ሰለሞን ሽፈራው
ለራሳቸው በምዕራቡ ዓለም ሀገራት የተደላደለ የቅንጦት ህይወት እየኖሩ በሚያዛምቱት የጥላቻ
ፖለቲካ ሀገራችንን ወደለየለት የብተና አደጋ የሚወስድ ሁከትና ግርግር ለመቀስቀስ ያለመ ሴራ በማውጠንጠን ስለተጠመዱት አክራሪ ዲያስፖራ
ተቃዋሚዎች ሲወሳ ቀድመው ትዝ የሚሉን ግለሰቦች አሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ቀዳሚውን ስፍራ ሊይዙ ከሚችሉ ፅንፈኛ የዲያስፖራ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች
መካከል አንዱና ምናልባትም ዋነኛው ጁሐር መሐመድ ስለመሆኑም ደግሞ ደፍሮ መናገር ይቻላል፡፡
ጁሐር መሐመድ የሚባል አደገኛ ግለሰብ፤ እርሱ በሀገረ-አሜሪካ ተቀምጦ የራሱን ሰላማዊ ህይወት
እየኖረ እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የኦሮሞ ወጣቶችን ልብ አሸፍቶ
ለሀገር አውዳሚ የአመፃ ተግባር ለማነሳሳት ያለመ ዕኩይ አስተሳሰቡን በስፋትና በንቃት የማራገብ ዘመቻ ላይ ከተጠመደ
ዓመታትን አስቆጥሯልና ነው፡፡ ከዚህ የተነሳም “ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ” ወይም ደግሞ በእንግሊዝኛው ምፃረ ቃል O.M.N የተሰኘ
የራሱን የመረጃ መረብ እስከ መዘርጋትም ደርሷል፡፡ እናም ጁሐር መሐመድ ተብዬው የማህበራዊ ሚዲያ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ከሰሞኑ ኦሮሚያ
ክልልን ለማተራመስ ስለሚሞክሩበት የአመፅ ተግባራቸው ጉዳይ ለአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ ጣቢያ የአማርኛው ክፍለ ጊዜ በሰጠው ወቅታዊ ቃለምልልስ
ላይ ሲናገር የተደመጠውን አሸባሪ መልዕክት የሰማ ማንኛውም ጤናማ አዕምሮ ያለው ሰብዓዊ ፍጡር ክፉኛ ሊደነግጥ የሚችል ይመስለኛል፡፡
ግለሰቡ ጥቅምት 07 ቀን 2009 ዓ.ም ለ “ቢ.ኦ.ኤ” በሰጠው ቃለ መጠይቅ፤ የዘንድሮውን
የኢሬቻ በዓል ተከትሎ የተከሰተው የሁከትና ግርግር እንቅስቃሴ ላይ የተሰማሩት እርሱው ጉዳይ አስፈፃሚ ቡድኖች፤ በተለይም ሰበታ
ከተማን ጨምሮ በሌሎች የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው፤ በርካታ የህዝብ ሀብት ንብረት ያወደሙበትን ዕኩይ ድርጊት
ሁሉ “ተገቢ እርምጃ ነው” ሲል የገለፀበት አግባብ ለሰሚው የሚያስደነግጥ ሆኖ አግኝቼዋለሁና ነው፡፡ ስለዚህም ጁሐር ተብየው ግለሰብ
በሰሞነኛው አሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ቃለምልልሱ ላይ ሲናገር የሰማሁትን እጅግ በጣም አስነዋሪና መወገዝ ያለበት ፕሮፖጋንዳ መነሻ አድርጌ፤
ይልቁንም እንደርሱ ዓይነቶቹ የአራት ኪሎውን መንበረ ስልጣን በአቋራጭ መቆናጠጥ ይቻላል ብለው ያመኑ ዲያስፖራ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች
ምን ያህል ቀልባቸውን እስኪስቱ በፅንፈኛ አስተሳሰባቸው እንደሰከሩ ለማመላከት የሚረዳ የግል አስተያየቴን እስነዝር ዘንድ ፈልጌያለሁ፡፡
