Friday, 30 September 2016

ቀበሮ የበግ ላት ይወድቅልኛል ብላ…




ኢብሳ ነመራ
በውጭ አገራት፤ በተለይ በሰሜን አሜሪካና በአንዳንድ የአውሮፓ አገራት የሚኖሩ፤ እድላቸው ሆኖ የትምክህትና የጠባብነት ልክፍታቸው አልሽር ያላቸው፤ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት መረጋገጥና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት መመስረት ራስምታት የሆነባቸው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያለፈውን ዓመት አብዛኞቹን ወራት አቅላቸውን ስተው ነበር የከረሙት፤ አቅላቸውን ያሳታቸው ደግሞ በአንዳንድ የአማራ አካባቢዎችና በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ተቀስቅሰው የነበሩ ሁከቶች ናቸው። እነዚህ ሁከቶች ትምክህተኞቹን ካሁን አሁን ፌደራላዊ ሥርዓቱን ንዶ  የአንድ ብሄራዊ ማንነት የበላይነት የነገሰበት ሥርዓት ሊመለስ ነው የሚል፤ ጠባቦቹን ደግሞ ፌደራላዊ አንድነቱ ፈርሶ ገንጥለን የምንገዛው አገር ልናገኝ ነው የሚል ገጉት ነው አቅል ያሳታቸው፤ “ቀበሮ የበግ ላት ካሁን አሁን ወደቀ ብላ ለሃጯን እያዝረበረበች ስትከተል ዋለች” እንደሚባለው መሆኑ ነው።
እርግጥ ዜጎች በተለይ ወጣቶች በሁከት እስኪገነፍሉ ቅሬታ የፈጠረባቸው ነገር መኖሩ አይካድም። ይህም የባለፉት አንድ ተኩል አስርት ዓመታት የኢኮኖሚ እድገት ተጠቃሚነት ያልደረሳቸውና የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ስልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀማቸው የተፈጠረው የመልካም አሰተዳደር መጓደልና የፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል መዛባት የፈጠረው ቅሬታ ነው። በወጣቶች ላይ ቅሬታ የፈጠረው ሁኔታ ከገዢው ፓርቲ ኢህአዴግና ከመንግሥት ችግር የተፈጠረ መሆኑን በይፋ አምነዋል። ይሁን እንጂ፤ ቅሬታዎቹ መፍትሄ የሚያገኙበት ሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ነበር። በቅድሚያ ቅሬታዎቹ አውዳሚ ባልሆነ መንገድ ቀርበው በውይይት እልባት ሊያገኙ የሚችሉበት ልማዳዊ አሰራር አለ። ይህ ካልሆነ ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ አልሰጥ ያለውን መንግሥት በምርጫ ማስወገድ ይቻላል። ሁኔታዎች የከፉና አጣዳፊ ቢሆኑ እንኳን ሕዝብ የመረጣቸውን ወኪሎቹን ጠርቶ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረግ የሚቻልበት ሥርዓት ነበር።
ይህን ስር የሰደደ ቅሬታ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ እንዲፈታ ከማድረግ ይልቅ በድንገት ወደአውዳሚ የኃይል ተቃውሞ እንዲሸጋገር በማድረግ ረገድ ከኤርትራ መንግሥትና በኤርትራ መንግሥት በኩል አንዳንዶቹም በቀጥታ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር ያለተቀደሰ ጋብቻ የፈፀሙ ትምክህተኛና ጠባብ ብሄረተኛ ቡድኖች መኖራቸውን የሚያመለክቱ ተጨባጭ ሁኔታዎች አሉ ። ይህ ተጠልፎ ወደሁከትነት የተቀየረ ሁኔታ ነበር ካሁን ካሁን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ይንዳል በሚል ህልም ሲያቅነዘነዛቸው የነበረው፤ የበግ ላት የወድቃል ብላ ስትንከራተት እንደዋለችው ቀበሮ።
