለጋ የገባው የተለያዩ ሀገራት ዜጋ ነው፡፡ሳኡዲዎች የራሳቸውን ሀገር የተለያዩ ስራዎች በሙያዊ ብቃትና ክህሎት ለመምራትና ለማስተዳደር የሚችል ከፍተኛ ዘመናዊ እውቀትና ችሎታ ያለው ሰው በብዛት የላቸውም፡፡አላፈሩም፡፡ዛሬም ችግሩ አልተቀረፈም፡፡
ትላልቅ የሚባሉት ድርጅቶቻቸው የሚመሩትና የሚተዳደሩት በውጭ ዜጎች ነው፡፡እነሱም  በደረጃ ይከፈላሉ፡፡ምእራባውያን ባለሙያዎች በመጀመሪያ ደረጃ ክብርና መብታቸው ተጠብቆ የሚሰሩ ሲሆኑ ከእነሱ ቀጥለው ሕንዳውያን ይገኛሉ፡፡
የኤሽያ ተወላጆች በተለያዩ መስኮች ተሰማርተው ይሰራሉ፡፡በቤት ሰራተኝነት በድህነት ከምትጠቀሰውና ከምትጠራው አፍሪካ በስደት የሚሄዱት ዜጎች ተሰማርተውበታል፡፡ ያማል፡፡ይቆጠቁጣል፡፡አፍሪካም እኮ መጠቀም አለመቻልዋ እንጂ በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገች ነች፡፡
እዚህ መደብ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችም ይገኛሉ፡፡ራሳቸው ሳኡዲዎች ዝቅ ባሉ የስራ መደቦች ላይ ወርዶ መስራትን በባሕላቸው እንደ ነውር የሚቆጥሩ ናቸው፡፡ለዚህ ነው አብዛኛው ስራ በስደተኞች የሚሸፈነው፡፡ቀደም ባሉ አመታት የሳኡዲ መንግስት ወደሀገሩ በሕገወጥ መንገድ የገቡ ስደተኞችን በተመለከተ ባወጣው የሰባት ወራት የምሕረትና የለቃችሁ ውጡልኝ አዋጅ የኢትዮጵያ መንግስት በሪያድ ስደተኞች ካምፕ ታስረው የነበሩትን ጭምር በማስለቀቅ ከ100 ሺህ 620 በላይ ኢትዮጵያውያንን በቀን 20 ዙር የአየር በረራ በማድረግ በሰላም ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ አድርጎአል፡፡ዛሬም ሳኡዲ አረቢያ ሕገወጥ ስደተኞች ይውጡልኝ ብላለች፡፡የእኛም ዜጎች በብዛት ይገኛሉ፡፡መንግስት ለመቀበል የራሱን ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡
ከጥቂት አመት በፊት ኢትዮጵያውያን እዛው እያሉ ከሳኡዲ ፖሊስ ጋር በተፈጠረ ግጭት የተቃውሞ ሰልፉ ሕጋዊነት የለውም በሚል በሳኡዲ ፖሊስ በተወሰደ እርምጃ ሶስት ዜጎቻችን መገደላቸው ይታወሳል፡፡ሂዩመን ራይት ዋች በተነሳው አመጽና በእስር ላይ ባሉት ሰራተኞች ላይ ሰብአዊ ጥፋት ከመከተሉ በፊት ምርመራና ማጣራት እንዲደረግ በወቅቱ የገለጸ ቢሆንም የሳኡዲ መንግስት የሰጠው ምላሽ የለም፡፡
ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛት በአፍሪካ ሁለተኛዋ ሀገር ነች፡፡በአሕጉሪቱ በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ የምትገኝ ሀገር ስትሆን አለም አቀፉ የሰራተኞች ድርጅት 27 በመቶ ሴቶች 13 በመቶ ወንዶች ስራ የላቸውም ሲል ይገልጻል፡፡የስራ ውስንነት በሀገር ውስጥ ያለው ከባድ የኑሮ ሁኔታ ኢትዮጵያውያን በነዳጅ ዘይት ሀብታም ወደሆኑት ሀገራት በብዛት እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኖአል ሲል የአልጀዚራ ዘገባ ይገልጻል፡፡ዛሬ ላይ ሁኔታው ተለውጦአል፡፡በሀገር ላይ መስራትና መለወጥ የሚችሉበት ሰፊ እድል አለ፡፡ሳኡዲ አረቢያም የአለማችን የመጨረሻዋ ድሀ ሀገር ነበረች፡፡ያከበራት ሰርቶ መለወጥ ሳይሆን የተፈጥሮ ስጦታ የሆነው የነዳጅ ዘይት ሀብት ነው፡፡ኢትዮጵያ ደግሞ ሰርታ እየተለወጠችና እያደገች ያለች ሀገር ነች፡፡