እንግዲያውስ የመጣጥፌን ርዕስ “እነ ስልጣን አረቄው” እንድለው ስላደረገኝ የጁሐር መሐመድ
ሰሞነኛ ንግግር ያፈጠጠ እና ያገጠጠ ነውረኝት የተንፀባረቀበት መሆን የሚያስታውሱ ነጥችን ቃል በቃል ለመጥቀስ እሞክራለሁ፡፡ ስለዚህም
ግለሰቡ “አገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ትልልቅ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ከአገልግሎት ውጭ ለማድረግ ሲባል የሚወስደው ፋብሪካዎችንና ሌሎች
መሰል ተቋማትን የማቃጠል እርምጃ ስርአቱን የማዳከሚያ ስትራቴጂ ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ተገቢነቱ ታምኖበት የተጀመረ እርምጃ የተቃውሞ
እንቅስቃሴያችን ዋነኛ ስትራቴጂ ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል እንጂ ህዝቡን እንደሚጎዳ ተግባር መታሰብ የለበትም” ሲል በአስነዋሪው
ሀገር አውዳሚ ድርጊታቸው ሊኩራራበት ሲቃጣው መደመጡን ልብ በሉልኝ፡፡
እኔን እንደ አንድ ሰላማዊ ዜጋ እንድደነግጥም ጭምር ያደረገኝ የግለሰቡ ምላሽ ግን፤ በተለይም
“ስለዚህ ትልልቅ የመንግስት ተቋማትን ጨምሮ ፋብሪካዎችንና ሌሎች የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ውጤቶችን በተጠና ጥቃት እያወደምን
ስርዓቱ እንዲዳከም የማድረጉን ስትራቴጂ ይበልጥ አጠናክረን እንቀጥልበታለን ብዬ አምናለሁ፡፡ እኔ ከዚህ አኳያ በመጫወት ላይ ያለሁትን
አውንታዊ ሚናም አሁን ያለው ስርዓት ወድቆ የሽግግር መንግስት እስኪቋቋም ድረስ እገፋበታለሁ፡፡ እንጂ ትግላችንን ሊያስቆሙን ስለፈለጉ
እናቆማለን ብሎ ማሰብ የማይቻል ጉዳይ ነው…!” ወዘተ ሲል እቺን ሀገር እንደ ሀገር ለማተራመስ ቆርጠው ስለመነሳታቸው በእርግጠኝነት
ስሜት የገለፀበት ዛቻው ነበር፡፡ ታዲያ ይህ እንደ ጁሐር መሐመድ ያሉት፤ ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ወዲያ ማዶ በሚገኘው የሰለጠነ ክፍለ
ዓለም የሚኖሩ የጠባብ ብሔርተኝትና የትምህክት አስተሳሰብን አቀንቃኝ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ለመላው የዚህች አገር ህዝቦች እየደገሱልን
ያሉት የትፋት አደጋ፤ የሚቋምጡለት ስልጣን ልክ እንደ የሀበሻው አረቄና (ካቲካላ) ሳያሰክራቸው አልቀረም ብዬ እንድጠራጠር ቢያደርገኝ
ምኑ ይገርማል!;
እስቲ ለማንኛውም ለዚህ የህሊና ፍርድን ለሚሻ ጥያቄዬ ተገቢነት እንደማንፀሪያ ሊታዩ የሚችሉ
አንዳንድ አሳማኝ ታሪካዊ ምክንያቶችን ለማንሳት ይረዳኝ ዘንድ፤ ኢህአዴግ መራሹ የኢትዮጵያ ህዝቦች ፀረ ጭቆና ትግል ደርግን አሸንፎ
ወደ ስልጣን ስለመጣበት እጅግ የተራዘመና በዚያው ልክም ደም ያፋሰሰ ፈታኝ ሂደት የማውቀውን ያህል ላውሳ፡፡ መቸስ አሁን ላይ እነ
አቶ ጁሐር መሐመድ ከምዕራቡ ዓለም ሀገራት የስደት ኑሯቸው በሚያናፍሱት የ “ፌስቡክ” ዘመን ውዥንብር እንደ ኢያሪኮ ሊያፈራርሱት