ታዲያ ትምክህተኛ ጠባብ ብሄረተኞች ሁከቱ የሥርዓት ለውጥ የማምጣት አቅም እንዲኖረው ለማድረግ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። በማህበራዊ ሚዲያ የእርስ በርስ ግጭት እንዲቀሰቀስ አድርገዋል። በዚህ ዘመን እጅግ ጸያፍ የሆነ የዘር ማጥራት እርምጃ አነሳስተዋል። ሕዝብ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ፣ በተለይ ወጣቱ በመንግሥት ላይ ተቆጥቶ እንዲነሳ ያለምንም ሃፍረት ሃሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት ቀስቅሰዋል። በሰሜን አሜሪካና በአንዳንድ የአውሮፓ ከተሞች የኢፌዴሪን መንግስት የሚቃወም ሰልፍ አካሂደዋል፣ መቶም፤ ሃምሳም ሆነው። ኢትዮጵያ በመንግሥታትና በዓለም አቀፍ ተቋማት በክፉ ገጽታ እንድትታይ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል። በአሜሪካ አንድ ሎቢ የሚያደርግላቸው ሴናተር በመግዛት የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያሳድር ማድረግ የሚያስችል RH 2016 የተሰኘ ደንብ ለማስጸደቅ በመፈጨርጨር ላይ መሆናቸውንም ሰምተናል።
ከሁሉም የሚያሳዝነው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ብሄራዊ ማንነት፣ ሃይማኖት፣ አመለካከት፤ ወዘተ. ሳይለያየው በአንድ አቋም ታላቅ አገራዊ መግባባት ፈጥሮ በራሱ አቅም እየገነባው የሚገኘውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማስተጓጎል ቃል ገብተው በእርስ በርስ ግጭት የምትታመስና ደካማ ኢትዮጵያ ከማየት ያረጀ አመለካከት ያልተላቀቁ ግብጻውያንን ማስፈንደቃቸው ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የማይቋረጥ መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቢያውቅም፣ በራሱ ልጆች ሴራ በግብፆች ዘንድ የተፈጠረው ኢትዮጵያ ደካማ ትሆናለች፣ የግድቡም ግንባታ ይቆማል የሚል ተስፋ ተፈጥሮ ማየቱ ነው እጅግ ያሳዘነው፤
ያም ሆነ ይህ፤ በውጭ አገር የነበረው ላቱ ይወድቅልኛል ብላ በጉን ስትከተል እንደዋለችው ቀበሮ፤ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ሊናድ ነው በሚል ተስፋ አቅላቸውን ያጡ የአሃዳዊ ሥርዓት ናፋቂ ትምክህተኞችና ትንሽዬ የሚገዙት አገር ለመፍጠር ያለሙ ጠባቦች፤ በተለየ በውጭ አገራት በሚኖሩ መሰሎቻቸው ዘንድ የኢትዮጵያ መንግሥት አለቀለት፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፊት ነስቶታል የሚል ስሜት መፈጠሩን የሚያመለከቱ ሁኔታዎችን ታዝበናል። በሌላ በኩል፤ ይህ ሁኔታ አገሪቱን ፈውስ ለሌለው መከፋፈል ይዳርጋታል የሚል ስጋት የተፈጠረባቸውም አሉ።
ታዲያ ሰሞኑን በአሜሪካ ኒውዮርክ የተካሄደው 71ኛው የተባበሩት መንግሥታት ጉባኤና በተለይ በተጓዳኝ የተካሄዱት የስደተኞችን ጉዳይ የሚመለከት ዓለም አቀፍ መድረክ እንዲሁም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊዎች ጋር በወቅታዊ ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያካሄዱት ውይይት ኢትዮጵያ አሁንም ዓለም የሚፈልጋት አገር መሆኗን በግልጽ አሳይቷል። ልትፈርስ ነው በሚል ለፈነደቁት፣ ለሰጉትም፤ ውዥንብሩን ገፈፍ አደርጎታል።
ይህን ለማሳየት ያህል ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅተ 71ኛ ጉባኤ በተጓዳኝ በአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ አስተባባሪነት ስድስት አገራት፤ ማለትም ካናዳ፣ ጀርመን፣ ጆርዳን፣ ሜክሲኮ፣ ስዊድን፣ ኢትዮጵያ በተሳተፉበት የስደተኞችን ጉዳይ የተመለከተ የውይይት መድረክ ላይ ፕሬዝዳንት ኦባማ ኢትዮጵያን አስመልክተው የተናገሩትን አጠቅሳለሁ።
