ብ. ነጋሽ
ኢትዮጵያ
ዘንድሮም በአየር ንብረት መዛባት የተፈጠረ ድርቅ ተጽእኖ ስር ወድቃለች።
የድርቁ ተጽእኖ ያረፈው በኦሮሚያ የቦረናና፣ ጉጂና ምስራቅ ሃረርጌ ዞኖች፤ በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ደቡብ ኦሞ ዞን
ሰገን ወረዳዎች፤ የኢትዮጵያ ሶማሌ ዘጠኝ ዞኖች፤ እንዲሁም የተለያያ የአፋር አካባቢዎች ላይ ነው። እነዚህ አካባቢዎች በአብዛኛው
ቆላማና የአርብቶ አደር መኖሪያ አካባቢዎች ናቸው። በዚህ የድርቅ ተጽእኖ 5 ነጥብ 6 ሚሊየን ህዝብ ለአስቸኳይ ግዜ የምግብ እርዳታ
ጠባቂነት ተዳርጓል። ባለፈው ዓመት 10 ነጥብ 2 ሚሊየን ህዝብ ለድርቅ ተጽእኖ ተጋልጦ እንደነበረ ይታወሳል።
ይህ የባለፈው
ዓመት ሃገሪቱን የመታት ድርቅ በሃምሳ ዓመታት ካጋጠማት ሁሉ የከፋ ነበር። ይሁን እንጂ ድርቁ ለአንድም ሰው ህይወት መጥፋት ምክንያት
ሳይሆን፣ በድርቁ ሳቢያ ሰዎች ከመኖሪያ ቂያቸው ሳይፈናቀሉ፣ የትምህርት ሂደት ሳይስተጓጎል መከላከል ተችሏል። ይህን የባለፈውን
ዓመት አስከፊ ድርቅ በመከላከል ተግባር ላይ የኢፌደሪ መንግስት ከፍተኛውን ድርሻ መያዙ ይታወቃል። የባለፈው ዓመት ድርቅ ላይ ከውጭ
ከመጣ የእህል እርዳታ ቀረጢት መሳ ለመሳ የኢፌዴሪ መንግስት አርማ ያለባቸው
ቀረጢቶች ተሰልፈው እንደነበረ የታወሳል። ይህ በኢትዮጵያ የድርቅ ጉዳት ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ነው። መንግስት
ይህን ድርቅ ለመከላከል የ16 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ባጀት መድቦ እንደነበረም ይታወሳል።
ኢትዮጵያ
ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በተለያየ ግዜ ማለትም በ1985/86፣ በ1994፣ በ2003 ዓ/ም የተለያየ የተጽእኖ ደረጃ ባላቸው
ድርቆች ተመትታለች። እነዚህ ከ1983 ዓ/ም በኋላ ያጋጠሙ ድርቆች ከዚያ ቀደም ከነበሩት በተለይ የቅርርብ ግዜ ታሪካችን አካል
የሆኑት በ1965/66 እና 1976/77 ዓ/ም ካጋጠሙ ድርቆች በተለየ ወደችጋርነት ተለውጠው ለሰው ህይወት መጥፋትና መፈናቀል ምክንያት
አልሆኑም። የእነዚህን ድርቆች ተጽእኖ የመከላከሉ ስራ በተለይ የ1985/86 እና የ1994 ዓ/ም ድርቅን የመከላከል ስራ በውጭ
እርዳታ የተከናወነ ነበር። መንግስት የድርቁን ተጽእኖ ምንም ሳይሸሽግ በወቅቱ ይፋ አውጥቶ እርዳታ በመጠየቅ በሰው ህይወት ላይ
ጉዳት ሳይደርስ መከላከል ችሏል።
የ2008ቱና
የዘንድሮውን ተጽእኖ በመከላከል ረገድ ግን መንግስት የአንበሳውን ድርሻ ለመያዝ በቅቷል። ልክ እንደቀደሙት የድርቅ ተጽእኖዎች ሁሉ
ችግሩን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ቢያሳውቅም፣ እርዳታ እስኪደርስ እጁን አጣጥፎ አልጠበቀም። ከራሱ የመጠባባቂያ የእህል ክምችት
በማውጣት የአስቸኳይ ግዜ እርዳታ አቅርቧል።
ይህ በአጋጣሚ
የሆነ አይደለም። ሃገሪቱ ባለፉ 13 ዓመታት ያስመዘገበችው ተከታታይ ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት የፈጠረው አቅም ነው። የአምናው
ድርቅ ሲጀምር ሃገሪቱ 450 ሺህ ሜትሪክ ቶን የመጠባባቂያ የእህል ክምችት ነበራት። ይህ የእህል ክምችት በጎደለበት መጠን እየተተካ
