Monday, 6 February 2017

የአረንጓዴው ልማት ተስፋዎች




አባ መላኩ
የአገራችን አካባቢዎች በተራሮች ላይ በተሰሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎች ከታች ላሉት ማሳዎች አነስተኛም ሆነ ከፍተኛ ፍሰት ያላቸው ወንዞች ሳይቀሩ ፍሰታቸው የበለጠ እንዲጨምር አድርጓል፤ በድምር ውጤቱም ግድቦችም ከደለል እና አላስፈላጊ ቆሻሾች መሞላት ታድጓል። በአገራችን ከሦስት እና አራት አመታት በፊት የተጎዱ ማሳዎች፣ ቦረቦሮች እና ቁጥቋጦዎችንም ሆነ የግጦሽ ሳር ለመመልከት አዳጋች ነበር። ዛሬ ዛሬ በተሰሩ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎች አፈሩም፣ ውሃውም፣ ቁጥቋጦዎችም ከሰውም ሆነ ከእንስሳት ንክኪ ነፃ ተደርገዋል።
ይህ በመሆኑም የደን ልማቱ ተስፋፍቶና የምንጭ ውሃው ጎልብቶ ለማስተዋል ተችሏል። በዚህም አርብቶ አደሩም ሆነ አርሶ አደሩ ዘመን የተሻገረውን የመጠጥ ውሃ ችግርን ለመቅረፍ አስችሎታል። የደን ልማቱ ለአካባቢው ማህበረሰብ እየሰጠ ያለው ጥቅም የላቀ ነው የሚባለው በዋናነት የስራ እድል በመፍጠሩ ነው። የደኑን ጥብቅነት ደጀን በማድረግ ወጣቶች ተደራጅተው በተለያዩ ስራዎች እንዲሰማሩ በማድረግ ስራ አጥ ወጣቶችን የስራ እድል በመፍጠር ሌላ ተልዕኮን እንዲይዝ አድርጓል።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት እንቅስቃሴ በተለያዩ አገራትና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተቀባይነት እያገኘና ለሌሎች አገራት በአርአያነት እየቀረበ ይገኛል።  ከእነዚህ አገራት መካከልም አሜሪካ አንዷ ናት።
ኢትዮጵያ በጎርጎሮሳዊያኑ 2025 ልታሳካ የምትፈልገውን ከካርቦን ልቀት ነጻ የሆነ ኢኮኖሚ እውን ለማድረግ እየሰራች መሆኗን በበርካቶች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ተግባር ሆኗል፡፡ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ኖረዌይ፣ ስዊድን እና እንግሊዝ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት እንደሚደግፉ በተለያየ ወቅት ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡
ባለፉት ዓመታት በፊት የተነደፈውና እስካሁን ድረስ በተገቢው መንገድ እየተከናወነ ያለው  የአየር ንብረት ለውጥንዘላቂ የአረንጓዴ ልማት ለማምጣት በሚያስችል ተግባር ውጤታማ እየሆነ መምጣቱ ያደባባይ ምስጢር ሆኗል።  ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ጥቂት አገሮች ተርታ የተሰለፈችበትን የአየር ንብረትን በመቋቋም አረንጓዴ የኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ ብትነድፍም፣ ለጥቂት ዓመታት በተግባር ላይ ሳታውለው ከቆየችበት ምክንያት አንዱ የፋይናንስ እጥረት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ከከባቢ አየር ብክለት ነፃ የሆነና ዜሮ የካርቦንዳይኦክሳይድ በካይ ጋዝ ደረጃ ላይ ትደርስበታለች ተብሎ ይፋ የተደረገ ብሔራዊ ዕቅድ ነው፡፡
በደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ በተደረገው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ ይፋ የተደረገው ይህ ስትራቴጂ፣ በወቅቱ እንግሊዝና ኖርዌይን ጨምሮ ጥቂት የአውሮፓ አገሮች ፖሊሲው ከሚፈልገው ገንዘብ ውስጥ ቁንጣሪውን ለመርዳት ቃል ገብተው ነበር፡፡ በፖሊሲው መሠረት ኢትዮጵያ ከካባቢ አየር ብክለት ነፃ የሆነ ኢኮኖሚ ለመፍጠር፣ 150 ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ ገንዘብ ያስፈልጋታል፡፡