ፕሬዝዳንት ኦባማ በንግግራቸው፣ ኢትዮጵያ የተለያዩ ሃገራትን ስደተኞች ተቀብላ ሰብአዊ ድጋፍ በማድረግ አርአያነት ያለው ተግባር እየፈፀመች ብለዋል። አያይዘውም፤ ጀርመን፣ ቱርክ፣ ፓኪስታን፣ ካናዳና ስዊድንም አስተዋጾአቸው የጎላ መሆኑን ያወሱት ፕሬዚዳንቱ፥ ሌሎች አገሮችም ይህንኑ ተሞክሮ ቢጋሩ በስደተኞች ላይ እየደረሰ ያለውን ውስብስብ ችግር መፍታት ይቻላል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የዓለማችን አንድ በመቶ ወይም 65 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች ተሰዶ ይገኛል። ከእነዚህ ስደተኞች መካከል አብዛኛዎቹን አስጠግተዋቸው የሚገኙት 10 የማይበልጡ አገሮች መሆናቸውን ያመለከቱት ፕሬዝዳንት ኦባማ፣ ኢትዮጵያም 800 ሺህ ስደተኞችን በማስጠጋት ከአፍሪካ ቀዳሚውን ስፍራ መያዟን አስታውሰዋል። በተለያዩ የዓለም አገራት በስደት የተጠጉ ሰዎች የትምህርት እድል፣ ፍትህ የማግኘትናእኩልነት የመታየት ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አሳስበዋል።
በዚህ መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ባላት አቅም ሁሉ ስደተኞችን በመቀበል ድጋፏን እነደምታጠናክር ገልጸዋል። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ስደተኞች ያለምንም መገለል የትምህርት እድል እንዲያገኙ፣ በግብርና እና በሌሎች የሥራ መስኮች እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል። በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ 30 በመቶ ለስደተኞች የሥራ እድል  መመቻቸቱንም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ ለተቀበለቻቻው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች፤ በተለይ የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችላትን አቅም እንድታጎለብት የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ 200 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ብድር ለመስጠት ወስኗል። የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የሚሰጠው ብድር በአገሪቱ ለሚገኙ ስደተኞች የሥራ እድል የሚፈጥሩ ሁለት ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት የሚውል መሆኑን ከባንኩ የተገኘ መረጃ ያመለክታል። በዚህ ብድር በአገሪቱ ከሰፈሩ 850 ሺህ ያህል ስደተኞች መካከል 30 ሺህዎቹ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ እንዲያገኙ ይደረጋል።
ይህም ብቻ አይደለም። በቀጣይነት በኢትዮጵያ ከተጠለሉ ስደተኞች መካከል 100 ሺህ ስደተኞች በኢንዱስትሪ ፓርኮች የስራ እድል የመፍጠር እቅድ ተይዟል። ይህን እቅድ ለማሳካትአጠቃላይ 500 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋል ተብሏል። ለዚህ እቅድ ተግባራዊነትም የአለም ባንክ፣ ብሪታንያ እና ሌሎች የአውሮፓ አባልገራት ደጋፍ ለማድረግ ስምምነታቸውን ገልጸዋል።
የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዚዳንት ዌርነር ሆዬር ወደአውሮፓ ከሚሄዱ ስደተኞች መካከል በርካቶቹ አደገኛውን ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት ኢትዮጵያ ማረፊያቸው መሆኗን አስታውሰው፣ የተሻለ አማራጭ እና የገቢ ምንጭመፍጠር በአቅራቢያቸው እንዲቆዩ በማድረግ፣ ወደ አውሮፓ የሚደረገውን አደገኛ ጉዞ ለመቀነስ እንደሚረዳ አመልክተዋል።