የተባበሩት መንግስታት ስደተኞች ኤጀንሲ በበኩሉ ቀደም ባሉ አመታት ከ51 000 በላይ ኢትዮጵያውን የኤደንን ባህረሰላጤ ለማቋረጥ ሲሉ እራሳቸውን አደገኛ ለሆነ ሁኔታ አሳልፈው መስጠታቸውን ገልጾአል፡፡በዚህ ሁኔታ ሪፖርቶች እንደሚገልጹት ጀልባዎች ይሰጥማሉ፡፡ወይንም ከሚፈልጉት የባሕር ዳርቻ በጣም ርቀው ያወርዱአቸዋል ሲል አልጀዚራ ቀደም ባሉ ግዜያት ዘግቦአል፡፡
በሳኡዲአረቢያ ስደተኞች ይደበደባሉ፡፡ይሰቃያሉ፡፡ሰብአዊ ክብርና መብታቸው ይገፈፋል፡፡ ይገረፋሉ፡፡በሀሰት ተከሰው ፍርድቤት እንዲቀርቡ ከተደረገ በኃላ ይታሰራሉ፡፡ከበድ ባለ ወንጀል ከተከሰሱም የሞት ፍርድ ይፈረድባቸዋል፡፡ተፈጻሚ ከሆነም አንገታቸው በሰይፍ ይቀላል፡፡ለስደተኛው ሰው ሀገር ሳያሳውቁም እርምጃ ይወስዳሉ፡፡ይህም እጅግ የከረረ አለም አቀፍ ተቃውሞ በሳኡዲ አረቢያ መንግሰት ላይ ሲያስነሳ ቆይቶአል፡፡አሁንም አልበረደም፡፡ከዚህ ሁሉ መከራና ስቃይ ይልቅ በሀገር ተከብሮ መኖር እየተቻለ ለምን እዚህ አይነቱ ጭንቅ ውስጥ ይገባል ብሎ ራስን መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡
ስደተኞች በሳኡዲ እስር ቤት ከታሰሩ ምግብ እራሳቸው እንዲገዙ ይደረጋሉ፡፡ይህ የትም ሀገር ላይ አይደረግም፡፡አሳሪው መንግስት ከሆነ ለታሰረው ሰው ምግብ ሕክምና በነጻ ያቀርባል፡፡በሳኡዲ አረቢያ እስርቤቶች የታሰሩ ዜጎች እንደሚገልጹት ከሆነ ምግብ ሕክምና አያገኙም፡፡በረሀብ በበሽታ ይቀጣሉ፡፡በፖሊሶች ይደበደባሉ፡፡ከሳኡዲ ለቀው እንዲወጡ ሲደረግ ያፈሩት ንብረት ቴሌቪዥን አልጋ ፍሪጅ ወዘተ ሸጠውት እንኳን እንዲወጡ አይፈቀድላቸውም፡፡ትተውት እንዲወጡ ነው የሚደረገው፡፡
ከሚሊዮን በላይ የሆኑ የኤሽያ ስደተኞች ከሳኡዲ ተባረዋል፡፡አላማው የበለጠውን ስራ ሳኡዲዎች እንዲሸፍኑት ለማድረግ ነው፡፡ኢትዮጵያውያኑ በሳኡዲ ፖሊስ የተፈጸሙትን የግፍ ድብደባና የግድያ ወንጀሎች በሞባይሎቻቸው ቀርጸው ይዘውታል፡፡
በአንድ የሳኡዲ አረቢያ እስርቤት ብቻ በተጨናነቀ መልኩ 900 እስረኞች ታፍገው ከዛም ውስጥ ኢትዮጵያውያን እንደነበሩበት የሚገልጸው ኢትዮጵያዊ ከ24 ሰአታት በኃላ ትንሽ ምግብ እንደሰጡዋቸው የሚፈልጉትን ምግብና ውኃ በከፍተኛ ውድ ዋጋ እንዲገዙ መገደዳቸውን ይናገራል፡፡ሀዋ ግዛው በኦማንና በሳኡዲ አረቢያ በቤት ሰራተኝነት ያገለገለች ሲሆን ከፍተኛ መንገላታት እንደደረሰባት ታስረዳለች፡፡
በጄዳ እስርቤት ውስጥ 15 ቀናት ማሳለፍዋን ምግብ መጸዳጃ ቤት ሆስፒታል መጠቀም እንደማይቻል ገልጻለች፡፡አሰሪዎችዋ የሰራችበትን ገንዘብ እንደከለከሉዋት ተመልሳ ወደዛ ሀገር መሄድ እንደማትፈልግ ሌሎችም ዜጎችም እንዳይሄዱ ማስጠንቀቅ እንደምትፈልግ ተናግራለች፡፡ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተመላሽ ስደተኞቸን በተመለከተ አብሮ የሚሰራው አለምአቀፉ የስደተኞች ድርጅት የኢትዮጵያውያኑ የአካልና የአእምሮ ሁኔታ በከባድ ሕመም ውስጥ እንደሚገኝና የሚያሳስበው መሆኑን ቀደም ባሉ ግዜያት ገልጾአል፡፡