በወቅቱ ይፋ የተደረገው ስትራቴጂ እንደሚያትተው፣ ይህንን ገንዘብ ምዕራባውያኑ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ገንዘቡ ለአየር ብክለት ተጋላጭ የሆኑ (ለብክለት አስተዋጽኦ ሳይኖራቸው በግሪንሀውስ ጋዝ ልቀት የሚጎዱ) አገሮች በካሳ መልክ የሚያገኙት እንጂ ችሮታ ወይም ዕርዳታ ተደርጎ መታየት የለበትም ሲሉ ይሟገታሉ፡፡ 
መንግሥት 15 ዓመት ውስጥ ለአረንጓዴ ልማት ያስፈልገኛል ያለውን 150 ቢሊዮን ዶላር ፋይናንስ፣ ደኖችን በማፋፋት በእነሱም የሚታመቀውን ካርቦንዳይኦክሳይድ በመለካትና በመሸጥ የካርቦን ፋይናንስ እየተባለ የሚታወቀውን ስልት ለመከተል ያስባል፡፡ ከአሥራ አምስት ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ የነፍስ ወከፍ ገቢ በአማካይ 1000 ዶላር ደርሶ አገሪቱ መካከለኛ ኢኮኖሚ ይኖራታል ብሎ የሚያስበውና ለዚሁ እየሰራ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሠረት ሊያሳካው እንደሚችል አቅዶ እየሰራ ይገኛል፡፡
ፖሊሲውን ለማስጸፈም ይረዳሉ የተባሉ የመተግበሪያ ረቂቅ ማኑዋሎች ላይ ውይይት ተደርጎባቸው ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ በዚህ መሠረት አዲስ የተቋቋመው የአካባቢና የደን ሚኒስቴር ስልታዊ የሆኑ የቴክኒክ ዝርዝር ማኑዋሎችን አዘጋጅቷል፡፡ መንግስት ከውጭ መንግሥታት ገንዘብ መገኘቱን ተከትሎ እያንዳንዱ የመንግሥት መሥሪያ ቤት፣ የሚያከናውነውን ሥራ በተመለከተ ዕቅዱን ሲያቀርብ፣ የሥራ ክንዋኔው የሚገመገምበት አሰራር ለውይይት ቀርቦ አስተያየት ተሰጥቶበታል፡፡
ዓለም የኢኮኖሚ ውጣውረድ ውስጥ መግባቷ ኢትዮጵያ የምትፈልገውን 150 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ለማግኘት የሚያስችሉ አጋጣሚዎች ላይ ተፅዕኖ ቢኖረውም   አንዳንድ አገሮች የተሻለ የገንዘብ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ። በሌላ በኩል ግን የአገሪቱን የአካባቢ ጥበቃ ሲመራ የነበረው ተቋም ማለትም የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ከዚህ ቀደም በነበረው የአሠራር ስልት ሲተች ቆይቷል፡፡
ይኸውም የተቋቋመለትን አካባቢን የመንከባከብ ተግባር በሥራ ጠባያቸው የጥቅም ግጭት ላለባቸው መሥሪያ ቤቶች ሥልጣኑን በውክልና መስጠቱ ነው፡፡ ለምሳሌ የመንገዶች ባለሥልጣን በሥሩ የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ የሚያካሂድለት የራሱ አካል አለው፡፡ ግብርና ሚኒስቴር ዓላማው ግብርናን ማስፋፋት ሆኖ ሳለ፣ ደንን እንዲንከባከብ ኃላፊነት መውሰዱ የአገሪቱን የአካባቢ ጥበቃ በተቀናጀ ሁኔታ ለመፈጸም የራሱ አሉታዊና አወንታዊ ሁኔታዎች ሊኖሩት እንደሚችሉ መገመት አይከብድም።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በአለማችን ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ ከሆኑ 10 ሀገራት መካካል አንዷ መሆኗን የመንግስታቱ ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ድርጅት ጥናት ያመለክታል፡፡ በአማካይ ሙቀት መጠን መጨመርና የዝናብ ስርጭት መዛባት የመሰሉ ቀጥተኛ የሆኑ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎች ተጠቂ ናት፡፡ የአገሪቱ 80 በመቶ ዜጎች መተዳደሪያ እንዲሁም 40 በመቶ ሀገራዊ ምርት የተመሰረተበት የግብርናው ዘርፍ፤ የአየር ንብረት ለውጡ ቀጥተኛ ተጠቂ መሆናቸው ተጋለጭነቱን ያባብሰዋል፡፡ የአየር ንብረት በአለማችን ላይ ከደቀነው ተጨባጭ አደጋ ባሻገር የዘላቂ ልማት አማራጮችን ይዞ መምጣቱ አልቀረም፡፡
