ወንድይራድ ኃብተየስ
የኢትዮጵያ
ህዝብ ቀንደኛ ጠላቱን በመለየቱ ድህነትን ለማጥፋት ቀና ደፋ እያለ ይገኛል። አስተማማኝ የኢኮኖሚ መሠረት ያላት አዲሲቷን
ኢትዮጵያ ለመገንባትም ቆርጦ ተነስቷል፡፡ ባለፉት ሁለት አሥርት
ዓመታት የተመዘገቡትን የልማት ውጤቶችና የተገኙ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋት ብሎም ሙሉዕ ለውጥ በማምጣት ሂደቱ ቀጣይነት
እንዲኖረው ሰፊ ጥረቶች እየተካሄዱ ናቸው። በተለይም መንግሥት ሁለተኛውን የአምስት ዓመታት ለመተግበር ለነደፈው የዕድገትና
ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ ህዝቡ ሰፊ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛል።
አገሪቱ
በከፍተኛ ደረጃ እየተገበረቻቸው ካለችው ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል የስኳር ልማት ፕሮጀክት ተጠቃሽ ነው። ትህም አገሪቱ በአምስት
ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ልትተገብራቸው ከያዘቻቸው ዐበይት የልማት ፕሮጄክቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ
አሥር ፋብሪካዎችን ለማቋቋም እቅድ ተይዞ እየተሰራ ይገኛል። አገሪቱ የስኳር ምርትን በከፍተኛ ደረጃ ለማምረት የሚያስችል አቅም
እንዳላት በጥናት ተረጋግጧል፡፡ ይህንን ሃብቷን በመጠቀም በቂ የስኳር ምርትን በማምረት የህዝቧን ፍላጎት ማሟላትና ከህዝቡ
ፍላጎት የተረፈውን ለውጪ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪን ማስገኘት የሚያስችላት ስትራቴጂ ነድፋ በመሥራት ላይ
ትገኛለች፡፡
ከነዚህም
አንዱ የሆነው የወልቃይት ስኳር ልማት ፕሮጀክት ሥራው እየተካሄደ ይገኛል። ፕሮጀክቱ በአካባቢው ሊያደርስ ስለሚችለው ጉዳትና ስለሚያስገኘው
ጠቀሜታ በተገቢው ተጠንቷል። ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋርም በፕሮጀክቱ አስፈላጊነትና በአፈጻፀሙ ሂደት ዙሪያ በቂ ውይይት
ተካሂዷል። ህዝቡም ስለ ስኳር ልማቱ ጠቀሜታ በበቂ ደረጃ ግንዛቤ
ተይዟል።
ልማቱ
ሰፊ የሥራ እድል ከመፍጠሩም ባሻገር በቂ መሠረተ ልማት በአካባቢው እንዲዘረጋ ያግዛል። የአካባቢው ኅብረተሰብ የ24 ሰዓታት
የመብራት አገልግሎትንም ያገኛል። የስልክ አገልግሎት ሽፋንም በዚያው መጠን ያድጋል። ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማትም
ይስፋፋሉ። አርሶ አደሩ የመስኖ ልማት ተጠቃሚ ይሆናል – በዚህም ምርታማነቱ ይጨምራል።
ከዚሁ
ጎን ለጎን ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ መንገድ ስለሚገነባና የህዝብ ማመላለሻ አገልግሎት ስለሚስፋፋ አርሶ አደሩ ምርቱን በቀላሉ
ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ይሆናል። አካባቢውም ከገጠርነት ወደ ከተማነት ይቀየራል። ይህ ለወልቃይት ሆነ ለሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ግልጽ ነው። ከኅብረተሰቡ ጋር ከተደረጉ
ተከታታይ ውይይቶች ለመገንዘብ የተቻለውም ይኼው ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞ የአካባቢው ህዝብ ልማቱን ለማፋጠን ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ
ይገኛል።
ሐቁ
ይህ ሆኖ ሳለ የከሰሩ ፖለቲከኞች እና የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎን ነን ባዮች እንደተለመደው ልማቱ ህዝብን አይጠቅምም የሚል ጭፍን ዘመቻ ጀምረዋል። ምንጊዜም የኢትዮጵያ ልማት፣ ሠላምና መረጋጋት
የማይፈልጉ እነዚህ አካላት መንግሥት ለስኳር ልማት ፕሮጀክት ሲል
የዋልድባን ገዳም አፈረሰው እያሉ ሲወተውቱ ነበር – ያኔ። መንግሥት የአካባቢውን ህዝብ ሳያማክር ነዋሪውን በግዳጅ
ከቀየው እያስነሳ ነው በማለትም ሲወነጅሉ ሰንብተዋል – ያኔ።
የገዳሙ መነኮሳትም ታሰሩ እያሉ ህዝበ ክርስቲያኑን ለማደናገርና ከመንግሥት ጋር ለማጋጨት የተንቀሳቀሱበትም ጊዜ ነበር – ያኔ።
የዋልድባ
ገዳም የኢትዮጵያ ህዝብ ገዳም ነው። የተከበረና የተቀደሰ የእምነት ሥፍራ ነው። በቦታው የሚያገለግሉ መነኮሳትም የተከበሩና
የበቁ የኃይማኖት አባቶች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የተረጋገጠው የኃይማኖት ነጻነት ተጠቃሚ ከሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ አካል
የሆነው የወልቃይት አካባቢ ህዝብም የኃይማኖት ነጻነቱ የተጠበቀ ነው። በመሆኑም ገዳሙን የሚነካበት አካል የለም። የስኳር ልማቱ
ገዳሙን አይነካም። ገዳሙ የበለጠ ተከልሎና ተከብሮ ይኖራል። እሰካሁን በነበረበት ሁኔታ ኃይማኖታዊ ተልዕኮውን ያከናውናል።
የወልቃይት
አካባቢ ህዝብም ሆነ የዋልድባ ገዳም ማኅበረሰብ የስኳር ልማት ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ህዝብ ያለውን ጠቀሜታ በመረዳት ከመንግሥት
ጋር ተባብረው ለፍጻሜው የበኩላቸውን እገዛ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ከቀበሌያቸው ለሚነሱ አንድ ሺህ ለሚጠጉ ነዋሪዎች ለመኖሪያ
በመረጡት ቦታ ተለዋጭ መንደሮች እየተገነቡ ነው። በእነዚህ መንደሮች አስፈላጊው መሠረተ ልማት እየተሟላ ይገኛል። በመስኖ
የሚለማ የእርሻ ቦታም ይሰጣቸዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የዋልድባ ገዳም መነኮሣት ለእርሻ ይጠቀሙበት ከነበረው ቦታ ወደ ፕሮጀክቱ
ለሚገባው የተወሰነ ቦታም ተለዋጭ በመስኖ የሚለማ የእርሻ ቦታ ይሰጣል። ስለዚህ ህዝቡን ለመጥቀም የሚገነባው የስኳር ልማት
