Wednesday, 17 May 2017

ከራስ ታሪክ ስለ መማር አስፈላጊነት




ሰለሞን ሽፈራው
     እንግዲህ ወርሃ-ግንቦት ላይ ነው አይደል የምንገኘው? ስለዚህም ከዛሬ 26 ዓመት በፊት ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ ህዝቦች ፀረ ጭቆና የትጥቅ ትግል ስላለፈበት ታሪካዊ እውነታ አንስተን አንዳንድ ጠቃሚ ተሞክሮዎችን ብንለዋወጥ ምን ይለናል? ኧረ እንደኔ እምነት ከሆነስ ከዚያን ጊዜው ፈርጀ ብዙ ፈተናን በፅናት ተጋፍጦ ማለፍ የጠየቀ ውጣውረድ ውስጥ እየነቀስን በ መውሰድ፤ ለዛሬዋ ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት ጥንካሬ ማዳበሪያነት ልንጠቀምባቸው የሚገባ የትግል መርሆዎች ጥቂት እንዳልሆኑ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡
     ለማንኛውም ግን ይህቺን ማስታወሻ እንድፅፍ የገፋፋኝ ዋነኛ ምክንያት፤ የካቲት 2009 ዓ.ም ታትሞ ከወጣው ዘመን መፅሔት ጋር ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ ያደረጉት ሁለት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ከፍተኛ የአመራር አካላት ለመፅሔቱ የሰጡት ሃሳብ እንደሆነ ልብ ይባልልኝ፡፡ ሁለቱ የገዥው ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች፤ የኦ.ህ.ዴ.ድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅህፈት ቤት ኃላፊውና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባሉ አቶ በከር ሻሌና እንዲሁም ደግሞ የብአዴኑ  አቶ ዓለምነው መኮንን እንደነበሩም ይታወሳል፡፡ እንግዲያውስ ሁለቱም በተጠቀሰው ተመሳሳይ ሃላፊነት ላይ የሚገኙ ከፍተኛ የየድርጅታቸው አመራር አካላት ለዘመን መፅሔት በሰጡት የወቅቱን ሀገራዊ ፖለቲካ የሚመለከት ቃለ ምልልስ ላይ በርካታ ተሃድሶ - ተሃዶሶ የሚሸትቱ ቁምነገሮችን እንዳካፈሉን እየገለፅኩ፤ ከዚያ መሀል አንዳንድ ነጥቦችን ብቻ እንዳነሳ ይፈቀድልኝ፡፡
     ይህን ስልም ደግሞ፤ በተለይም የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ፅህፈት ቤት ሃላፊና የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት አቶ አለምነው መኮንን “ስለትምክህት ሲነሳ ሰፊውን አማራ ህዝብ የሚወክል አድርገው የሚወስዱ አሉ፤ ይህ እጅግ የተሳሳተና የተዛነፈ አስተሳሰብ ነው” በሚል ዓብይ ርዕስ ዙሪያ የሰጡት ማብራሪያ ሁላችንንም የሚያስማማ ሆኖ እንዳገኘሁት ለመጠቆም ያህል ነው፡፡ በአጠቃላይ የወቅቱ ፖለቲካዊ ችግራችን ዋነኛ ምክንያቶች ተደርገው የሚቆጠሩት የትምክህትና የጠባብ ብሔርተኝት ፅንፈኛ አመለካከቶች አንድን ህዝብ እንደ ህዝብ ይወክላሉ ብሎ ማመን መሰረታዊ ስህተት ስለመሆኑ ሁለቱ የኢህአዴግ ከፍተኛ የአመራር አካላት ለመፅሔቱ በሰጡት ቃለ-ምልልስ ላይ አሳምረው እንዳስቀመጡት ነው የተረዳሁት፡፡