መንግስት በዘርፉ የተሻለ ልምድ ያላቸውን የልማት አጋር አካላትን ለመሳብ ጥረት እንደሚደረግም ስትራቴጂው ያመለክታል፡፡ ኢትዮጵያ በተለመደው የኢኮኖሚ ዕድገት አማራጭ ብትጓዝ 2002 . የነበራት 150 ሚልዮን ቶን የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት 2022 . ከዕጥፍ በላይ በማደግ 400 ሚልዮን ቶን ይደርሳል፡፡
የልማቱ ኢትዮጵያ የምትከተለው የአረንጓዴ ልማት ዕድገት አማራጭ ምንነት፣ ከልማትና ትራንስፎርማሽን ዕቅዱ ጋር ያለው ቁርኝት፣ አዋጭነት፣ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብና ለአከባቢያዊ ሀገራት ያለው ፋይዳ እንዲሁም ተግዳሮቱን በተገቢው መንገድ በመዳሰስ  የአረንጓዴ ልማት ዕቀድ የአየር ንብረት ለውጥ ታሪካዊ ሀላፊነት ያለባቸው የበለጸጉት ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ተጽኖ ለመቀነስ የታዳጊ አገራት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት እየተሰራ እንዳል መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ከታዳሽ ሀይል በተለይም ከውሃ ሀይልን በማመንጨት በተነጻጻሪ ከሌሎች ሀገራት ቀድማ አረንጓዴ ልማትን መተግበር የጀመረችው ኢትዮጵያ፣ ሀገሪቱ ለአየር ንብረት ለውጥ ያላትን ተጋላጭነት በፍጥነት የአረንጓዴ ልማት ማስፈጽሚያ ስትራቴጂ ቀርጻለች፡፡ የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን፣ የደን ልማት፣ ታዳሽ ሀይል አማራጭ መከተል እንዲሁም የትራንስፖርት፣ የኢንዱስትሪ የቤት ልማትን በተስማሚ ቴክኖሎጂ መተግበር የአገሪቱ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂው መሰረቶች ናቸው፡፡
የስትራቴጂው መሰረቶች አተገባበር እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡ የመጀመሪያው የስትራቴጂው መሰረት የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን ሲሆን፣ ዘርፉ የአገሪቱ ኢኮኖሚ መሪና የአብዛኛው የሀገሪቱ ዜጎች መተዳደሪያ መሆኑ ልዮ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡ የግብረናውን ዘርፍ ለማሳደግ ከዚህ ቀደም በተለምዶ እንደሚደረገው የሚታረስ መሬትን ማስፋፋትና የቀንድ ከብቶችን ቁጥር ከማሳደግ ይልቅ የመሬትንና የቀንድ ከብቶችን ምርታማነት ማሳደግ የአረንጓዴ ልማት አቅጣጫ ነው፡፡
የተሻሻሉ የሰብልና የቀንድ ከብት ዝርያዎችን አርሶ አደሩ እንዲጠቀም ማድረግ የግብርና ዘርፍ ማሳደጊያ ሰልት ነው፡፡ የደን ጭፍጨፋን ለመቀነስ በተለይም በተራቆቱና በተጎዱ አከባቢዎች ዝቅተኛ፣ መካከለኛ እንዲሁም ከፍተኛ የመስኖ ልማት ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋትም በስትራቴጂው የተያዘ ዕቅድ ነው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂው የተመሰረተው የደን ሃብት ልማት ላይ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ደን 80 በመቶ ለሚሆኑ በተለይም በገጠሩ የሀገሪቱ ክፍል ለሚኖሩ ዜጎች የሀይል ምንጭ ነው፡፡ ከዚህ ንብ በማነብ፣ የጫካ ቡና እና ከጣውላ የሚገኘው ምርት የጠቅላላ ሀገራዊ ምርትን 4 በመቶ ድርሻ ይዛል፡፡