ስለመቃረባቸው የሚናገሩለትን ፌዴራላዊ ስርዓት ለመመስረት ያስቻለንን የዚህች አገር ፖለቲካ አጠቃላይ ገፅታ የፈጠረው፤ ኢህአዴግ
መራሹ የኢትዮጵያ ህዝቦች ፀረ ብሔራዊና መደባዊ ጭቆና የትጥቅ ትግል፤ በተራዘመ የዕርስበርስ ጦርነት ሂደት የደርግ ኢ.ሠ.ፓን እንደተራራ
የገዘፈ ወታደራዊ አገዛዝ ስላስወገደልን እንደነነበር አይዘነጋም፡፡
“በግዙፍነቱ ከመላው አፍሪካ አቻ አይገኝለትም” እየተባለ ይነገርለት የነበረው የደርግ ኢ.ሠ.ፓ
ወታደራዊ አምባገነን ስርዓት እስከ አፍንጫው አስታጥቆ የመብት ጥያቄ ባነሱ የዚች አገር ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ላይ የሚያዘምተውን
እጅግ ጨፍጫፊ የጦር ሃይል ያን ያህል በተራዘመ የትጥቅ ትግል ሒደት ለማስወገድ ሲባል ድፍን 17 ዓመታትን የፈጀና ሁለቱንም ጎራ
እጅጉን የሚዘገንን የህይወት መስዋዕትነት ያስከፈለ ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ጦርነት ሲካሄድ መቆየቱም የማይስተባበል አሳዛኝ እውነታ
ነው፡፡ ይህ በትናንቱ የዚች አገር ወንድማማች ህዝቦች የታሪክ ሂደት ውስጥ እየተጋፈጥን ያለፍነው መራር እውነታ በተለይም ዛሬ ለገጠመን
ፖለቲካዊ ቀውስ ማንፀሪያነት ይጠቅማል ከሚል እምነት ሳላነሳው ማለፍ የማይኖርብኝ ተያያዥ ጉዳይ ግን አለ፡፡
እርሱም ደግሞ ደርግን በተራዘመና ገጠርን ማዕከል አድርጎ በተካሔደው ፀረ ጭቆና የትጥቅ ትግል
ለማስወገድ ሲባል ፤ በተለይም የሰሜናዊ ኢትዮጵያን ወንድማማች ህዝቦችን ከጎናቸው አሰልፈው ጨቋኙን የአገዛዝ ስርዓት የመፋለምና
ትግሉን ድል የማቀዳጀት ታሪካዊ ሃላፊነታቸውን የተወጡት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለእያንዳንዱ አካባቢ የነፃ መሬታቸው ነዋሪ ህብረተሰብ
ሀብት ንብረት የተለየ ጥንቃቄ የሚያደርጉበት አግባብ እንደነበር ለማስታወስ ፈልጌ ነው፡፡ ለአብነት ያህልም፤ አብዛኛውን የትጥቅ
ትግሉ ዘመን እንቅስቃሴ ባስተናገደው የያኔው የትግራይ ክፍል ሀገር ከተደጋጋሚ የደርግ ሰራዊት መጠነ ሰፊ ወረራ ጋር የሞት ሽረት
ፍልሚያ እየገጠሙ ድርጅታዊ ህልውናቸውን ጨርሶ ከመጨፍለቅ አደጋ መታደግም ጭምር ይጠበቅባቸው የነበሩት የህወሐት፤ ብሎም የብአዴን
ታጋዮች “ሆነ ብሎ ማንኛውም ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ የመሰረተ ልማት ተቋም ላይ ጥቃት መፈፀም የለየለት ፀረ ህዝብ አቋም እንደ
መያዝ ስለሚቆጠር ያን አድርጎ የተገኘ ታጋይ ከባድ ቅጣት እንደሚጠብቀው መገንዘብ አለበት” የሚል መርህ ያራምዱ ነበር፡፡
ከዚህ ፅኑ እምነታቸው የተነሳምነው መላውን የሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል ከገጠር እስከ ከተማ ከወታደራዊ
የደርግ ኢ.ሠ.ፓ መንግስት ፈርጄ ብዙ የአፈና መዋቅር ነፃ እያወጡ ወደ መሀል አገር ዘልቀው እስኪገቡ ድረስ እንብዛም ትርጉም ያለው
የህዝብ ቅሬታ ያስከተለ ሀብት ንብረት በማውደም የሚጠቀስ አንድም የጦርነት ውሎ አጋጣሚ ያልተገኘባቸውም፡፡ ሌላው ቀርቶ በ1983ቱ
