ቶሎሳ ኡርጌሳ
ኢትዮጵያ
ከ28ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ድልን ተቀዳጅታለች። ሀገራችን በተለይም ከግብፁ መሪ አበዱልፈታህ
አልሲሲና ከደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማርዲያት እንዲሁም ከሌሎች አባል ሀገራት መሪዎች ጋር ያካሄደችው የሁለትዩሽ ግንኙት
ውጤታማ ነበር። ከግብፁ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ጋር የተደረገው ባለ አምስት ነጥብ ስምምነት፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ
ግንኙነት በማጠናከር መተማመን መፍጠርን፣ የአካባቢውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የፀጥታ ትብብር ማጠናከርን ያካተተ ነው።
ከዚህ
በተጨማሪም የሁለቱን ሀገሮች ወንድማማችነት የሚጎዳ ማንኛውንም ዓይነት ድርጊት መቆጣጠርንና መገደብን፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን
በተመለከተ የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ የጋራ ቴክኒክ ኮሚቴ አማካይነት በትብብር የመሥራት አስፈላጊነትን፣ በመሪዎችና በተቋማት
ደረጃ መረጃ በመለዋወጥ ተከታታይ ምክክሮች ማድረግን፣ የህዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን የበለጠ ማሳደግን፣ የሀገራቱ የመገናኛ
ብዙሃን የበኩላቸውን ሚና የማድረግ ስምምነቶችንም በውስጡ ያካተተ ነው። እነዚህ ስምምነቶች ኢትዮጵያ መቼም ቢሆን በጋራ ተጠቃሚነት
ዙሪያ ከየትኛውም ሀገር ጋር አብሮ የመስራት መርህዋን ያሳየችበት ነው ማለት ይቻላል።
በሌላ
በኩልም ሀገራችን ከፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጋርም በሁለትዮሽ ጥቅሞች ላይ ያተኮረው ውይይትና ስምምነት የሀገራችንን መቼም የማይለወጥ
የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ ያንፀባረቁ ነበር። ከሌሎች መሪዎችም ጋር እንዲሁ። በተለይም በቅርቡ የደቡብ ሱዳን መንግስት ከግብፅ አቻው
ጋር ካይሮ ላይ ያካሄደውን ስምምነት ተከትሎ፤ በአንዳንድ ማህበራዊ የተናፈሰው አሉባልታ መሰረተ ቢስ መሆኑን የሁለቱ ሀገራት መሪዎች
ከመግለፃቸውም በላይ፤ ሀገራቱ በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ በመሠረተ ልማት፣ በሰላምና በፀጥታ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን
አስታውቀዋል—ማናቸውም መሰረተ ቢስ ወሬዎች የሁለቱን ሀገራት ጠንካራ ግንኙነት ሊያሻክረው እንደማይችል በማብራራት ጭምር።
ይህ
ስምምነት ኢትዮጵያ ከየትኛውም ጎረቤት ሀገር ጋር በጋራ ተጠቃሚነትና ሀገሪቱን በመደገፍ የምትሰራ መሆኑን ያረጋገጠችበት ክስተት
ነው። ይህ ዕውነታ ሀገራችን ችግሯን ከውጭ ወደ ውስጥ የምትመለከት ሳትሆን፣ ከውስጥ ወደ ውጭ በመመልከት ዋነኛውን ውስጣዊ ችግሯን
በመፍታት፤ ከጎረቤቶቿና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዩች ዙሪያ ከምትገናኛቸው ሀገራት ጋር ተባብር ለመስራት ያላትን ቀናዒ ፍላጎት
የሚያረጋግጥ ነው። ለዚህ ደግሞ ሀገራችን የምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስድ ይመስለኛል።
እርግጥ
ማንኛውም ፖሊሲ ሲቀረፅ የሀገሪቱን አንገብጋቢና ተጨባጭ ሁኔታን መነሻ ያደርጋል። ከዚህ አኳያ ደርግ እንደ ወደቀ የነበረው ፈታኝ
ሁኔታ የኢኮኖሚ ድቀት እንዲሁም የሰላም እና የዴሞክራሲ እጦት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ በወቅቱ አምባገነኑን ስርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዳይመለስ ግብዓተ መሬቱን የፈፀሙት የኢትዮጵያ
ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የነበረባቸው ችግር እንደ ሀገር ለመቆም ለህልውናቸው ወሳኝ የሆኑትን ውስጣዊ ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲውም ይህንን መሰረታዊ
እውነት ባገናዘበ መልኩ፤ ድህነትን የሚያስወግድ፣ የኢኮኖሚ ልማትን፣ ብልፅግናን፣ ዴሞክራሲን ብሎም ሰላምን በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲነደፍ
መደረጉ ለዚሁ ነው፡፡
እንደሚታወቀው
ደርግ ሲከተለው የነበረው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከሥርዓቱ አምባገነናዊ ፖሊሲ በመነጨ ሁሉንም ጎረቤት ሀገሮች “በይወሩኛል” ጥርጣሬ
ዓይን የሚመለከትና በጠብ የመፈላለግ ስሜት የታጀለ ነበር፡፡ በውስጥ ያለውን ችግር ከመመልከት ይልቅ ጣቱን ወደ ውጭ በመቀሰር የሚታወቀው
የደርግ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ፤ ሀገሪቱን ለከፋ የኢኮኖሚ ድቀት የዳረገና መቋጫ ወደሌለው የእርስ በርስ ጦርነት ያስገባ ነበር፡፡
አናም ይህ በጠብ የመፈላለግ የደርግ ፖሊሲ ሀገሪቱ ከአስተማማኝ ሰላም ማግኘት የነበረባትን ጥቅም በማስቀረቱም ባሻገር፤ ለአስከፊ
ማህበራዊ ቀውስና ድህነት ዳርጓታል።
ሆኖም
ኢህአዴግ ሀገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ሀገራችን የምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ተቀይሮ ማጠንጠኛው በጋራ ጥቅም ላይ በተመረኮዘ
ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ላይ እንዲያተኩር ተደርጓል። በዚህም ገና ከጅምሩ በሽግግር መንግስቱ ወቅት መንግስት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ
ጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠት ባሻገር፣ ለአፍሪካ ቀንድና ለአካባቢው ዘላቂ ሰላም መስፈን የሚያስችሉ አካሄዶችን ተከትሏል፡፡ ይህም በሀገሪቱ
የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣት ያስቻለ ከመሆኑም ባሻገር፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን
የተወሰደ ርምጃ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ተግባሩም ለምስራቅ አፍሪካ ሰላም ወዳድ ህዝቦች መልካምና ጠንካራ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ የከፈተ
ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
የሽግግር
መንግሥቱን ቻርተር ተመርኩዞ የተዘጋጀውና በአሁኑ ወትት ብሔራዊ ጥቅማችንን በማስጠበቅ ብሎም ሀገራዊ ህልውናችንን እያረጋገጠ የሚገኘው
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ፤ የውስጥ ችግሮቻችንን በመቅረፍ ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚኖረንን ግንኙነት በጋራ
ጥቅም እና ሰላም ላይ እንዲመሰረት አድርጓል፡፡ ሰሞኑን ከአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች ጋር የተደረገው የሁለትዮሽ ግንኙነትም
መሰረቱ ይኸው ሀገራችን የምትመራበት የውጭ ገንኙነት ፖሊሲ ነው፡፡
በፖሊሲው
ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ከጎረቤት ሀገሮች ጋር የሚከተለው መንገድ
በግልጽ ተብራርቷል፡፡ ከቀጣናው ሀገራት ጋር የሚኖረን ግንኙነት በመከባበር ላይ የተመሰረተ እንዲሁም ሰጥቶ በመቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ
እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ዓለማችን በፈጣን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የእሽክርክሪት ለውጥ ውስጥ የምትገኝ በመሆኗ፤ ቋሚ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ
ግንኙነትን ማለም የማይታሰብ ጉዳይ ነው፡፡ ይሁንና መንግስት
ባለፉት 15 ዓመታት ውስጥ ያከናወናቸውና ተሰሚነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጎለብት ያደረገው የዲፕሎማሲ ድል፤ ጎሬቤቶቻችን ከልማታችን
ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው መሆኑን በእርግጠኝነት መናገር የሚቻል ይመስለኛል፡፡
እንደሚታወቀው
ማንኛውም ፖሊሲ ዝርዝር አፈጻጸሞችን አያካትትም−ሁኔታዎች ተለዋዋጭ
ናቸውና፡፡ ይሁንና ወሳኝ የሚባሉ አንኳር ጉዳዮችን ይዘረዝራል፡፡ ከዚህ በመነሳት የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ
ከጎረቤት ሀገሮች ጋር የሚኖረንን ግንኙነት የገለፀው ይህንኑ መርህ ተከትሎ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የቀጣናው ሀገራት ለሀገራችን ካላቸው
ፖለቲካል ኢኮኖሚ ጠቀሜታ አኳያ እየተቃኙ ግንኙነቱ እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡ ይህ የግንኙነት ደርዝም ትናንት የነበሩትንም ይሁን በአዲስ
መልክ እንደ ሀገር የተቋቋሙ ሀገራትን የሚመለከት ነው፡፡
ይህን
ዕውነታ ከሶማሊያና ከቀሪዎቹ የቀንዱ ሀገራት አኳያ መመልከት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ በሰነዱ ላይ በግልጽ እንደተመለከተው፤ ሀገራችን
በሶማሊያ ላይ የምትከተለው ፖሊሲ በዋናነት የሀገሪቱን ሠላምና ዴሞክራሲ
እንዲሰፍን በሚያስችል መልኩ ገቢራዊ የሚሆን ነው፡፡ ይህም በዚያች ሀገር ያለው አለመረጋጋት ቢቀጥል ወደ ሀገራችን ወይም ወደ አካባቢው አሊያም በሶማሊያ ህዝብ ላይ የሚያስከትለውን
ጉዳት ለመቀነስ ታስቦ የተዘጋጀ መርህ መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡
የአንድ
ሀገር ፖሊሲ በሌላኛው ሀገር ውስጥ ለዕድገትና ለመረጋጋት እጅግ ቁልፍ የሚባሉትን ሠላምና ዴሞክራሲን እንዲሰፍን እንጥራለን ከማለት
ውጭ፤ እያንዳንዱን አፈጻጸም ደረጃ በደረጃ ሊዘረዝር አይችልም፡፡ ከዚህ አኳያ በሶማሊያም ይሁን በሌሎች የቀንዱ ሀገራት ላይ ኢትዮጵያ
የምትከተለውን ፖሊሲ በተገቢው ሁኔታ ገልጿል፡፡ ይህም ሀገራችን ከአፍሪካ
ቀንድ አኳያ የምትከተለውን የዲፕሎማሲ መስመር የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡
በአጠቃላይ
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይና የደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂን በምርኩዝነት ይዞ ላለፉት 15 ዓመታት በሰከነና በሳል አመራር እየታገዘ ዛሬ
ላይ የደረሰው የኢትዮጵያ መንግስት የአንጸባራቂ ዲፕሎማሲያዊ ድሎች ባለቤት ነው፡፡ እነዚህ ድሎች ሀገራችንን በብሔራዊ ጥቅም ያረጋገጡ፣
እኩልነትንና የጋራ ተጠቃሚነትን ያጎለበቱ እንዲሁም ቀጣናዊ ትብብርንና ሰላምን የፈጠሩ በመሆናቸው ነገም ሆነ ከነገ ወዲያ ተጠናክረው
የሚቀጥሉ ናቸው፡፡ ሰሞነኛው ሀገራችን ከግብፅ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከሌሎች የቀጣናው ሀገራት ጋር ያደረገችው ስምምነቶች ብሎም ከሌሎች
የአህጉሪቱና ሌሎች ሀገሮች ጋር ጋር ያደረገችው የሁለትዮሽ ውጤታማ ግንኙነቶች የዚሁ ፖሊሲ ነፀብራቅ መሆናቸው ሊዘነጋ አይገባም፡፡
No comments:
Post a Comment