በተባበሩት መንግስታት 71ኛ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ወደአሜሪካ ኒው ዮርክ ተጉዞ የነበረው በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም የሚመራው ቡድን እገረ መንገዱንም ከአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተገናኝቶ ተነጋግሮ ነበር። ከመገናኛ ብዙሃን የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድና አንደር ሴክሬተሪ ሻነን ስሚዝ ጋር ተወያይተዋል። በዚህ ወቅት የኢፌዴሪ መንግሥት በተለይ በጽንፈኛ ዳያስፖራ ወፌ ቆመች ሲባለለት የነበረውን ኢትዮጵያን የማፍረስ ዓላማ ያለው ሁከት በተመለከቱ ጉዳዮች ዙሪያ ለውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች ማብራሪያ ተሰጥቷል። በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ግጭትና ግጭቱን ለመፍታት እየተደረገ ስላለው ጥረትም ማብራሪያ ሰጥተዋል። መንግሥት የግጭቱን መንስኤ በመለየት የተለያዩ የመፍትሄ እርምጃዎችን በመውስድ ላይ መሆኑንም በዝርዝር ማብራራታቸውን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ግርማ ብሩ አስታውቀዋል። በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተውን ግጭት ለመፍታት መንግሥት እየተከተለ በሚሰጠው መፍትሄ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ኃላፊች ደስተኞች መሆናቸውን መግለፃቸውንም መገናኛ በዙሃን ዘግበዋል።
እዚህ ላይ ችግሩን ለመፍታት አየተወሰደ ያለው እርምጃ የቱ ነው? ሊባል ይችል ይሆናል። መልሱ፤ የችግሩን ምንጭ በውጭ አካላት ላይ ከማላከክ ይልቅ ወደ ውስጥ በመመለከት ለመለየት የተደረገው ጥረት ነው። በዚህም የችግሩ ምንጭ የኢኮኖሚው እድገት የሕዝቡን ፍላጎት ሊያረካ በሚችል ልክ አለማደጉና አንዳንድ የመንግሥት ኃላፊዎች ስልጣናቸውን ሕዝብን ከማገለገል ይልቅ ለግል መገልገያነት በማዋል የመልካም አሰተዳደር መጓደልና የሃብት ክፍፍል መዛባት መፍጠራቸው መሆኑ ተለይቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም ይህን ጉዳይ በተባበሩት መንግስታት 71ኛ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግርም አንስተውታል።
ለማስታወስ ያህል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም ባደረጉት ንግግር በየአገራቱ ያለው ችግር ምንጭ ውስጣዊ ነው። ይህን በመቀበል ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ አገር ነች። የውስጥ ችግርን ምንጭ ወደውጭ በማላከክ የሚደረግ መፍትሄ ፍለጋ ችግር ከማስከተል ያለፈ ፋይዳ የለውም ነበር ያሉት፤
እርግጥ፤ ይህ የችግሮችን ምንጭ ወደራስ የመወስድ አካሄድ ለኢትዮጵያ መንግሥትና ለገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ አዲስ አይደለም። ከአስር ዓመት በፊት በተዘጋጀው የውጭ ጉዳይ እና የደህንነት ስትራቴጂ ላይ የሰፈረ ጉዳይ ነው። በዚህ ስትራቴጂ መሰረት መሰረታዊ የአገሪቱ ችግር ድህነትና የዲሞክራሲ መጓደል መሆኑ ተገልጿል። የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን ማጥቃት የሚችሉት እነዚህ ችግሮች እስካሉ ድረስ ብቻ መሆኑንም ስትራቴጂው ያስረዳል። እናም በስትራቴጂው መሰረት ቀዳሚው የውጭ ጣልቃ ገብነትን መከላከል የሚያስችለው ብቸኛ መንገድ ድህነትን ማስወገድና ዴሞክራሲን ማስፈን ነው። እንግዲህ የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የሥራ ኃላፊዎች በሰሞኑ ችግር አፈታት ላይ ያደነቁት ይህን የችግር አያያዝ ሥርዓት መሆኑ እርግጥ ነው። መንግሥት የአገሪቱን ችግር የሚፈታው ለአሜሪካ መንግሥት ብሎ ባይሆንም፤ ጽንፈኛ ዳያስፖራዎች የፈጠሩትን ውዥንብር ማጥራት በመጠቃቀም ላይ ለተመሰረተ የአገራት መልካም ግንኙነት ስለሚያግዝ  ግልፅ እይታ መፍጠሩ አስፈላጊ ነው።