     ስለዚህም፤ ትምክህተኝነት ተብሎ ስለሚፈረጀው የአስተሳሰብ ፅንፍ በተነሳ ቁጥር ጉዳዩን ከመላው የአማራ ህዝብ ጋር ሊያያይዙት የሚቃጣቸው እነማን እንደሆኑ በአቶ ዓለምነው ቃለ ምልልስ ላይ የተብራራበት አግባብ አሳማኝና ምክንያታዊ የመሆኑን ያህል፤ እንዲሁም አቶ በከር ሻሌ ለመፅሔቱ የሰጡት ማብራሪያም ጠባብነት ከሰፊው የኦሮሞ ህዝብ ጋር ተቆራኝቶ የሚገለፅበት ምንም ዓይነት መሰረታዊ ምክንያት እንደሌለ አሳምረው እንደገለፁት ነው ደፍሮ መናገር የሚቻለው፡፡ ስለሆነም ሁለቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ከፍተኛ የአመራር አካላት፤ ይልቁንም ደግሞ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ለተስተዋለው የፀጥታ ችግር መንስኤ እንደሆኑ ተደርገው በሚወስዱት የፅንፈኝነት መገለጫ አመለካከቶች ዙሪያ የሰጡትን ምላሽ ተጨማሪ ሃሳብ ለማከል ስል ነው ዛሬ እቺን ሃተታዬን ለመጫጫር የፈለግኩት፡፡
     እናም ከዚህ አኳያ ለሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የሚያገለግል ጠቃሚ ልምድ አድርጌ የምወስደው ጉዳይ ቢኖር፤ አንጋፋው የግንባሩ አባል ድርጅት ህወሐት በተለይም ለድፍን 17 ዓመታት በተካሔደው የትጥቅ ትግል፤ ጉዞ መሰል የአስተሳሰብ መዛነፎችን እያረቀ ለማቃናት ሲል ያሳየውን ያላሰለሰ ጥረት ነው፡፡ ስለሆነም ድርጅቱ ከተመሰረተበት 1967 ዓ.ም ጀምሮ ያነገበውን መሰረታዊ ዓላማ ሊፃረር በሚችል መልኩ የሚንፀባረቁ የአመለካከት ችግሮችን አምርሮ ከመታገል የቦዘነበት አጋጣሚ እንዳልነበርና ይልቁንም ደግሞ ጠባብ ብሔርተኝነት የሚገለፅበት አስተሳሰብ ላይ ያልተቋረጠ የአመለካከት ማጥራት ትግል እያደረገ እንደመጣ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡
     ለዚህ አስተያየቴ ጥሩ አብነት ተደርጎ ሊቀርብ የሚገባውም፤ ህወሐት ሁለተኛውን መደበኛ ድርጅታዊ ጉባኤውን ባካሔደበት የ1976 ዓ.ም መድረክ ላይ እንደመፈክር የተወሰደው መሪ ሃሳብ “ወያነና አካል ወያነ ኢትዮጵያ እዩ!” ማለትም “አብዮታችን የኢትዮጵያ አብዮት አካል ነው” የሚል እንደነበር ማስታወስ ይመስለኛል፡፡ በወቅቱ ይህ የሁለተኛው መደበኛ ጉባኤ መሪ መፈክር ወይም ሃሳብ ከመቸውም ጊዜ ይልቅ ጎላ ባለ መልኩ እንዲስተጋባ የተወሰነበት ዋነኛ ምክንያትም ደግሞ፤ ህወሐት መራሹን የትግራይ ህዝብ ፀረ ብሔራዊና መደባዊ ጭቆና የትጥቅ ትግል ሀገር አቀፋዊ ግብ የሌለው ለማስመሰል የሚሞከርበት የአንዳንድ እንደ ኢ.ህ.አ.ፓ ያሉ ትምክህተኛ የፖለቲካ ሃይሎች አሉታዊ ፕሮፓጋንዳ ሊያሳድር ይችል የነበረውን ተፅእኖ ለማስወገድና ምንም ዓይነት የአመለካከት ብዥታ ሳይኖር ሁሉም አባል ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመመስረት ያለመ ተልዕኮውን ለማሳካት በፅናት መታገሉን እንዲቀጥል ለማድረግ ሲባል እንደነበር ተደጋግሞ የተገለፀ ጉዳይ ነው፡፡