ሳይጎድል እንዲቀጥል ማድረግ የተቻለበት ሁኔታም ነበር።
የዘንድሮው
ድርቅ ተጽእኖ ያረፈባቸው ዜጎች ቁጥር ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በግማሽ የቀነሰ ቢሆንም፣ ባህሪው ግን የተለየ ነው። ይህም
በቆላማ የአርብቶ አደር መኖሪያ አካባቢ የተከሰተ ከመሆኑ የመነጨ ነው። የአርብቶ አደሩ ኑሮ በእንስሳት ላይ ጥገኛ ነው። የምግብ
ፍጆታውን የሚያሟላው በየዕለቱ ከእንስሳ በሚያገኘው ወተት፣ ቅቤ፣ ትኩስ ደምና መሰል የእንስሳ ተዋጽኦ ነው። ድርቁ የእንሰሳት መኖ
ሲያጠፋው የዕለት የምግብ ፍጆታውን ማሟላት የማይችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። አነዚህ የእንሰሳ ተዋጽኦዎች በየእለቱ የሚገኙ በመሆኑ
የድርቁ ተጽእኖ ፋታ የሚሰጥ አይደለም። ይህ የዘንድሮው ድርቅ አንዱ ልዩ ባህሪ ነው።
ከዚህ
በተጨማሪ ለአርብቶ አደሩ የአስቸኳይ ግዜ የምግብ እርዳታ ከማቅረብ ጎን ለጎን የኑሮው መሰረት ለሆኑት እንስሳት መኖ ማቅረብ ያስፈልጋል።
የእንስሳት መኖ የማቅረብ ስራ ግን ለሰው የምግብ እርዳታ እንደማቀረብ ቀላል አይደለም። በቅድሚያ ለሁሉም የአርብቶ አደር እንስሳ
የሚበቃ መቂ መኖ በሃገሪቱ ማግኘት አዳጋች ነው። ለእንስሳ መኖ የሚሆን ሳር ከውጭ ሃገር ገዝቶ ማጋጓዝም የማይሆን ነገር ነው።
ከዚህ በተጨማሪ የእንስሳ መኖ በተለይ ሳር ቦታ ሰለሚዝ የማጓጋዙ ተግባር ውድ ነው። ለምሳሌ በቀን አራት ከብቶችን የሚመግብ አንደ
አራተኛ ሜትር ኩብ ሳር አንድ ኩንታል እህል ከሚይዘው ቦታ በላይ ቦታ ይይዛል። ይህን ያህል ይዘት ያለው መኖ ደግሞ ለአራት ከብቶች
የአንድ ቀን ፍጆታ ብቻ ነው የሚውለው። ከዚሀ አኳያ ሲታይ በአማካይ በአባወራ እስከሃምሳ ከበቶች ላሉት የአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ
ለሁሉም እንስሳት የሚበቃ መኖ በየእለቱ የድርቁ ተጽእኖ በሚኖርባቸው በወራት ምናልባት አመት ለሚሞላ ግዜ ማቅረብ የማይቻል ስራ ነው። መኖው እንደልብ ቢኖር፣ በቂ የማጓጓዝ አቅም
እንኳን ቢኖር እነኳን አንድን ከብት በዚህ አኳኋን ለወራት መመገብ ከከብቱ ዋጋ በላይ ወጪ ያስወጣል። ሰለዚህ አዋጭ አይደለም።
ያም ሆኑ
ግን ቢያንስ ለዘር የሚሆኑ ከብቶችን ለማትረፍ መኖ የማቅረብ ስራ እየተከናወነ ይገኛል። ይሁን እንጂ ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት
ለሁሉም እንስሳት መኖ ማቅረብ ሰለማይቻል እንስሳት የሚሞቱበት ሁኔታ ይታያል። በጉጂ ዞን ብቻ ከሃያአራት ሺህ በላይ ከብቶች መሞታቸውን
መረጃዎች ያመለክታሉ። በቦረና ያለው ሁኔታ ደግሞ ከጉጂ ዞንም የከፋ ነው። አርብቶ አደሩ በእንስሳ ሞት ምክንያት የሚደርስበትን
ጉዳት ለመቀነስ ከብቶቹን ለገበያ እንዲያቀርብ ጥረት እየተደረገ ነው። ከዚህ በተጨማሪ እንስሳቱን አርዶ ቋንጣውን ለመከላከያ ሰራዊትና
ለዩኒቨርሲቲዎች እንዲያቀርብ የማድረግ ውጥንም አለ። ይህም ቢሆን ግን በከብቶች ሞት ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት በጉልህ መቀነስ
የሚችል አይደለም።
በድርቁ ምክንያት የሚሞቱትን እንስሳትን ለማዳን የሚደረገው ጥረት
አስቸጋሪ ቢሆንም በገንዘብ የማይተመነው የክቡሩን የሰው ልጅ ህይወት በድርቁ ሳቢያ እንዳይጎዳ የመከላከሉ ስራ ግን በአስተማማኝ