ከሰሞኑ ሁኔታ ወጣ ባሉ ጉዳዮችም ላይ ውይይት ተደርጓል። ይህም በምስራቅ አፍሪካ ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር በሚቻልበትና የኢትዮጵያ ሚና በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር  ኃይለ ማሪያም፤ ኢትዮጵያ በተለይ በሶማሊያም ሆነ በደቡብ ሱዳን ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የምታደርገውን የመሪነት ሚና አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል። ኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ወደ ድርድር እንዲመጡ ግጭቱ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ጥረት በማድርግ ላይ መሆኗንም አስረድተዋል። በሶማሊያ አልሸባብን በመዋጋት አካባቢው ከሽብር ስጋት ነፃ እንዲሆን የማድረግ ሚናዋንም እየተወጣች ነው ብለዋል። አምባሳደር ግርማ ብሩ በጉዳዩ ላይ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ብሎም በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን እያደረገች ያለውን ጥረት አሜሪካ እንደምትደግፍ አረጋግጠዋል።
እንግዲህ ኢትዮጵያ እጅግ በከፍተኛ የመንግሥታት ድምጽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሆና መመረጧ ይታወሳል። ከዚህ በተጨማሪ፤ ቀደም ባሉት ዓመታት ለአፍሪካ፤ በተለይ ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላምና መረጋጋት ያበረከተችውን አስተዋፅኦና በገለለተኝነት ሰላምን የማስከበርና የመጠበቅ ብቃቷን መነሻ በማድረግ ባለፈው ሰኔ በደቡበ ሱዳን መንግሥት ተፋላሚዎች መካከል ያገረሸውን ውጊያ በመከላከል የአገሪቱን ሰላም የመጠበቅ ኃላፊነት ለአፍሪካ አገራት ሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲሰጥ ሲወሰን በቀዳሚነት ተመርጣለች።
ከሃያ ስድስት ዓመታት በላይ መንግሥት አልባ ሆና ስትታመስ የነበረችው ሶማሊያም አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖባት ለመጀመሪያ ጊዜ የምስራቅ አፈሪካ አገራት በይነ መንግስታትን (ኢጋድ) ጉባኤ ለማካሄድ በቅታለች። የኢጋድ አባል አገራት መሪዎች በሞቃዲሾ ተገኝተው የቀጠናው ልማትና ሰላም ላይ መክረዋል። ይህ የኢጋድ ስብሰባ በሞቃዲሾ መካሄድ የሶማሊያ ሰላም ምን ያህል  እንደተሻሻለ ያሳያል። ሶማሊያ ከመንግሥት ምስርታ ጀምሮ አሁን የደረሰችበትን አካባቢያዊ ሁነት ማስተናገድ ያስቻለ ሰላም እንዲገኝ በማድረግ ረገድ ኢትዮጵያ ትልቁን ድርሻ ትወስዳለች። የሶማሊያ ሰላም የኢትዮጵያን ለቀጣናው ሰላም ያላትን ቁርጠኝነትና ብቃት ለዓለም ያሳየ፤ የዚያኑ ያህል ተቀባይነቷንም ከፍ ያደረገ ሁኔታ ነው።
በአጠቃላይ የተወሰኑ በውጭ አገራት የሚኖሩ የትምክህትና የጠባብነት ጽንፍ ቡድኖቸ የኢትዮጵያን ገፅታ ለማበላሸት ያደረጉት ጥረትና በአንዳንድ እዚያው በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የነዙት ኢትዮጵያ በምእራባውያን ዘንድ ተቀባይነት እያጣች ነው የሚል ወሬ መሰረተ ቢስ መሆኑን ያሳያል። ኢትዮጵያ አሁንም በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ውስጥ ትኩረት የሚስብ ድርሻ ያላት ዓለም የሚፈልጋት አገር ነች። የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትም አልተናጋም። ሥርዓቱ ካሁን አሁን ተናደ የሚለው ተስፋ የበግ ላት ይወድቅልኛል ብላ ለሃጯን እያዝረበረበች ስትከተል እንደዋለችው ቀበሮ ከንቱ ተስፋ ነው።

No comments:

Post a Comment