ለአገሪቱ ጤናማ ዕድገት ከፍተኛ ሚና ያለው የደኑ ዘርፍ ጉዳት ለመቀነስ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ስልቶችን ቀይሷል፡፡ ዜጎች ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን እንዲጠቀሙ ማድረግ፤ ከማገዶ ውጭ  በኤሌክትሪክ፣ ባዮጋዝና በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ ምድጃዎች ህብረተሰቡ እንዲጠቀም በማድረግ የደን ምንጠራን ትርጉም ባለው መጠን መከላከል የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂው ሌላው ስልት ነው፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን የተጎዱ መሬቶችን በመከለል እንዲያገግሙ ማድረግና ተጨማሪ መሬትን በደን በመሸፈን የደን ልማቱ እንዲስፋፋ የሚያደርጉ ስልቶች ናቸው፡፡ ኤሌክትሪክ ለዘመናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ የሀይል ምንጭ ነው፤ ይህንኑ ተታሳቢ በማድረግ፣ ለአገር ውስጥና ለአከባቢያዊ ፍጆታ የሚያስፈልገውን የኤሌክትሪክ ሀይል ፍጆታን፤ ከታዳሽ የሀይል ምንጮች ማስፋፋት የስትራቴጂው ሶስተኛ መሰረት ነው፡፡
ከከተሞችና እንዱስትሪዎች የሀይል ፍጆታ አንስቶ ለመስኖ የሚያስፈልገውን ውሃ ለመግፋት ይዉላል፡፡ በአማካይ 10 በመቶ በላይ የሚያድገው የሀገሪቱ አኮኖሚ በአመት 14 በመቶ በላይ የኤሌክትሪክ ሃይል ያስፈልጓል፡፡ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ለሎች የሚተርፍ ዕምቅ ታዳሽ ሀይል አማራጭ እንዳላት በዘርፉ የተሰሩ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከታዳሽ የሀይል ምንጮች ብቻ 60 ሺህ ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚያስችል ዕምቅ አቅም አላት፡፡
ከዚህም ውስጥ የሀይድሮ ዘርፉ 45 ሺህ ሜጋ ዋት በመያዝ፣ የታዳሽ ሀይል ምንጭ 75 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡ ከጂኦተርማል፣ ከንፋስና ከፀሀይ የሚገኘው ቀሪውን 25 በመቶ ድርሻ ይይዛል፡፡ ኢትዮጵያ ያላትን ታዳሽ የሀይል አማራጭ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የተረፈውን ደግሞ ወደ ውጭ በመላክ 50 ሚልዮን ቶን ለአየር ንብረት ዋነኛ መንስዔ የሆኑት ሙቀት አማቂ ጋዞችን መቀነስ ትችላለች፡፡

የህብረቱ ጉባኤና ሀገራችን ለወጣቶች የሰጠችው ትኩረት




                                                         ቶሎሳ ኡርጌሳ
28ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የህብረቱ መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ ላይ መካሄዱ ሀገራችን ወደ ቀድሞ አስተማማኝ ሰላሟ በአፋጣኝ መመለሷን የሚያመላክት ነው። ጉባኤው በመዲናችን ሲካሄድ በርካታ ጉዳዩች ተነስተዋል። ከእነዚህ ውስጥ በዋነኛነት የሚጠቀሰው የወጣቶች ጉዳይ ነው።