ህዝቡን ለመጉዳት እንደተደረገ በማስመሰል ህቡዕ የፖለቲካ አጀንዳን ማስፈፀሚያ ሊሆን አይገባም።
የከሰሩ
ፖለቲከኞች መንገድ ላይ እንደመሸባቸው አላወቁም እንጂ ህዝቡ የሚጠቅመውንና የሚጎዳውን ለይቶ አውቋል። ልማቱን ለማደናቀፍ
የሚንቀሳቀስ ማንኛውንም አካል የሚቀበልበት ሁኔታ አክትሟል። በኃይማኖት
ሽፋን የወልቃይትን ህዝብ ለማወናበድ ከንቱ ልፋት መሆኑ ያልገባቸው ፖለቲከኞች ማወናበዱን ቢቀጥሉበትም ጆሮውን ነፍጓቸዋል –
አይሰማቸውም።
እነዚህ
ወገኖች የኢትዮጵያ ሠላም፣ ዴሞክራሲና ልማትን ለማደናቀፍ የማይሞከር ነገር መኖር የለበትም ከሚል እምነት በመነሳት ሲሆን ሌላው
ደግሞ በሌሎች አገራት የሚኖሩ የእምነቱ ተከታዮች ላይ ቅሬታን
ለማጫር የሚያደርጉት ጥረት ነው። የኢትዮጵያ ዕድገት እንደ እግር እሣት የሚያንገበግባቸው አካላት ተስፋ ሳይቆርጡ ሥልታቸውን
እየቀያየሩ ሠላም የማደፍረስ ተግባራቸውን አሁንም ቀጥለውበታል። አሁን ሰሞን በቤንሻንጉል ጉሙዝ በህዳሴው ግድብ ላይ ጥቃት
የመፈፀም ተልዕኮ ይዘው የከሸፈባቸው ፀረ ልማት ኃይሎች ለዚህ ጥሩ ማሣያዎች ናቸው።
የከሰሩ
ፖለቲከኞች ኃይማኖትን ለድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያ በመሣሪያነት
መጠቀምን ለምን መረጡ? ተግባራቸው በተደጋጋሚ እየተጋለጠ ለምን መቋጫ አላገኘም? አማኞች እምነቱ ከሚያዘው ውጭ የተለያየ እንቅስቃሴ ሲያጋጥማቸው ለምን
አፋጣኝ ርምጃ አይወስዱም? የሚሉትንና ተዛማጅነት ያላቸው ሌሎች ጥያቄዎችን መመለስ ተገቢነት ይኖረዋል።
እነዚህ
የከሰሩ ፖለቲከኞች ኃይማኖትን በመሣሪያነት መጠቀም የፈለጉበት ምክንያት የኢትዮጵያ ህዝብ ለኃይማኖቱ ቀናኢና ለእምነቱ ሟች
መሆኑን ስለሚያውቁ ነው። የእስልምናም ሆነ የክርስትና ኃይማኖት አማኞች ለለኃይማኖታቸው ህወታቸውን አሳልፈው ለመስጠት
እንደማያመነቱ በመገንዘብ ነው። ከዚህ አንጻር ኃይማኖታዊ የመሰሉ ጥያቄዎችን በማንሳት አማኞች ውስጥ ሰርጎ በመግባት በመርዝ
የተለወሰ ማር ለማጉረስ ጥረት ማድረግ ያዋጣል የሚል እምነት በማሳደራቸው ነበር። ሌላው ደግሞ በኃይማኖት ምክንያት የሚነሱ
ግጭቶች መቋጫ አይኖራቸውም የሚል እምነት በማሳደራቸውና ህዝቡን መቋጫ ወደሌለው ግጭትና ሁከት ለማስገባት በማቀድ ነው። ለዚህም ነው አንድ ጊዜ በእስልምና ኃይማኖት በሌላ ጊዜ ደግሞ በክርስትና ኃይማኖት
ሽፋን እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት።
ሁኔታው
በተደጋጋሚ እየተነሳ ያለበት ሁኔታ ቢኖርም እነዚህ ፖለቲከኞች የሚያነሷቸው ኃይማኖት አዘል ጥያቄዎችና የሚያደርጓቸው ኃይማኖት
ለበስ እንቅስቃሴዎች በጥንቃቄ የተቃኙ በመሆናቸው መቋጫ አልተገኘላቸውም። ትክክለኛ የኃይማኖት ጉዳይ መስለው እንዲታዩ በየወቅቱ
ከሚከሰቱ ሁነቶች ጋር እያቆራኙ ከማቅረባቸው በላይ በእያንዳንዱ እምነት ውስጥ ለተሰገሰጉ አባሎቻቸው ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ
አንዳንድ ፈሪሃ ፈጣሪ የራቃቸውን አማኞች በገንዘብ ኃይል በማታለል የእነሱን ፍላጎት እንዲያራምዱ ስለሚያደርጉ
ነው።
ምንም
እንኳን በተለያየ ጊዜ ያነሷቸው ጥያቄዎች ኃይማኖታዊ ተልዕኮ
እንደሌላቸው እርቃናቸው የወጡበት ሁኔታ ቢኖርም ከውጭ በሚያገኙት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ በመታገዝ የተለያዩ እቅዶችን በመንደፍና
ሥልታቸውን በመቀያየር አፍራሽ ተልዕኳቸውን ለማሳካት ጥረት
ስለሚያደርጉ መቋጫ የለሽ ሆኗል።
በየወቅቱ ከሚከሰቱ ሁነቶች ጋር ነገሮችን በማዛመድ የተለያየ
ኃይማኖት ለበስ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ አማኙ ኅብረተሰብ ከወቅቱ ሁኔታ ጋር የተዛመደውን ነገር እውነት መስሎ
ስለሚታየው እውነታው እስኪወጣ ድረስ በቀናኢነት ስለሚቀበል ነው።
ህዝበ ሙስሊሙም ሆነ ህዝበ ክርስቲያኑ ማንኛውም ነገር ከፈጣሪ መሆኑን ያምናል።
ክፉ የሚሰራ ዋጋውን ከፈጣሪ ያገኛል የሚል እምነት ስላለው
ይታገሳል። የሚነሳው ነገር ኃይማኖታዊ ሽፋን የለበሰ ፖለቲካ በመሆኑ ግን አንድ ጊዜ ተነስቶ የሚቆም አይሆንም። በተደጋገመ
ቁጥር ኃይማኖታዊ ሥርዓቱንና አስተምህሮ እየሳተ ወደዋና ዓላማው መግባት ይጀምራል። ውሎ ሲያድርም ኃይማኖታዊ ተልዕኮ
እንደሌለው ፈጦ ይወጣል። በተለያየ ጊዜ በኃይማኖት ሽፋን
የተደረጉ ሙከራዎች ውጤት የሚያሳየውም ከዚህ የተለየ አይደለም።
የክርስትናም ሆነ የእስልምና ኃይማኖቶች አስተምህሮ
እንደሚያስቀምጠው አንድ ሰው ለሁለት አለቆች ወይም ጌቶች መገዛት አይቻልም። ገንዘብንና ፈጣሪን አጣምሮ መውደድ አይቻልም።
ለገንዘብ ያደረ አምላክን ትቷል፤ ገንዘብን የናቀ አምላክን ወዷል። አንዳንድ አማኞች ለገንዘብ በመገዛት ሌላውን አማኝ ለማሳመን ጥረት ስለሚያደርጉ የኃይማኖቱ ተከታዮች የጉዳዩን ውስጠ
ምስጢር ለማወቅ ጊዜ ይወስድባቸዋል። ለጊዘውም ቢሆን በፈጣሪ ስም የሚመጣ በመሆኑ ይቀበሉታል።
ተስፋ የቆረጡ ፖለቲከኞች ኃይማኖትን በሁለት መልክ
ይፈልጉታል። አንደኛው በኃጥያትና በክፋት የተጨማለቀ ህሊናቸውን ትንሽ ለማሳረፍ ያስችለናል ከሚል እምነት ነው፤
ሌላው ደግሞ በዚያ ለኃይማኖቱ ቀናኢ የሆነ ህዝብ በሚሰበሰብበት የተቀደሰ ሥፍራ ኃይማኖት ለበስ ህቡዕ አጀንዳቸውን ተግባራዊ
ለማድረግ ያግዘናል ብለው ስለሚያምኑ ነው።
ዓላማው የአገሪቱን ሠላም በማደፍረስ በግርግር ለመጠቀም
መሞከር ነው። የከሰሩ ፖለቲከኞች ከኃይማኖትና ከጽንፈኝነት የሚቆራኙትም ከዚህ አንጻር ነው። ተስፋ የቆረጠ አጥፍቶ መጥፋትን
ይመርጣል። ሌላውንም ይዞ መሞትን ይመኛል። የሚታየው ህይወትም ሆነ ብሩህ ነገር የለም። እኛ ግን ሥራ ላይ ነን – ጊዜ
የለንም! ሁሉም ነገር ጨለማ ነው። ጨለማውን ግን ብቻውን ለመጋፈጥ አቅምና ሥነ ልቦናዊ ጥንካሬ አይኖረውም። ይህ በውስጥ
ከሰነቀው ህቡዕ አጀንዳ ጋር ሲጣመር የጥፋት መንገድን መከተል ዓይነተኛ ስትራቴጂ አድርጎ ይጠቀማል። "እኔ ከሞትኩ
ሰርዶ አይብቀል!" አይደል ተረቱ።
No comments:
Post a Comment