     እንግዲያውስ ከዚያን ጊዜ በፊትም ሆነ በኋላ በነበረው የትጥቅ ትግሉ ታሪክ ውስጥ፤ ህዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ (ህወሐት) መላው የሀገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክንዳቸውን አስተባብረው የአፄ ኃ/ስላሴን ፊውዳላዊ ስርዓተ መንግስት ለማንኮታኮት እንዲነሱ ምክንያት የሆነውንና ግን ደግሞ በደርግ ስልጣን መጨበጥ ምክንያት ተኮላችቶ የቀረበውን የስርነቀል ለውጥ ፍለጋ ሂደት፤ ወይም ደግሞ የኢትዮጵያን አብዮት ግቦች ዳር ለማድረስ ያለመ ዓላማ አንግቦ የሚታገል የፖለቲካ ድርጅት መሆኑን ካለመገንዘብ በሚመነጭ የአመለካከት ችግር ላይ የሚያወላውል የእርምት እርምጃ የተወሰደበት አጋጣሚ ጥቂት እንዳልነበር ማስታወስ አይከብድም፡፡ ይህን ስንልም ደግሞ፤ ህወሐት መራሹ የትግራይ ህዝብ ፀረ ጭቆና የትጥቅ ትግል ሂደት ከጊዜ ወደጊዜ ክንዱን እያፈረጠመ ቀጥሎ ደርግን ያህል እጅጉን የገዘፈ የድህነትና የኋላ ቀርነት ዘመኛ ጨርሶ እንዲወገድ በማድረግ ረገድ ታሪክ የማይዘነጋውን አውንታዊ ሚና ለመጫወት የበቃው በተለይም የጠባብ ብሔርተኝት መገለጫ ተደርጎ የሚወስደውን ፖለቲካዊ የአስተሳሰብ ችግር ያለማሰለስ እየታገለና ድርጅታዊ ቁመናውን ከመሰል የአመለካከት መዛነፎች እያፀዳ ነው ማለታችን ይሆናል፡፡
     እንዲያውም እንደኔ እንደኔ ከሆነስ፤ ህወሐት እንደአንድ ከአርባ ዓመታት በላይ በዘለቀ የትግል ሂደት ውስጥ ተጉዞ የመጣ አንጋፋ የፖለቲካ ድርጅት፤ ለሌሎቹ የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች እጅግ ጠቃሚ ተሞክሮ የሚያስተላልፍበት ገፅታው፤ በተለይም እኛ ኢትዮጵያውያን ህዝቦች ከትናንቱ የጋራ ታሪካችን የወረስናቸውን እንደ ትምክህትና ጠባብ ብሔርተኝነት ዓይነቶቹን ኋላ ቀር አስተሳሰቦች ፊት ለፊት እያወጣ በምክንያታዊ ትንተናው ሲፋለማቸው የተስተዋበት ፅኑ አቋም ነው ቢባል ተገቢነት ይኖረዋል ባይ ነኝ፡፡ ስለዚህም፤ ህወሐት ከየካቲት 1967 ዓ.ም እስከ ግንቦት 1983 ዓ.ም ድረስ በተካሔደው የትጥቅ ትግል ዘመን ታሪኩ ውስጥ ያጋጠሙትን ከአባላቱ የአመለካከት ብዥታ የሚመነጩ ፈተናዎች ሁሉ፤ እንዴት ባለ ከዴሞክራሲያዊ ባህሪው በሚመነጭ ድርጅታዊ የችግር አፈታት ዲስፕሊኑ እየተሻገራቸው እንደመጣ መለስ ብሎ የማስታወስና ጠቃሚ ልምድ የመቅሰም ፍላጎቱ ያለው ሌላ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ በእርግጥም ጠቃሚ ቁምነገሮችን መማር የማይቻልበት ምክንያት እንደማኖር ነው እኔ በግሌ የሚሰማኝ፡፡
     ህወሐት (ኢህአዴግ በትጥቅ ትግሉ ዘመን ያጋጠሙትን ከአንዳንድ አባላቱ የአስተሳሰብ መዛነፍ የሚመነጩ የጠባብነት ዝንባሌ መገለጫ ችግሮች፤ እንደየወቅቱ ሁኔታ በሚቃኝ የመፍትሔ ፍለጋ ዘዴ አማካኝነት ተወያይቶ ለመቅረፍ ከመጣር ቦዝኖ የማያውቅ ድርጅት ስለመሆኑ ሲወሳ፤ አብረው ከሚነሱት የታሪክ አጋጣሚዎች አንዱን ብቻ ለአብነት ያህል ማስታወስ በቂ ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም፤ ከዚህ አኳያ ለሌሎቹ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የተሻለ ተሞክሮ ሊያስጨብጥ ይችላል የምለው ጉዳይ፤ በተለይም የትጥቅ ትግሉ ሂደት ሊገባደድ ግድም የተስተዋለውን የጠባብ ብሔርተኝት አዝማሚያ የተንፀባረቀበት የህወሐት ታጋዮች የአመለካከት ችግርና ድርጅቱ ያን ችግር ከምንጩ ለማድረቅ የቻለበትን የመፍትሔ እርምጃ ነው፡፡