አዎ! የህብረቱ የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ያካሄደው ጉባኤ ላይ የቀድሞዋ የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ዶክተር ድላሚኒ ዙማ እንደተናገሩት፤ ለወጣቶችና ሕፃናት ትኩረት የማይሰጥ አገር ብሩህ ተስፋ የለውም። አክለውም የስራ ዕድል ካላገኙት አፍሪካውያን 60 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች በመሆናቸው፤ ይህን እምቅ ሃብት በመጠቀም የአህጉሪቱን ህዝቦች ህይወት ወደ ተሻለ ዕድገት ማሸጋገር እንደሚገባ አስረድተዋል።
እርግጥም የጉባኤው ቀዳሚ ጉዳይ ወጣቶች ነበሩ። ወጣቶች የአህጉሪቱ አባል ሀገራት ተስፋዎች ብቻ ሳይሆኑ፤ አባል ሀገራቱ እናድጋለን ብለው ካሰቡና ከዚህም አኳያ እቅዳቸውን ዕውን ለማደረግ ከሻቱ ለወጣቶች የግድ ቅድሚያ መስጠት ይኖርባቸዋል። ከዚህ አኳያ በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ የኢፌዴሪ መንግስት ከሀገራችን የህዝብ ቁጥር ግማሽ ያህል የሚሆኑት ወጣቶች ስራ እንዲያገኙና የሀገሪቱ የልማት ሃይል አንቀሳቃሽ ሆነው የተያዘው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግቡን እንዲመታ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ለማድረግ የራሱን ዕቅድ ይዞ እንደነበር እናስታውሳለን።
ሁላችንም እንደምናስታውሰው በወቅቱ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ለህዝብና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ መክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ “…የሀገራችን ወጣቶች የወደፊቷ ኢትዮጵያ ገንቢዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ዛሬ በምንገኝበት ወቅት የራሳቸው ፍትሃዊ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ፍላጐትና ጥያቄዎች ያሏቸው በመሆኑ እነዚህን በአግባቡ የመመለስ ጉዳይ ቀዳሚ ትኩረት ይሰጠዋል” በማለት ተናግረዋል። ይህ የመንግስት አቋምም ከወጣቶች ጥያቄዎች መካከል ሁሉንም ችግሮቻቸውን አስተሳስሮ የመፍታት ዕድል የሚሰጠው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን የማረጋገጥ ጉዳይ በመሆኑ ከያዝነው ዓመት ጀምሮ ወጣቶች የስራና የሃብት ፈጠራ እድላቸው በተጨባጭ እውን እንዲሆንና እየሰፋም እንዲሄድ ከፍተኛ ጥረት እንደሚደረግ መግለፃቸው ይታወሳል።
ይህ ጥረት ይሳካ ዘንድም የፋይናንስ አቅርቦትን ማስፋት፣ አዳዲስ የኘሮጀክት ሃሳቦችን ማመንጨትና አሳታፊ የአፈፃፀም ስርዓት መገንባትን ድግ እንደሚልና መንግስትም በያዝነው ዓመት በሁሉም ወረዳዎች የሚገኙ ወጣቶችን ለኢኮኖሚያዊ ልማት ተጠቃሚነት የማብቃት ዓላማ ያለውና ለዚህ ዓላማ ብቻ የሚውል የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ በማቋቋም ስራውን በ10 ቢሊዮን ብር እንደሚጀምር ማስታወቃቸውም አይዘነጋም። የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቀየሰው ይህ ኘሮግራም በየጊዜው እየተገመገመ አስፈላጊው የማስተካከያ ርምጃ የሚወሰድ መሆኑንም ማስታወቃቸው እንዲሁ የሚታወስ ነው።
እርግጥ ይህ የ10 ቢሊዮን ብር ተንቀሳቀቃሽ ፈንድ በቅርቡ በመንግስት ከፀደቀ በኋላ ወደ ስራ ለመግባት ተችሏል። በፌዴራል ደረጃ ከተያዘው ከዚህ ተንቀሳቃሽ ፈንድ በተጨማሪ ክልሎች የራሳቸውን በጀት በማከል የወጣቱን የስራ አጥነት ሁኔታ ለመቀነስ ርብርብ እየተደረገ ነው። ለምሳሌ ያህል በቅርቡ የኦሮሚያ ክልል ለወጣቶች ስራ ፈጠራ ያግዘው ዘንድ የስድስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በጀት ማፅደቁን ማስታወስ ይቻላል። ሌሎች ክልሎችም በተመሳሳይ ሁኔታ በጀት መመደባቸው እንዲሁ።