በሳኡዲ አረቢያ የሚገኙት የውጭ ዜጋ የሆኑ ሰራተኞች ቁጥር እስከ 2013 ድረስ 9 ሚሊዮን ይጠጋ የነበረ ሲሆን ወደ ሀገሪቱ መፍለስ የጀመሩት የነዳጅ ዘይት ከተገኘበት ከ1930 ጀምሮ መሆኑን ዊኪፒዲያ ፍሪ ኢንሳክሎፒዲያ ይገልጻል፡፡ሳኡዲ አረቢያ በውጭ ተወላጆች ድጋፍ የቆመች ሀገር ነች፡፡አሁንም በቴክኒክ ስራ ከፍተኛ ቦታዎች በእርሻ በጽዳትና በቤት በኢንዱስትሪዎች የውስጥ አገልግሎት ውስጥ በብዛት የሚሰሩት የውጭ ዜጎች ናቸው፡፡
ምእራባውያንና ሕንዶች ከፍተኛውን ቦታ ይይዛሉ፡፡የአፍሪካና የደቡብ ምስራቅ ኤሽያ ተወላጆች ዝቅተኛ ቦታዎች ላይ ይሰራሉ፡፡ ሰፊ የሆነ የነዳጅ ዘይት ሀብትዋን ለመጠቀም የግድ የውጭ ዜጎችን እውቀትና ጉልበት በስፋት ከመጠቀም ሌላ አማራጭ አልነበራትም፡፡ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኃላ ወደ ሳኡዲ የገባው የቴክኒክ የባለሙያና የአስተዳደር ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን መረጃዎች ይገልጻሉ፡፡
በ1985(እኤአ) የዘይት ዋጋ በማሽቆልቆሉ የውጭ ሰራተኞችን ቁጥር በተለይ ከኤሽያ የሄዱትን በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀነስ አድርጋለች፡፡በ2012 በሳኡዲ የወጣ ኦፌሴላዊ መረጃ ዜጋ ያልሆኑ የውጭ ሀገር ሰራተኞች 66 በመቶ የሚሆነውን ስራ መሸፈናቸውን በሳኡዲ አረቢያ የስራ አጥ ዜጎች ቁጥር 12 በመቶ መሆኑን የውጭ ዜጎች በአማካይ ወደየሀገራቸው 18 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በየአመቱ እንደሚልኩ ያሳያል፡፡
ቸግሩ የራሳቸው የሳኡዲዎች ነው፡፡ባለሙያ ለሚጠይቀው ስራ ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎችን ለማፍራት አለመቻላቸው፤የትምህርት ስርአታቸው በሀይማኖት ላይ ያተኮረ መሆኑ ለችግሩ መግዘፍ ስራዎች በውጭ ሰዎች ለመሸፈናቸው በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡
በ2010 የወጣው የሲአይኤ ወርልድ ፋክት ቡክ እትም በሳኡዲ አረቢያ ዜጋ ያልሆኑ የውጭ ዜጎች ቁጥር 31 ፐርሰንት እንደሆነ ይገልጻል፡፡
የሳኡዲ አረቢያ ሕግ ለስደተኞች በቂ ጥበቃና ከለላ አይሰጥም፡፡ዘ ጋርድያን ቀደም ባሉ አመታት እንደዘገበው ወደ ሳኡዲ አረቢያ ለመሄድ የሚመለመሉት ሰዎች በራሳቸው ሀገር ሆነው ለሚልኩ ኤጀንሲዎች ከፍተኛ ገንዘብ ይከፍላሉ፡፡ስፖንሰሮች ሰራተኞቹ ወደሀገራቸው ከገቡ በኃላ ፓስፖርታቸውን ተቀብለው ይወርሱአቸዋል፡፡አንዳንዴ አሰሪዎች የሰራተኞችን ፓስፖርት ተቀብለው ይወስዳሉ፡፡የትም እንዳይንቀሳቀሱ ቦታ እንዳይቀይሩ መሆኑ ነው፡፡ከባርነት በምንም አይለይም፡፡