ሁኔታ ውጤታማ ነው። ባለፈው ዓመት የተከሰተውን የከፋ የድርቅ ተጽእኖ
በመከላከል የተገኘው ወጤት ይህነኑ መድገም እንደሚቻል ያረጋግጣል። በዘንደሮው ድርቅ
ለለተጎዱ ዜጎች
የአስቸኳይ ገዜ እርዳታ የሚውል 141 ሺህ
ሜትሪክ
ቶን
እህል
ከመጠባበቂያ
ምግብ
ክምችት
በማውጣት
ወደ
አካባቢዎቹ
በመጓጋዝ ላይ
ይገኛል። በአንዳንድ አካባቢዎች በቂ እርዳታ እየደረሰ አይደለም የሚል ቅሬታ ቢሰማም አጠቃላይ የእርዳታ አሰጣጥ ሂደቱ ግን
በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ሊደርስ እንደማይችል የሚያረጋግጥ ነው። የመንግስት የመጠባበባቂያ የእህል ክምችተ አምና ከነበረበት
450 ሺህ ሜትሪክ ቶን ወደ 670 ሜትሪከ ቶን ማደጉም የእርዳታ አቅርቦት እጠረት እንደማይፈጠር ያረጋግጣል። በእርዳታ
አቅርቦት ላይ የሚሰማው ቅሬታ ከአቅርቦት እጥረት የመነጨ ሳይሆን አሰተዳደራዊ ነው።
በእርዳታ አቅርቦት ላይ በተለየ መዘግየት ላይ የሚሰማውን ቀሬታ ለማቃለል የአሰራር
ስርአት ተዘርግቷል። ይህም የእርዳታ ስርጭት ስርአቱን መቆጣጣር የሚያስችል አሰራር ነው። የብሄራዊ የአደጋ ስጋት
ኮሚሽን እንዳስታወቀው ለድርቁ ተጽእኖ ለተጋለጡ ዜጎች የሚቀርብ የአስቸኳይ ግዜ እርዳታ
ላይ
አልፎ
አልፎ
መዘግየቶች
ይስተዋላሉ።
ይህን ችግር ለመፈታት ድርቅ በተከሰተባቸው የአርብቶ
አደር
አካባቢዎች
የሚቀርበውን
እርዳታ
የሚቆጣጠር
ብሄራዊ
ኮማንድ
ፖስት
ሊቋቋም
ነው።
ኮማንድ ፖስቱ በፌደራልና በክልል መንግስታት
የሚሰጥ
እርዳታን
የሚከታተልና
በታችኛው
አመራር
ዘንድ
የሚስተዋሉ
የአፈጻጸም
ክፍተቶችን
በማስተካከል
እርዳታው
ለሚመለከተው
አካል
እንዲደርስ
የማድረጉን ስራ የማገዝ ተልዕኮ ያለው ነው። ብሄራዊ ኮማንድ
ፖስቱ
ከክልልና
በሚመለከታቸው
የፌዴራል
ሚኒስቴር
መስሪያ
ቤቶች
በመቀናጀት
የሚዋቀር ነው።
ይህ በተለይ ከአስቸኳይ ግዜ እርዳታ አቅርቦት መዘግየት ጋር ተያይዞ ለሚነሳው ቅሬታ መፍትሄ ማበጀት ያስችላል።
እንግዲህ ድርቅ በአመዛኙ የተፈጥሮክስተት በመሆኑ ከነአካቴው ማስቀረት
አይቻልም። እናም ኢትዮጵያ ለወደፊትም በድርቅ መመታቷ አይቀርም። የቅርብ ግዜ ሁኔታዎች እንደሚያመለክቱት በፊት በየአስር አመቱ
ይከሰት የነበረው ድርቅ አሁን ድግግሞሹ እየጨመረ መጥቷል። በመሆኑም ድርቅን እንደድንገተኛ ችግር ሲደርስ ብቻ በዘመቻ
ለመከላከል ከመራሯጥ ይልቅ፣ አይቀሬ መሆኑን አስቀድሞ ተገንዝቦ ተጽእኖ መፍጠር እንዳይችል የሚያደርጉ ስትራቴጂዎችን ማዘጋጀት
አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። እርግጥ የሃገሪቱን ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ ወደመሰኖ ልማት ለማሸጋጋር እየተደረገ
ያለው ጥረት፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ መሪነቱን ድርሻ ከግብርና ወደኢንደስትሪ ለማሸጋጋር የተነደፈው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን
እቅድ የድርቅን ተጽእኖ በዘላቂነት የመከላከል ስትራቴጂ ተደረጎ ሊወሰድ ይችላል።
ይሁን እንጂ የህዝቡን አኗኗር መሰረት ያደረጉ በአጭር ግዜ ውስጥ
ሊተገበሩ የሚችሉ ስራዎችንም መስራት ያስፈለግል። ለምሳሌ በአርበቶ አደሩና በቆላማ አካባቢዎች የድርቅን ተጽእኖ በዘላቂነት