ታዲያ እነዚህ መንግስታዊ ጥረቶች ሀገራችን የአፍሪካ ህብረት በወጣቶች ላይ ከያዘው አቋም ጋር አንድ የሆነ አስተሳሰብ ቀደም ብላ ማራመዷን የሚያሳይ ይመስለኛል። ህብረቱ በወጣቶች የስራ ፈጠራና ተጠቃሚነት ዙሪያ የያዘው አቋም የሀገራችንን ፕሮግራም የሚያጠናክር መሆኑ ግልፅ ነው። እናም በወጣቶች የስራ ፈጠራና ተጠቃሚነት ዙሪያ የተያዙ አቋሞች ተጠናክረው ለወጣቱ ብሩህ ተስፋ ማምጣት ይኖርባቸዋል።
እርግጥ ወጣቶች የዚህች ሀገር ገንቢዎች ናቸው። ሀገራችንን ከድህነት ለማውጣት በሚደረገው ትግል ፋና ወጊዎች ሆነው መንቀሳቀስ ይገባቸዋል። በወጣቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ሀገርን ማበልፀግ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል። በእኔ እምነት እንደ ኢትዮጵያ ያለ በርካታ ቁጥር ወጣት ያለው ሀገር በወጣቱ ላይ ኢንቨስት አድርጎ ከወጣቱ አፍላ ጉልበት የሚያገኘውን ልማታዊ ፋይዳ ማረጋገጥ ካልቻለ ሁለት ችግሮች ሊያጋጥሙት ይችላሉ። አንደኛው በርካታ ቁጥር ያለው ስራ አጥ ወጣት ይፈጠርና ይህ ስራ አጥ ኃይልም የራሳቸው አጀንዳ ያላቸው የውስጥና የውጭ ሃይሎች መጠቀሚያ ሆኖ ለሁከትና ብጥብጥ በር የሚከፍት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ሀገራት ከወጣቱ ማግኘት የሚገባቸውን የልማት ተጠቃሚነት ዕውን ማድረግ አይችሉም።
እርግጥ ስራ የሌለው ወጣት ማናቸውንም ጉዳዮች እንደ ስራ ሊመለከት ይችላል—የሁከት ተግባርንም ቢሆን። ይህ ደግሞ የተረጋጋ ሰላምና የልማት ስራ የሚከናወንበትን ሀገር ሊረብሽና ወደአልተፈለገ አቅጣጫ ሊወስድ ይችላል። ለዚህ አባባሌ በቅርቡ በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው የሁከት ተግባር ሁነኛ አስረጅ ይመስለኛል። ወጣቶች በየአካባቢያቸው ካለው የመልካም አስተዳደር ችግር በተጨማሪ በሚፈለገው መጠን ስራ ሳይፈጠርላቸው በመቆየቱ፤ ለሀገራችን የውጭ ጠላቶች ለሚላላኩ የጥፋት ሃይሎች ፀረ-ኢትዮጵያ አጀንዳ ሰለባ ሆነው ነበር።
ይህ ሁኔታም በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉ የሚዘነጋ አይደለም። እናም አስቀድሞ ወጣቱን በሚፈለገው መጠን በስራ እንዲታቀፍ ማድረግ ቢቻል ኖሮ፤ የተከሰተው ጥፋት ዕውን አይሆንም ነበር—ከሀገራዊ ልማት ተጠቃሚ የሆነ ወጣት በምንም መልኩ የሀገሩን ጥቅም በመፃረር የሌሎች ባዕዳን ሃይሎች መጠቀሚያ ሊሆን ስለማይችል ነው። እናም የኢፌዴሪ መንግስት ከዚህ ዓመት ጀምሮ ወጣቱን አቅም በፈቀደ መልኩ አደራጅቶ ከልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ፕሮግራም ቀርፆ ወደ ስራ መግባቱ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ይመስለኛል።
ወጣቱ ኃይል አፍላ ጉልበት ያለው በመሆኑ፤ ሀገራት ይህን ለስራ ዝግጁ የሆነ ጉልበት በሚገባ መንገድ መጠቀም ይኖርባቸዋል። ይህን ጉልበት አጣጥሞ በተገቢው መንገድ መጠቀምም ለሀገራዊ ዕድገት ያለው ፋይዳ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው። ወጣቶች በተፈጥሯቸው ሁሉንም ነገር የመስራት ስሜት የታደሉ ናቸው። እነርሱን በማናቸውም ሀገራዊ የልማት ትልሞች ውስጥ በማስገባት ማሳተፍ ስራዎችን በአፍላ ጉልበት እንዲሁም በፈቃደኝነትና በፍላጎት ስሜት ሊተገብሩት ይችላሉ።