ሴቶች ይደፈራሉ፤በስራ ቦታቸው ከአቅም በላይ እንዲሰሩ ይገደዳሉ ሲል አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ይገልጻል፡፡ያሉበትን ሁኔታ ለባርነት ቅርብ የሆነ ሲል ይገልጸዋል፡፡ጥልቀት ያለው የጾታ የሀይማኖት የዘር መድልዎና በደል እንደሚፈጸምባቸው አጋልጦአል፡፡አስገድዶ ማሰር፤ፍርድ ቤት ማቅረብና በጭካኔ የተሞላ ቅጣት ሁሉ የሚፈጸምባቸው መሆኑን አስታውቆአል፡፡በሀሰት በወንጀል ተከሰው ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲቀጡ ይደረጋል፡፡ቋንቋውን ለመነጋገር አይችሉም፡፡አስተርጓሚም አይቀርብላቸውም፡፡ ሲከሰሱ የሀገራቸው መንግስት እንዲያውቅ አይደረግም፡፡የሞት ፍርድ ይፈረድባቸዋል፡፡
የስደተኞቹ ሀገር መንግስት ካወቀ የሞት ፍርዱን ሳኡዲዎች ተግባራዊ ለማድረግ ይከብዳቸዋል፡፡ለዚህ ነው የማያሳውቁት፡፡በ2011 ሩያቲ ቢንቲ ሳቱቢ የተባለች ኢንዶኔሽያዊት የቤት ሰራተኛ የአሰሪዋን ሚስት ገድላለች በሚል ከተከሰሰች በርካታ አመታት በኃላ አንገትዋ በሰይፍ ተቀልቶ ተገድላለች፡፡ግድያውን በቪዲዮ ቀርጸው ኦንላይን በማስተላለፋቸው ከፍተኛ ውግዘት ደርሶባቸዋል፡፡
በመስከረም 2011 አንድ ሱዳናዊ ስደተኛ ሰራተኛ ተወንጅሎ አንገቱ በሰይፍ ተቀልቶአል፡፡ድርጊቱን አሜንሲቲ አውግዞታል፡፡በጥር ወር ሪዛና ናፊክ የተባለች የሲሪላንካ ስደተኛ የቤት ሰራተኛ ጥበቃ ታደርግለት የነበረን ሕጻን ገድላለች በሚል በቀረበባት ክስ ከተፈረደባት በኃላ አንገትዋ ተቀልቶ ተገድላለች፡፡ይህ የሳኡዲዎች ፍርድና ግድያ አለም አቀፍ ትኩረት በመሳቡ በሳኡዲ መንግስት ላይ ከፍተኛ ውግዘት ደርሶበታል፡፡
ሲሪላንካ አምባሰደርዋን በወቅቱ ወደ ሀገርዋ እንዲመለስ አድርጋለች፡፡ተመሳሳይ ብዙ ዘግናኝና ሰቅጣጭ በውጭ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ኢስብአዊ ድርጊቶች ወንጀሎች በሳኡዲ አረቢያ ሞልተው ተርፈዋል፡፡ሰብአዊ ክብር ማጣትና ውርደት፤ መደፈር፤መገደል ወዘተ፡፡
ከዚህ ሁሉ ስቃይና መከራ ይልቅ በሀገር ላይ ሰርቶ ራስንና ቤተሰብን መለወጥ ማሳደግ እንደሚቻል በማመን ስደት እንዲገታ ለማድረግ መረባረብ አለብን፡፡ዜጎቻችን ይህንን በመሰለ ፈተናና መከራ ውስጥ ሊገቡ አይገባቸውም፡፡የተሻለች በመልማትና በማደግ ላይ የምትገኝ ሀገር አላቸው፡፡የዜግነት መብትና ክብራቸው ተከብሮ የሚኖሩባት ሀገር አላቸው፡፡ በአቅማቸው ሰርተው ማደግና መለወጥ ይችላሉ፡፡
ተደራጅተው ከመንግስት ብድር በመጠየቅ አዋጪ የሚሉትን ስራ መስራት እየሰሩም ማደግ ይችላሉ፡፡እንዲህ አይነቱን የዜግነት ክብርን የሚያዋርድ፤ራስን ለባርነትና ለከፋ ሕይወት አሳልፎ ከመስጠት ድርጊት ሁሉም ዜጋ የችግሩን ክብደት አይቶ ከስደት መቆጠብ  ስደት ይብቃ ማለት መቻል አለበት፡፡
ዜጎች ለስራ ወደውጭ ሀገር መሄድ ከፈለጉ ሕጋዊ ሁነው በመንግስት እውቅና አግኝቶ ተመዝግበው ቢሄዱ ለሕይወታቸው ዋስትና ያለው መሆኑን መረዳት አለባቸው፡፡የማንም መጫወቻ ከመሆን ይድናሉ፡፡ምንም ሆነ ምን ሀገርን የመሰለ ክብርና ጸጋ ሀገርን የመሰለ መከበሪያ የትም ሆነ የት ቢሄዱ አይገኝም፡፡ምንአለኝ ሀገሬ እንዲሉ!!

No comments:

Post a Comment