የግንቦት 20 ድል ዋዜማ “አዲስ አበባም ልክ እንደ ላይቤሪያው መዲና እንደሞኖሮቪያ የስርዓት አልበኝነት መፈንጫ የመሆን እጣ ይገጥማታል”
ሲሉ የተነበዩ ዓለምአቀፋዊ የሚዲያ ተቋማት ጥቂት እንዳልነበሩ ይታወቃል፡፡ ድል አድራጊው የኢህአዴግ ሰራዊት ወደ ከተማዋ መግባቱን
ተከትሎ የተስተዋለው ተጨባጭ እውነታ ግን ትንቢቱን ፉርሽ የሚያደርግ ሆኖ ነበር የተገኘው፡፡
በግልፅ አነጋገር ፤ ያኔ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ሰራዊት ራሻ ሰራሾቹን
ዘመናዊ መድፎችና ታንኮች ጨምሮ፤ ሌላም ሌላም ተወንጫፊ ሮኬቶችን የሚተኩስ የጦር መሳሪያ አሰልፎ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር እንኳን
አንድም ፋብሪካ ስለመቃጠሉ አልሰማንም ነበር፡፡ እነሆ ዛሬ ግን አገር አማን ነው ብለን በተቀምጥንበት፤ ከአንድ ደርዘን የማያንሱ
ፋብሪካዎች ላይ የቃጠሎ አደጋ ለማድረስ የሞከሩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ሃይሎች መኖራቸውን ለመታዘብ በቅተናል፡፡ እነዚሁ ቡድኖች ከአምና
እስከ ዘንድሮ በዘለቀ የሁከትና ግርግር ተቃውሟቸው ምክንያት ያወደሙትን የህዝብ ሀብት ንብረት መጠንም ቤት ይቁጠረው እንጂ እኔ
ለጊዜው ዝርዝር ማብራሪያ ለመስጠት የሚያስችል መረጃ የለኝም፡፡
ጉዳዩን የበለጠ አስገራሚና ለመፍታት የማያመች እንቆቅልሽ የሚያደርገው ምክንያት ደግሞ ፤ እነ
ስልጣን አረቄው ይሄን ሁሉ ሀገር አውዳሚ ዕኩይ ተግባራቸውን የሚፈፅሙት “ለሚታገሉለት ህዝብ ዘላቂ መብትና ጥቅም መረጋገጥ” ሲሉ
እንደሆነ ያለ አንዳች ሀፍረት ሊያሳምኑን ሲሞክሩ የመደመጣቸው ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ሊሆነን የሚችለውም በተለይ ጂሐር
መሐመድ የሚባለው ግለሰብ ከላይ በተጠቀሰው ሰሞነኛ ቃለምልልሱ አስረግጦ የተናገረውና እቺን ሀገር የሽብርተኞች መፈንጫ ሊያደርጓት
እንደሚፈልጉ የገለፀበትም ጭምር ዛቻ ነው፡፡
ታዲያ ጉዳዩን እንደምሳሌ ከተወሳው የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የትጥቅ ትግል ታሪክ ጋር ስናነፃፅረው፤
እነስልጣን አረቄው የኦ.ነ.ግ እና የመሰሎቹ መሪዎች አሁን ላይ እንደፈሊጥ የያዙት፤ የዚችን ምስኪን ሀገር አንጡራ ሀብት ንብረት
እንደተራ የቆሻሻ ክምር በእሳት እያጋዩ ከማውደም በሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ መንግስትን የማዳከም “ስትራቴጂ” በእርግጥም መስከራቸውን
የሚያመለክት አይደለምን? ለዚህ ጥያቄ የእናንተን ምላሽ ለእናንተው ትቼ፤ በእኔ እምነት ግን ወቅታዊውን የሰላምና መረጋጋት ችግር
የጋረጡብን የጥፋት ሃይሎች ሁሉ፤ በሚቋምጡለት ስልጣን የመጨበጥ ምኞታቸው ምክንያት አእምሯቸውን እስኪስቱ ድረስ ሰክረው መሆን አለበት
እንጂ ይህን ዕኩይ ተግባር “ለህዝብ ጥቅም ሲባል የሚፈፀም ነው” አይሉም ነበር ባይ ነኝ፡፡ መዓ ሰላማት!
No comments:
Post a Comment