     ስለዚህም፤ ከዛሬ 26 ዓመት በፊት፤ የደርግ ኢ.ሰ.ፓ.ን ግዙፍ የወታደራዊ አፈና መዋቅር ከመላው የትግራይ ምድር ተጠራርጎ እንዲወጣና ወደመሀል አገር እግሬ አውጭኝ ብሎ እንዲሸሽ ለማድረግ የበቃው የህወሐት (ኢህአዴግ ህዝባዊ ሰራዊት፤ ተሸናፊዎቹን የወታደራዊው መንግስት ክፍለ ጦሮች እያሳደደ መከተሉን ቀጥሎ፤ ከወልዲያ ወደ ደብረታቦር የሚያመራውን የቀኝ ክንፍ የያዘው የሰራዊታችን ክፍል በጥቂት ቀናት ውስጥ የባህር ዳር ከተማን ደጃፍ ያንኳኳበትን የድል አድራጊነት ግስጋሴውን ሲያፋጥን፤ እንዲሁም ደግሞ የበስተግራውን ክንፍ እንዲይዝ የታዘዘው የታጋዮች ሃይል ሰሜንና ደቡብ ወሎን ብቻም ሳይሆን እስከ ሰሜን ሸዋ ድረስ ዘልቆ ከመግባት የሚያግደው አልተገኘም ነበር፡፡
     ይህ ሲሆን የተስተዋለው በ1982 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ እንደነበርም የሚዘነጋ ጉዳይ አይደለም፡፡ በተለይም ደግሞ እኔ ራሴ በነበርኩበት የደቡብ ጎንደሩ ደብረ ታቦር ግንባር፤ ትርጉም ያለው የመከላከል ውጊያ ሳያጋጥመው ባህርዳርን ለመያዝ አንድ ስንዝር ያህል ርቀት ብቻ ቀርቶት የነበረው የኢህአዴግ ህዝባዊ ሰራዊት፤ በድርጅቱ ትዕዛዝ ለጊዜው ግስጋሴውን እንዲገታና ወደኋላ እንዲመለስ መደረጉን በዚህ አጋጣሚ አስታውሼው አልፍ ዘንድ ይሰማኛል፡፡ እናም ያኔ ደብረታቦር ግንባር በመባል ይታወቅ የነበረውን መስመር ተከትሎ በደርግ ጦር ላይ የጀመረውን የማጥቃት እርምጃ እየወሰደ ባህርዳር ደጃፍ ደርሶ የነበረው የኢህአዴግ ሰራዊት በድርጅታዊ ትዕዛዝ ወደኋላ ተመልሶ ታሪካዊውን የጎራ ተራራ እንደዋነኛ ገዥ መሬት በመውሰድ፤ እዚያው አካባቢ ይዞታውን እያጠናከረ ይቆይ ዘንድ መወሰኑን ተከትሎ ነው አንዳንድ የህወሐት ታጋዮች ያልተጠበቀ ዓይነት የፍትሐዊነት ጥያቄ ማንሳት የጀመሩት፡፡
     ማለትም፤ በወቅቱ ይስተዋል የነበረው ረጅም ርቀት ያለውን የእግር ጉዞ ያለማቋረጥ ለመጓዝ የመገደድ ሁኔታ ጨምሮ፤ አጠቃላይ ውጣ ውረዱ ከማይቀረው የመድማት፣ የመቁሰልና እንዲሁም የህይወት መስዋዕትነት የመክፈል ጉዳይ ጋር ሲደማመር ሊያሳድር ከሚችለው አሉታዊ ጫና አኳያ፤ ያልተለመደ ዓይነት የመሰላቸት መንፈስ ያጠላባቸው አንዳንድ ጓዶች “እኛ የታገልነው ከአብራኩ የከፈለንን የትግራይ ህዝብ እንደ የሐውዜን ሰማዕታት በደርግ ኢ.ሰ.ፓ አረመኔያዊ ጥቃት ከማለቅ መታደግ ይጠበቅብን ስለነበር እንጂ የአማራውንና የኦሮሞውን አገር ነፃ ለማውጣት ነው እንዴ!?” እያሉ ዕርስ በርሳቸው ሲነጋገሩ ተደመጡ፡፡
     ይልቁንም ደግሞ በወቅቱ የነበረውን ከጉና ተራራው ሰማይ ጠቀስ ከፍታ የሚመነጭና እስከ አጥንት ዘልቆ የሚሰማ እጅጉን ከባድ ቅዝቃዜ ወይም ብርድ መቋቋም ያቃታቸው አንዳንድ ጓዶቻችን ቅሬታውን እንደመልካም አጋጣሚ ሊጠቀሙበት ከመፈለጋቸው የተነሳ “ለመሆኑ ሌሎቹ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የት አሉ? የነኢ.ህ.ዴ.ን (ብአዴንና ኢ.ህ.ዴ.ድ. ጓዶች አብረውን ወደ ውጊያ የማይገቡበት ምክንያት ምንድነው? እንዴ ሁሉም የየራሱን ቀምበር ሊሸከም እየተገባ እኛ የትግራይ ልጆች ብቻ የመስዋዕት በግ የምንሆን ምን ዕዳ አለብንና ነው ጃል!?” ወደሚል ተጨማሪ ሃሳብ አዳብረውት እንደነበር ማስታወስ ይቻላል፡፡