ለመከላከል አርብቶ አደሩ ለእንስሳቱ ሳርና ውሃ ፍለጋ ከስፍራ ስፍራ የመጓጓዝ የኑሮ ዘይቤውን ቀይሮ አንድ ቦታ ረግቶ እንዲኖር
ማድረግ ያስፈልጋል። ይህም ውሃን ማእከል ያደረገ ስራ ነው። አርብቶ አደሩ አንድ ቦታ ረግቶ ሲኖር የግብርና ስራንም
ስለሚለማመድ የድርቅን ተጽእኖ የመቋቋም አቅሙ ይጠናከራል። እርግጥ በዚህ ረገድ ባለፉ አምስት ዓመታት የተጀመሩ ስራዎች
መኖራቸው ይታወቃል።
የፌደራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር አካባቢ ልማት ሚኒስቴር በቅርቡ
እንዳስታወቀው፣ የአርብቶ አደሩን የድርቅ ተጋላጭነት ለመቀነስና የምግብ ዋስትናውን በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሃገር አቀፍ ደረጃ የ5 ዓመት ፕሮግራም ተዘጋጅተቷል። በዚህ ፕሮግራም ከ200 ሚሊየን ዶላር በላይ ወጪ ተደርጎ ድርቅን ለመቋቋምና ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ስራሳዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ሶማሌ፣ የአፋር፣ የደቡብና የኦሮሚያ ክልል አርብቶ አደር ማህበረሰቦችን የእንስሳት ሃብት በማልማት ከገበያ ጋር በማስተሳሰር ተጠቃሚ ለማድረግ የውሃ፣ ትምህርትና የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ሽፋን የማሻሻል ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ሚኒስቴሩ አስታውቋል። በዚህ ረገድ እስካሁን አበረታች ውጤት መገኘቱንም አስታውቋል። በአሁኑ ጊዜ የመጠጥ ውሃ ሽፋን በኦሮሚያ አርብቶ አደር አካባቢ 68 በመቶ፣ በአፋር 63 በመቶ፣ በኢትዮጵያ ሱማሌ 62 በመቶ፣ በደቡብ 51 በመቶ መደረሱንም አመልክቷል። የእንስሳት ጤና ሽፋን በተመለከተም በኦሮሚያ አርብቶ አደር አካባቢ 81 በመቶ፣ በደቡብ አርብቶ አደር አካባቢ 72 በመቶ፣ በአፋር 67 በመቶ፣ በኢትዮጵያ ሱማሌ 63 በመቶ ደርሷል።
በአጠቃላይ የኢፌዴሪ መንግስት ድርቅ በሰው ህይወት ላይ ጉዳት
እንዳያደርስ የአስቸኳይ ግዜ የምግብና ተያያዥ እርዳታ በማቅረብ ተጽእኖውን የመቋቋም አቅሙ ባለፉ ዓመታት በተመዘገበው የኢኮኖሚ
እድገት ምክንያት አስተማማኝ ደረጃ ላይ ይገኛል። እስካሁን ያለው የሃገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታም የእድገቱን ቀጣይነት የሚያረጋግጥ
በመሆኑ ድርቅ ወደችጋርነት ተለውጦ የዜጎችን ህይወት የሚቀጥፍበት ሁኔታ ወደታሪክነት ተቀይሯል ማለት ይቻላል። ይሁን እንጂ
ድርቅ ሲከሰት ተጽእኖውን እንደድንገተኛ አደጋ በዘመቻ ለመከላከል የሚደረገውን ርብርብ አስቀረቶ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ የማደረግ
ስራ ብዙ ይቀረዋል። አጠቃላይ ኢኮኖሚውን ትራንስፎርም ከማድረግ ጎን ለጎን ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት በማውጣት የመስኖ ልማት
ድርሻን ማስፋት፣ በቆላማ የአርብቶ አደር አካባቢዎች ወሃን ማእከል ያደረጉ የልማት ስራዎችን ማከናወን ወዘተ በቅርቡ ጉልህ
ውጤት ማሳየት በሚችሉበት ሁኔታ መከናወን የሚገባቸው መሆኑ ሊታሰብበት ይገባል።
No comments:
Post a Comment