ይህ ደግሞ የተያዙ ዕቅዶችን ለመፈፀምና የሚፈለገውን ሀገራዊ ዕድገት ለማምጣት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል። ስለሆነም በወጣቶች ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ ውጤቱ መልሶ የሚከፍለው ሀገርን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ለዚህም ነው— የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ለወጣቶች ተጠቃሚነት ትኩረት በመስጠት አባል ሀገራቱ ወጣቱን በስራ ፈጠራ በማነፅ ከአፍላ ጉልበቱ ሊጠቀሙ እንደሚገባ የመከረው። 
እርግጥ የኢፌዴሪ መንግስት ለወጣቶች የሰጠው ትኩረት የህብረቱን ፍላጎት አስቀድሞ የተገነዘበ ነው ማለት ይቻላል። ግና እዚህ ላይ ‘ወጣቶች ሀገራችን የሰጠቻቸውን ትኩረት እንደምን ሊጠቀሙበት ይገባል?’ የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል። አዎ! ምንም እንኳን የጥያቄው ምላሽ ሊኖር የሚችለው በወጣቱ ትጋት ውስጥ ቢሆንም፤ እኔም ለመነሻ ይሆኑ ዘንድ ጥቂት ግንዛቤ ማስጨበጫዎችን ለማንሳት እሞክራለሁ።
ወጣቱ የመንግስትን ትኩረትና የተመደበለትን ተንቀሳቃሽ ፈንድ በአግባቡ ለመጠቀም ራሱን ለስራ ዝግጁ ማድረግ ይኖርበታል። በእኔ እምነት ራስን ለስራ ማዘጋጀት አንድን ችግር ለመፍታት ግማሽ መንገድ እንደመሄድ ያህል ይቆጠራል። እናም ወጣቱ አስቀድሞ ራሱን ለማንኛውም ስራ ማዘጋጀት አለበት። ማንኛውም ስራ ከችግር መውጫ ቀዳዳ መሆኑን ማመን ይኖርበታል። በአጭሩ ወጣቱ ስራን ሳይንቅና ምናልባትም በስደት ቢሄድ ለባዕድ ሀገራት ሊያበረክተው የሚችለውን የጉልበት ስራ ዓይነት ጭምር ስራዎችን አክብሮ በመስራት የመንግስትን ትኩረት አሟጦ ሊጠቀምበት ይገባል። “ስራ ክቡር ነው” የሚለውን አርማ ከፍ አድርጎ ማውለብለብ ይጠበቅበታል። ያኔ ራሱን፣ ቤተሰቡንና ከምንም በላይ እያሰበችለት ያለችውን ሀገሩን መጥቀሙ አጠያያቂ አይሆንም።
ከዚህ በተጨማሪም ወጣቱ ስራ ፈጣሪ እንጂ ስራ ጠባቂ ሊሆን አይገባም። ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የፌዴራል መንግስትና ክልሎች ወጣቱ በስራ ውስጥ እንዲያልፍ ተንቀሳቃሽ ፈንድ አዘጋጅተዋል። ወጣቱ በዚህ ፈንድ እንደምን ራሱን ለስራ ዝግጁ ማድረግ እንደሚችል ማሰብ ይኖርበታል። በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ውስጥ የተመቻቸ የስራ ምህዳር አለ። ዋናው ነገር ይህን ምቹ የስራ ድባብ በፈጠራ ክህሎት አጅቦ እንዴት ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻል ማወቁ ላይ ነው።
እናም አንድነት ኃይል በመሆኑ፤ በቅድሚያ ተደራጅቶ አዋጪ ስራን መምረጥ፣ የተገኘን ባጀት በስራ ላይ ብቻ ማዋል፣ እንደ አንድ ሆኖ ማሰብ፣ በተመረጠው ስራ ላይ በእኔነት መንፈስ መንቀሳቀስ እንዲሁም ከተጀመረው ስራ የሚገኝ ትሩፋትን በቁጠባና አግባብ በሆነ መንገድ ብቻ መጠቀም ከወጣቱ የሚጠበቁ ተግባሮች ናቸው። ስለሆነም ወጣቱ በመንግስት የተሰጠውን ትኩረት ያህል፤ እርሱም ራሱን፣ ቤተሰቡንና ሀገሩን በሚጠቅሙ ስራዎች ላይ በማዋል የነገ “እርሱነቱን” ከወዲሁ ማዘጋጀት ይኖርበታል።
በአጠቃላይ ከመሰንበቻው የተጠናቀቀው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የወሰዳቸው አቋሞች፤ ሀገራችን ከምትከተለው የወጣቶች ፖሊሲና ፕሮግራም ጋር መሳ ለመሳ የሚሄድ ነው። እናም እንደማንኛውም ሀገር ወጣት፤ የሀገራችን ወጣቶችም ይህን የአህጉሪቱን ብሎም የሀገራችንን ትኩረት በአግባቡ በማጤንና ወደ ተጨባጭ ስራ በመለወጥ ሊጠቀሙበት ይገባል እላለሁ።