     በዚህ መሰረትም፤ የፍትሐዊነት ጥያቄውን ያነሱት የህወሐት ሰራዊት አባላት ቁጥር ከቀን ወደቀን እየጨረመ ሲሔድ የተስተዋለበት ክስተት ከመከሰቱም ባሻገር፤ የአስተሳሰብ ችግሩ የባሰባቸው በርካታ ታጋዮች የየራሳቸውን ቡድን እየፈጠሩ ከነሙሉ ትጥቃቸው ወደትግራይ መመለስ የጀመሩበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበረም ነው የሚታወቀው፡፡ የያኔውን የአመለካከት ወረርሽኝ ከደብረታቦር ግንባር ውጭ ይገኙ ወደነበሩት የህወሐት /ኢህአዴግ ክፍለ ሰራዊቶች እንዲዛመት የማድረግ አሉታዊ ሚና ለመጫወት ሞክረዋል ተብለው የሚወቀሱ አኩራፊዎች እንደነበሩም ትዝ ይለኛል፡፡ ይህን የአንድ ሰሞን ክስተት ሲያንፀባርቁ ከተስተዋሉ የችግሩ ሰለባዎች መካከል አንዳንዶቹ “ደርግ ወደ ትግራይ እንዳይመለስ እምባ አላጌና ግራት ካሱ ላይ ምሽግ ሰርተን እንከላከላለን” የሚል አቋም ያራምዱ እንደነበር ሰራዊቱ ውስጥ በቀልድ መልክ ሲነሳ መስማቴንም አስታውሳለሁ፡፡
     ደግነቱ ግን፤ ድርጅታችን ህወሐት በተለመደው የውስጣዊ ትግል ባህሉ አማካኝነት ያኔ የተስተዋለው የጠባብ ብሔርተኝነት ኋላ ቀር አስተሳሰብ አዝማያ ሰለባ የመሆን ዕጣ የገጠማቸው ታጋዮች፤ ከአመለካት ብዥታ እንዲፈወሱና ወደቀድሞው የዓላማ ፅናታቸው እንዲመለሱ ስላደረገ የድል ጉዟችን እንብዛም አልተጓተተም ነበር፡፡ እናም ያኔ በቋፍ ላይ የነበረውን የደርግ ኢ.ሰ.ፓ ወታደራዊ የአፈና መዋቅር እንደስርዓት ጨርሶ የመንኮታኮቱ መልካም ዜና ለመላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተበሰረበት የግንት 20ው ታሪካዊ ድል ከአንድ አመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ እውን ሊሆን ቻለ፡፡
     ታዲያ ዛሬ ላይ እጅጉን በጎላና በሰላ መልኩ ሲፈታተነን የሚስተዋለውን ፈርጀ ብዙ ገፅታ ያለው አመለካከት ችግርስ በተመሳሳይ ህዝባዊ ህክምና (ክትባት) እንዲፈወስ በማድረግ የኢትዮይያን የህዳሴ ጉዞ አጠናክረን ማስቀጠልና እንዲሁም ዳር ማድረስ የማንችልበት ምክንያት ይኖራል እንዴ? እንደኔ እምነት ከሆነ ያን ከማድረግ የሚያግደን ተጨባጭ ምክንያት የለም ባይ ነኝ፡፡ 
     ስለዚህም ዋናው ቁም ነገር፤ ከራስ ታሪክ የመማርን አስፈላጊነት በቅጡ ከመገንዘብ በሚመነጭ ኢህአዴጋዊ የፖለቲካ ባህል የተቃኘ የትግል መንፈስን መላበስና ህዝቡ ለዘለቄታዊ የጋራ ዕጣፈንታው የሚበጀውን ውሳኔ ይሰጥ ዘንድ ዕድል የሚያገኝበትን መሰል የውይይት መድረክ መፍጠር መቻል ነው እንጂ አሁንም ቢሆን ተመሳሳይ መፍትሄ ማስቀመጥ አያዳግትም ባይ ነኝ እኔ፡፡ ለማንኛውም ግን ፈጣሪ ቀና ቀናውን የምናስብበትን ልቦና እንዲሰጠን እየተመኘሁ እነሆ ለዛሬው ሃተታዬን እዚህ ላይ አቃለሁ፡፡ መዓሰላማት!

    

No comments:

Post a Comment